You are on page 1of 66

አንድ ህብረተሰብ ወይም ማህበረሰብ ሊተሳሰርና ሊጠነክር የሚችለው

አገዛዙ ተግባራዊ

በሚያደርገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ነው !!

ለዶ/ር አቢይ በጀርመን ጉብኝታቸው ወቅት በእጅ ሊሰጥ የተዘጋጀ


የፖሊሲ ምክር !
ከፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር) 04.11.2018

ለተከበሩት ዶ/ር አቢይ አህመድ የፌዴራል ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኢትዮጵያ


ጠ/ሚኒስተር!

መግቢያ
ዛሬ በአብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮችና አገራችንንም ጨምሮ በግልጽ የሚታዩትን የተወሳሰቡ ችግሮች
ስንመለከት የችግሮቹ ዋናው ምንጮች በስልጣን ላይ ያሉት አገዛዞች እንደሆኑ መገንዘቡ ከባድ
አይደለም። አገዛዞች የመንግስቱን መኪና፣ ማለትም የሚሊታሪውን፣ የሲቪል ቢሮክራሲውን፣
የፀጥታውንና የፖሊሱን ስለሚቆጣጠሩ በዚህም አማካይነት የህዝቦቻቸውን ዕድል በአዎንታዊም ሆነ
በአሉታዊ መልክ ይወስናሉ። ይህ ጉዳይ ደግሞ ሊወሰን የሚችለው ባላቸው ንቃተ-ህሊናና የዕውቀት
ዐይነት ነው።

የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ የአገራችንና የአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የህብረተሰብ አወቃቀር ከአውሮፓው


የህብረተሰብ አወቃቀር መለየቱ ብቻ ሳይሆን፣ ታሪካቸውም በእነሱ ሊወሰን ችሏል። በዚህም ምክንያት
የተነሳ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች፣ አገራችንንም ጨምሮ አንድ ህብረተሰብ እንደማህበረሰብ ሊኖር
የሚያስችሉትን መሰረታዊ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ነገሮችን ማሟላት አልቻሉም። አብዛኛዎች የአፍሪካ
አገሮች በጥሬ-ሀብትና በእርሻ ምርት በመመካታቸውና፣ ይህንንም ዋናው የገቢ ምንጫቸው
በማድረጋቸው ከሰማንያ በመቶ የሚሆነው ህዝብ አስተማማኝ ገቢ የለውም። ጥቂቶች የተንደላቀቀ ኑሮ
ሲኖሩ አብዛኛው ህዝብ አንድ ሰው ለመኖር ከሚያስችለው የገቢ ገደብ በታች ነው የሚያገኘው።
በየአገሮች ውስጥ የተተከሉት እዚህ ግባ የማይባሉ ኢንዱስትሪዎችና የአገልግሎት መስኮች በጥቂት
ከተማዎች ብቻ የሚገኙ በመሆናቸው አብዛኛው ወጣትና ህዝብ ወደ ከተማዎች በመጉረፍ ከተማዎችን
በማጣበብ ላይ ይገኛል። በዚህም ምክንያት የተነሳ በተለይም በዋና ከተሞች ከፍተኛ መጨናነቅ መኖሩ
ብቻ ሳይሆን፣ ከቤት እጦትና ከመጸዳጃና እንዲሁም ከንጹህ ውሃ ጉድለት የተነሳ አብዛኛው ህዝብ ለበሽታ
የተጋለጠ ነው። ይህ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ አብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮች ከፍተኛ አለመረጋጋት
የሚታዩባቸው ይሆናሉ። መንግስታትም በቀላሉ የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎትና የስራ ዕድልን የማግኘት
ጉዳይ ማሟላት ስለማይችሉ የህዝባቸውን ጥያቄና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ተቃውሞ በአመጽ
ብቻ ሊመልሱ የሚሞክሩበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።

እንደሚታወቀው አብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮችና አገራችንንም ጨምሮ በታሪካቸው ውስጥ የፖለቲካ


ኢኮኖሚክስ፣ የሶስዮሎጂ፣ የሳይንስና የፍልስፍና መሰረት ስሌላቸው የየአገራቸውን ችግሮች ለመቅረፍና
የህዝባቸውን ፍላጎት ለማርካት ፍቱን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲዎች ማውጣት አልቻሉም።
የአለፈውን የሃምሳ ዐመታት የአፍሪካ አገሮችን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ታሪክ በምንመለከትበት ጊዜ አብዛኛዎች
ፖሊሲዎች ከውጭ የመጡ ናቸው። ፖሊሲዎቹ በሙሉ ከየአገሩ ተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሳት የተነደፉ
ባለመሆናቸው ተግባራዊ በሚሆኑበት ጊዜ ፍቱን መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ የባሰውኑ ህብረተሰቦችን
እያዘበራረቁ ናቸው። የችግሩን ዋና ምንጭ ለመጠየቅ የሚቃጣ የተገለጸለት ምሁራዊ እንቅስቃሴና
የሲቪል ማህበረሰብ በየአገሩ ባለመኖሩ ከውጭ የሚመጡ ኤክስፐርቶች፣ በተለይም የዓለም አቀፍ
የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ አማካሪዎች በተደጋጋሚ ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች
ተግባራዊ እንዲሆኑ ስለሚመክሩና ጫና ስለሚያደርጉ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ከውስጥ በሳይንስና
በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ማህበረሰብ ለመገንባት አልቻሉም። የባሰውኑ በውጭ ላይ ጥገኛ
በመሆናቸው የተነሳ ለህዝቦቻቸው አለኝታ ሊሆን የሚችል የኢኮኖሚ አውታር በአገር አቀፍ ደረጃ ሊዘረጉ
አልቻሉም። በተጨማሪም በዕዳ በመተብተብና የወለድ ወለድ በመክፈል ሀብት ወደ ውጭ እንዲፈስ
ከማድረግ በስተቀር የየአገሮቻቸውን ኢኮኖሚ በጠንካራ መሰረት ላይ ሊገነቡ በፍጹም አልቻሉም።
ለአብዛኛዎቹ አገሮች የተትረፈረፈ የጥሬ-ሀብት ለጠንካራ የኢኮኖሚ መገንቢያ መሰርት ከመሆን ይልቅ
በራሱ ችግርን ፈጣሪና ድህነትን አስፋፊ ነው የሆነባቸው።

Videos From Around The World እኛ


በአውሮፓ ለረጅም አመታት የምንኖር ኢትዮጵያውያን ምሁሮች የአገራችንና የሌሎች አፍሪካ አገሮችን
የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከአውሮፓው የህብረተሰብና የኢኮኖሚ አገነባብ ታሪክ ጋር ከአወዳደርን በኋላ
የደረስንበት ድምዳሜ በአገራችንም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ያለው ሁኔታ በዚህ መቀጠል
እንደሌለበት ነው። እንደሚታወቀው እያንዳንዱ ሰው በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረ እንደመሆኑ
መጠን የማሰብና የመፍጠር፣ እንዲሁም የኑሮውን ሁኔታ የመለወጥ ኃይልና ችሎታ አለው። በአጠቃላይ
ሲታይ አንድ ህዝብ በትክክለኛ ፖሊሲ ከተመራና እንዲተባበር ከተደረገ በአገር ውስጥ ባለው ሀብት
ማደግና ጠንካራ አገር መገንባት ይችላል። ጠንካራና የተከበረ አገርን የመገንባቱ ጉዳይ ምንም ወይም
ጥቂት የጥሬ-ሀብት ብቻ ያላቸው እንደ ጃፓን፣ ቻይና፣ደቡብ ኮሪያና ሲንጋፖር የመሳሰሉት አገሮች
አረጋግጠውልናል። ይሁንና ግን አብዛኛዎች የአፍሪካ አገዛዞች የህዝቦቻቸውን ፍላጎትና ህልም
ከማስቀደምና የምሁሮቻቸውን ምክር ከመስማት ይልቅ የዓለም ኮሙኒቲውን ምክር በመስማት
በየጊዜው ወደ አዘቅት እየወረዱና ህዝቦቻቸው አቅመ-ቢስ ሆነው እንዲቀሩ እያደረጉ ነው። ከዚህ ስንነሳ
የአገራችንን አስቸጋሪና አስቀያሚ ሁኔታ ለመለወጥ በእርስዎ የሚመራው መንግስት የግዴታ የኢኮኖሚ
ፖሊሲ ለውጥ ማድረግ አለበት። በአገራችን ውስጥ ህዝብን የሚጠቅምና አገርን በጠንካራ መሰረት ላይ
ለማስገነባት የሚያስችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ቀደም ያለው የአገራችን አገዛዝ
እስከዛሬ ድረስ ተግባራዊ ያደረገውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የግዴታ መመርመር አለብን። ከዚህ ስንነሳ
በእርግጥ ከእርስዎ በፊት የነበረው አገዛዝ እስከዛሬ ድረስ የአብዮታዊ ዲሞክራሲና የልማታዊ መንግስት
የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ወይ ተግባራዊ ያደረገው? የሚለውን ጥያቄ የግዴታ መመለስ ይኖርብናል። ይህ
ግልጽ ሲሆን ብቻ ነው ትክክለኛ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መንደፍ የሚቻለው።

አብዮታዊ ዲሞክራሲ ማለት ምን ማለት ነው ?


በመጀመሪያ አብዮት የሚለውን ፅንሰ-ሃሳብ እንመልከት። አብዛኛውን ጊዜ አብዮት የሚባለው ፅንሰ-
ሃሳብ ከኢንዱስትሪ ዕድገት ጋር ሲያያዝ፣ የኢንዱስትሪ አብዮት በመባል በሁላችንም መንፈስ ውስጥ
ሊቀረጽ ችሏል። ይሁንና በኢኮኖሚክስ የታሪክ ተመራማሪዎች ዕምነት የኢንዱስትሪ አብዮት ከመቅጽበት
የተካሄደ ሳይሆን አንድ ሰው በፈጠረው ቴክኖሎጂ ላይ ሌላው በመቀጠልና በማዳበር ወይም በማስፋፋት
በአንድ ወቅት የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ የታየበት እንደሆነ ይናገራሉ። በተጨማሪም ተሰበጣጥረው
የተለያዩ ምርቶችን ያመርቱ የነበሩ ትናንሽ እንዱስትሪዎች በአንድ አጠቃላይ የአመራረት ስልት
በመደራጀት ወደ ፋብሪካነት የተለወጡበትና፣ ከዚያ በፊት የትናንሽ ኢንዱስትሪዎች ባለቤት የነበረው
ራሱ ወደ ሰራተኛነት የተለወጠበትን ሁኔታ የኢንዱስትሪ አብዮት ብለው ይጠሩታል።

ወደ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ስንመጣም የመጀመሪያው አብዮት የተካሄደው እ.አ በ1640 በእንግሊዝ አገር
ሲሆን፣ ዕድገትን በሚፈልገው በአዲሱ የከበርቴ መደብና የሊበራል አስተሳሰብ ባላቸው ምሁራን በአንድ
በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሰፋፊ መሬቶችንና የመንግስትን መኪና በሚቆጣጠረውና ለውጥን
በማይፈልገው በአሪስቶክራሲው መደብና በንጉሱ መሀከል ነበር። ከ20 ዓመት የርስበርስ ጦርነት በኋላ
የከበርቴው መደብና ሊበራል ኃይሎች በአሸናፊነት በመውጣት ለካፒታሊዝም ዕድገት አመቺ ሁኔታን
ሊፈጥሩ ችለዋል። ሁለተኛው አብዮት ደግሞ እ.አ በ1789 ዓ.ም በፈረንሳይ አገር የተካሄደ ሲሆን፣ ዋና
ዓላማውም ያረጀውንና ዕድገትን የሚቀናቀነውን በንጉስ ሊውስ 16ኛ የሚመራውን ኋላ-ቀር አገዛዝ
አሽቀንጥሮ የጣለ አብዮት ነበር። አብዮቱ አሰቃቂ ቢሆንም ለአዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ በር የከፈተና
ፈረንሳይን ወደ ህብረ-ብሄር እንድታመራ ያደረገ ነው። በሶስተኛ ደረጃ፣ ሰፋ ባለመልክ በኮሙኒስቶችና
በሶሻል ዲሞክራቶች በመመራት በጀርመን ምድር በ1848 የተካሄደው አብዮታዊ እንቅስቃሴ ሲሆን፣ ይህ
አብዮታዊ እንቅስቃሴ ብዙ የአውሮፓ አገሮችን ያዳረሰ ነበር። በወቅቱ የወዝአደሩ መደብ ቀስ በቀስ
እየተደራጀና ለመብቱ መታገል እንዳለበት የተገለጸለት ነበር። ይህም ሊሆን የቻለው በጊዜው የወዝአደሩ
መደብ በቀን ከአስራ ሁለት ሰዓት በላይ ይሰራ ስለነበረና፣ የህፃናትም ስራ የተስፋፋ ስለነበር ወዝአደሩ
የግዴታ የስራ ሰዓት እንዲቀነስ ብቻ ሳይሆን ለዲሞክራሲያዊ መብቶች በመታገል የራሱን አገዛዝ
ለመትከል የሚንቀሳቀስበት ዘመን ነበር። በተለይም እንደጀርመን የመሳሰሉት አገሮች በአምባገነናዊ
የሞናርኪስቶች አገዛዝ የተነሳ የዲሞክራሲ ነፃነቶች የታፈኑበት ዘመን ስለነበርና፣ ከፍተኛም ብዝበዛ
በመካሄዱ ይህንን ለመግታት ሲባል የግዴታ ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ ሊካሄድ ቻለ። ይሁንና ግን እንቅስቃሴው
ሊከሽፍ ሲችል፣ እነቢስማርክ የማህበራዊ መሻሻል ህጎችን በማውጣት በኮሙኒስቶችና በሶሻል
ዲሞክራቶች የሚመራውን እንቅሳቅሴ ሊያኮላሹት ችለዋል። በቢስማርክም የማህበራዊ ፖሊሲ
አማካይነት አጠቃላይ የህክምና ኢንሹራንስ፣ የጡረታ አበልና ሌሎች የማህበራዊ ፖሊሲዎች ተግባራዊ
በመሆን ወዝአደሩ የዕድገት ተካፋይ ሊሆን በቅቷል። በፖሊሲው መሰረትም የኢንዱስትሪና የንግድ
ባለሀብቶች በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ የሰራተኛው መደብ እኩል በማዋጣት የማህበራዊ
መስኩን እንዲደጉሙ ተደርገዋል። ይህ ዐይነቱ የቢስማርክ የማህበራዊ ፖሊሲ እስከዛሬ ድረስ የሚሰራበት
ነው።

በአራተኛ ደረጃ፣ እ.አ በ1917 ዓ.ም በራሺያ ምድር የተካሄደው አብዮት ነው። የራሺያ አብዮት እነሌኒን
በሚመሩት በቦልሺቢኪ ፓርቲ የተካሄደና ግቡንም የመታ ሲሆን፣ ከራሺያ አልፎ ዓለም አቀፋዊ
ተፅዕኖም ነበረው። ለአብዮቱም ዋና ምክንያት የዛር መንግስት እስከዚያ ጊዜ ድረስ አስፈላጊውን የጥገና
ለውጦች ለማካሄድ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነው። ንጉሱና ቤተሰቦቹ በተደንላቀቀ ሁኔታ ሲኖሩ፣ ሰፊው የራሺያ
ህዝብ ደግሞ በድህነትና በረሃብ ዓለም ውስጥ የሚኖር ነበር። ይህ ሁኔታና፣ በተለይም ደግሞ ከ1914-
1918 ዓ.ም የጀርመን ወራሪዎች በራሺያ ላይ በከፈቱት የመጀመሪያው ዓለም ጦርነት አገዛዙ ተዳክሞ
ስለነበር እነሌኒን ይህንን ተጠቅመው በ1917 ዓ.ም የጥቅምትን አብዮት አወጁ። በዚህም የተነሳ የጦርነት
ኮሙኒዝም የሚባለውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማወጅ በጦርነቱ ምክንያት የደቀቀውን ኢኮኖሚ
እንዲያገግም ለማድረግ አስፈላጊ እርምጃዎች ተወሰዱ። በግል ይዞታ ስር የሚገኙ የንግድ
እንቅስቃሴዎችንና ኢንዱስትሪዎችን በመንግስት ቁጥጥር ስር በማዋል፣ በተለይም የእርሻው ዘርፍ
ተጨማሪ ምርት(Surplus Product) ያመርት ዘንድ አስፈላጊው እርምጃዎች ተወሰዱ። ይሁንና ይህ ፖሊሲ
እንደተጠበቀው ውጤታማ ባለመሆኑ፣ እነ ሌኒን ይህንን የጦርነት ኢኮኖሚ ፖሊሲ በአዲስ የኢኮኖሚ
ፖሊሲ በመተካት የገበያ ኢኮኖሚ ሊስፋፋና ሊዳብር የሚችልበትን ሁኔታ አመቻቹ። በአዲሱ የኢኮኖሚ
ፖሊሲ መሰረትም(New Economic Policy)፥ ትናንሽ የንግድ መደብሮችና(Retail Trade)፣ ትናንሽና
ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች በግል ይዞታ ስር እንዲውሉ ሲደረግ፣ ባንኮች፣ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች፣
የውጭው ንግድ፣ የመንገድና የመገናኛ መመላለሻዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲቀሩ ተደረገ።
አብዮቱ እስከፈነዳና እነዚህ ፖሊሲዎች ተግባራዊ እስከተደረጉ ድረስ አብዛኛው የራሺያ ግዛትና ህዝብ
በኢኮኖሚም ሆነ በሌሎች ነገሮች ከሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ጋር ሲወዳደር እጅግ ወደ ኋላ የቀረ
ነበር። ለዚህም ነው እነ ሌኒን ይህንን ኋላ-ቀርነት በመገንዘብ በራሺያ ምድር ሁለ-ገብ የሆነ
መብራት(Electrification) መግባት ወይም መስፋፋት እንዳለበትና፣ ይህም ለኢንዱስትሪ መስፋፋትና
ማደግ የመጀመሪያው ቅድመ-ሁኔታ እንደሆነ ያወጁት።

አሁንም ቢሆን ይህ ፖሊሲ በተለይም በእርሻው መስክ የተጠበቀውን ውጤት ባለማምጣቱ እነስታሊን
በ1928 ዓ.ም በግዴታ ላይ የተመሰረተ የህብረት እርሻ ፕርግራም(Collectivization) በማስፋፋት
በተለይም የከተማውን ህዝብ ለመመገብ ጥረት አደረጉ። በዚህ ዐይነቱ የግዳጅ የህብረት ፖሊሲ
አማካይነት በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ቢሞትም፣ በተለይም ከ1930ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ
ሶቭየትህብረት በኢንዱስትሪ አብዮት የመረቃ ውጤት በማስገኘትና ከተማዎችን በመገንባት አነሰም
በዛም ወደፊት ልትራመድ ችላለች። የምዕራቡ ዓለም የሶቭየትህብረትን ሁለ-ገብ ዕድገት ለመቀልበስ ሲል
በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰላዮችን በማሰማራቱ ይህ ሁኔታ በስታሊንና በተቀሩት የቦልሺቢኪ መሪዎች
መሀከል መጠራጠርንና መጠላላትን አስከተለ። በተለይም እነ ቡሃሪን የመሳሰሉ የኢኮኖሚክስ ምሁራን
ለቀቅ ያለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመፈለጋቸውና ለዚህም በመከራክራቸው ስታሊን ይህንን ዐይነቱን
አመለካከት አብዮቱን እንደመቀልበስ አድርጎ በመመልከቱ ቁጥራቸው የማይታወቁ ምሁራንን ጨረሰ።

ሶቭየትህብረት በኢኮኖሚም ሆነ በሌሎች መስኮች፣ ማለትም በባህልና በከተማዎች ግንባታ ወደፊት


ልትገፋ የቻለችው የእነ ሂትለርን ጦር ድል ካደረገችና ሁለ-ገብ የአገር ግንባታ ፖሊሲ ማካሄድ ከጀመረች
ወዲህ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ ስንነሳ በሶቭየትህብረትም ሆነ በተቀሩት ተቀጥያ የምስራቅ አውሮፓ
አገሮች በአብዮትና በሶሻሊዝም ስም የተካሄደው የግንባታ ፖሊሲ የኢኮኖሚክስ የታሪክ ተመራማሪዎች
እንደሚሉት ከኋላ የመያዝ(Catching-Up Strategy) የኢንዱስትሪ ተከላ እንቅስቃሴ እንደሆነ ይናገራሉ።
ይህ ዐይነቱም ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ ሰፊውን ህዝብ ያሳተፈ ሲሆን፣ ቀስ በቀስም ከድህነትና ከረሃብ
እንዳላቀቀው የተረጋገጠ ነገር ነው። ስለሆነም በተለይም ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ በአብዛኛዎቹ የሶሻሊስት
አገሮች ሰፊው ህዝብ የመማር ዕድል ያገኘበት፣ የጤና መስክ የተስፋፋበት፣ ከተማዎች የተገነቡበትና
ህዝቡም በንጹህ ቤት ውስጥ እንዲኖር የተደረገበት፣ የስራ መስክ የተረጋገጠበትና ህዝቡም ተከታታይ
ገቢ እንዲያገኝ የተደረገበት ዘመን እንደነበር ይታወቃል። ይህ ዐይነቱ የሁለ-ገብ ዕድገት እንቅስቃሴ ደግሞ
በጊዜው የታሪክ ግዴታ ነበር ማለት ይቻላል። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ
የመንግስት ቁጥጥር ያለበትና በዕቅድ ይካሄድ የነበረ በመሆኑ ለፈጠራ የሚያመች አልነበረም። ከዚህም
በላይ አብዛኛዎቹ የሶሻሊስት አገሮች ልክ እንደ ምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮችና አሜሪካ በዓለም
አቀፍ ደረጃ ጥሬ-ሀብትን የሚቀራመቱ ወይም የሚበዘብዙ ስላልነበሩ ወደ ውስጥ ለዕድገት
የሚያመቻቸውን የገንዘብም ሆነ የጥሬ-ሀብት እንደልብ ማግኘት አልቻሉም። በዚህም ምክንያት የተነሳ
ከሰባና ከሃምሳ ዐመት የሶሻሊስት ኢኮኖሚ ግንባታ ሙከራ በኋላ ወደፊት ሊገፉ አልቻሉም።

በአጠቃላይ ሲታይ የኢኮኖሚ ዕድገትን ታሪክ ስንመረምር በአውሮፓ ምድር ውስጥም ካፒታሊዝም ቀስ
በቀስ ተግባራዊ ሊሆንና የበላይነትን ሊቀዳጅ የቻለው ሰፊውን ህዝብ በማንቀሳቀስና በስራ ላይ
እንዲሰማራ በማድረግ ከብዙ ጊዜ የሙከራና የልምድ(Trial and Error) ግንባታ በኋላ እንደሆነ ጥናቶች
ያረጋግጣሉ። የካፒታሊስት አገሮች በንጹህ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ብቻ ነው ሊያድጉ ወይም
እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት የሚለው የተረት ወሬ ነው። ከዚህ በመነሳት በአ. አ እስከ ሚያዚያ 2018
ወር ድረስ በህወሃት ግንባር ቀደምትነት ስልጣንን የያዘው የኢሃዴግን አገዛዝ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ
ፖለቲካና የመንግስት ልማታዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲን ውስጣዊ ይዘትና ተግባራዊነቱን እንመርምር።

የቀደመው አገዛዝ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ምንነት !


የቀድሞው የኢሃዴግ አገዛዝ ስልጣንን ከመንጠቁ በፊት እ.አ በ1974 ዓ.ም የታሪክና የህብረተሰብ ግዴታ
ሆኖ ደርግ ስልጣንን ከያዘ በኋላ የመሬት ላራሹ ታውጇል፤ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች፣ ባንኮችና
የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ ተደርገዋል። እንደሚታወቀው አብዮቱ
ከመፈንዳቱ በፊት ከ500 000 በላይ የሚሆን ህዝብ በረሃብ ህይወቱን እንዳጣና፣ ከሰማንያ በመቶ በላይ
የሚሆነውም ህዝባችን ደግሞ በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲኖር የተገደደ ነበር። አብዛኛው ህዝብ በጎጆ
ቤት ውስጥ ሲኖር፣ ለብርድ፣ ለዝናብና ለአውሬ የተጋለጠ ነበር። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ተግባራዊ
የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከ5% በታች የሆነውን ህዝብ የጠቀመ ሲሆን፣ ይህ ዐይነቱ የዘመናዊነት ፖሊሲ
በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተማዎች ጎልቶ ሲታይ፣ እዚያው በዚያው ደግሞ ድህነትና በሀብት መደለብ
ተፋጠው የሚታዩበት ዘመን ነበር። በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተማዎች መሀከል ዘመናዊ ዕድገት
የሚመስል ነገር ቢታይም፣ በጊዜው የነበረውን አጠቃላዩን የኢኮኖሚ አወቃቀር በምንመረምርበት ጊዜ
በአገራችን ውስጥ ያልተስተካከለና ድህነትን የሚፈለፍል ኢኮኖሚ መሰል እንቅስቃሴ እዚህና እዚያ ይታይ
ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳ አብዛኛው ተማሪ አስራሁለተኛን ክፍል ሲጨርስ የስራ ዕድል ለማግኘት
ሲል ወደ አዲስአበባ የሚመጣ እንጂ እዚያው የተወለደበት፣ ያደገበትና የተማረበት ቦታ ስራ ማግኘት
አይችልም ነበር። ሁለ-ገብ የሆነ የሙያ ማሰልጠኛ መማሪያ ትምህርትቤት በየክፍለ ሀገሩ ዋና ከተማዎችና
አውራጃዎች ባለመኖሩ፣ በተለይም ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የማይችለው አብዛኛው ወጣት ዝም ብሎ
የሚንቀዋለል ነበር። ከዚህም ባሻገር በአብዛኛዎቹ የክፍለ-ሀገራት ከተማዎችና ወረዳዎች፣ እንዲሁም
የምክትል ወረዳዎች ኋላ-ቀር የሆኑ የአገዛዝ መዋቅሮች በመዘርጋታቸው፣ መስሪያቤቶቹ ባልተማሩ ሰዎች
ይተዳደሩ የነበሩ ናቸው። በየክፍለ-ሀገራቱ የሚገኙት የአስተዳደር መስሪያቤቶች በየአካባቢው
የሚገኘውን የሰውን ኃይልና የተፈጥሮን ሀብት ለማንቀሳቀስና ዕድገትን ለማምጣት የሚችሉ
አልነበሩም። ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች በየቦታው መተከል እንዳለባቸው የተገነዘቡ
ባለመሆናቸው የጥሬ-ሀብትና የሰው ኃይል በቀላሉ ይባክን ነበር። ስለሆነም በወቅቱ አብዮቱ መፈንዳቱ
የሚያስገርም አይደለም። ይሁንና ይህ አብዮት በአንድ በኩል በውስጣዊ የአደረጃጀት ድክመትና የሃሳብ
አንድነትና (Lack of Unity of Thought) የርዕይ ጥራት አለመኖር፣ በሌላ ወገን ደግሞ አብዮቱን
የሚቀናቀኑና ለውጥን የሚጠሉ የውስጥ ኃይሎች ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበርና በመተባበር ርብርቦሽ
በማድረጋቸው የተፈለገው ለውጥ ሊመጣ አልቻለም። ትግሉ ዕድገትንና ለውጥን ለማምጣት የሚደረግ
ከመሆን ይልቅ ስልጣንን ለመያዝ ከፍተኛ አትኩሮ ስለተሰጠው የመጨረሻ መጨረሻ ወደ ርስበርስ
መተላለቅ አመራ። በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ወጣትና ምሁራዊ ኃይል ህይወቱን እንዲያጣ ተደረገ።

ይህንን ዐይነቱን በቀላሉ ለመግለጽ የሚያስቸግረውን አብዮታዊ ሂደትና የዕድገት ሙከራ ነው የውጭና
የውስጥ ኃይሎች ከሶሻሊዝም ጋር በማያያዝ ዘመቻ ማካሄድ የጀመሩት። ለውጡን የማይፈልጉ የውስጥ
ኃይሎች በኢምፔሪያሊስት ኃይሎች በመደገፍ የአብዮቱን ውጤቶች ለመቀልበስና ስልጣንም የህዝብ እጅ
ውስጥ እንዳይገባ ያላደረጉት ጥረት ይህ ነው አይባልም። ደርግ ከወደቀ በኋላ ስልጣንን የተረከበው አገዛዝ
ዋናው ተግባሩም የአብዮቱን ድሎች አይ መቀልበስ ወይም በራሱ ስር በማጠቃለል ራሱን ማደለብ ነበር።
የአብዮቱን ድሎች ለመቀልበስ ደግሞ የግዴታ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና (IMF) በዓለም
ባንክ(World Bank) የተጠናቀረ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማካሄድ ነበረበት። ደርግ ሲወድቅ ስልጣኑን
የተረከበው አገዛዝ ከቀረቡለት ቅድመ-ሁኔታዎች አንዱ ይህንን የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው በማቆላበጥ
የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እያለ የሚጠራውን ተግባራዊ ማድረግ ነበር። በፖሊሲው መሰረትም በመንግስት
ቁጥጥር ስር የነበሩትን ኢንዱስትሪዎች፣ ትላልቅ የንግድ መደብሮች፣ ባንኮችንና የኢንሹራንስ
ኩባንያዎችን ወደ „ግል ሀብትነት“ መለወጥ ነበር። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ በመንግስት ቁጥጥር ስር
የነበሩትን የህዝብ ሀብቶች ወደ ግል ሀብትነት ማዘዋወር እዚያው በዚያው የተካሄደና ጥቂት ግለሰቦች
ገንዘብ ከባንክ በመበደር የተቀራመቱትና የገዙት ነው። ከዚህ ውስጥ አብዛኛውን ድርሻ የሚይዘው
በጊዜው የነበረው ኢፈርት የሚባለው ትልቁ ኩባንያ ነው።

ከዚህ አልፎ በዚህ ዐይነቱ የፀረ-አብዮት ፖሊሲ እርምጃዎች አማካይነት የአገራችን ብር ከዶላር ጋር
ሲወዳደር ዝቅ እንዲል (Devaluation) ይደረጋል። የውጭው ንግድ ልቅ ይሆናል። ወደ ውስጥ ደግሞ
በዋጋዎች ላይ ይደረግ የነበረው ቁጥጥር ይነሳል። በተጨማሪም ለማህበራዊ መስኮች ይመደብ የነበረው
ባጀት ወደ ሌላ ይዛወራል። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ በመባል
ሲታወቅ፣ ዋና አላማውም የገበያን ኢኮኖሚ ተግባራዊ ለማድረግ ነው የሚል ነበር።

ከ1980 ዓመታት ጀምሮ ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ በብዙ የአፍሪካ አገሮች፣ በተለይም
በጋናና ናይጄሪያ ተግባራዊ ቢሆንም ወደ ውስጥ ሰፋ ያለና ግልጽ የሆነ የገበያ ኢኮኖሚ እንዲገነባ
አላስቻለም። በእነዚህ አገሮችና በኢትዮጵያም ጭምር በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪ ተከላና
ሰፋ ያለ የስራ-ክፍፍል ሊካሄድና ሊዳብር አልቻለም። ከተማዎችና መንደሮችም በዕቅድ ሊሰሩና
የተተከሉትም ኢንዱስትሪዎች ሰፋ ያለ የስራ መስክ ሊከፍቱና አስተማማኝ ገቢ ሊያስገቡ በፍጹም
አልቻሉም። ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች እዚህና እዚያ በመተከል ለገበያ ኢኮኖሚ መስፋፋት
መሰረት ሊጥሉ አልቻሉም። ይልቁንስ ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለአገልግሎት መስኩ መስፋፋት ነው
በር የከፈተው። ስለሆነም ይህንን የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ያደረጉ ኢትዮጵያና አንዳንድ
የአፍሪካ አገሮች ገንዘባቸው ከዶላር ጋር ሲወዳደር ዝቅ በመደረጉ፣ በአንድ በኩል ከውስጥ ግሽበትን
ሲያስፋፋ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የንግድ ሚዛናቸው ወደታች በማሽቆልቆል ችግር ውስጥ ገብተዋል። የንግድ
ሚዛንን መዛባትና የባጀት ክፍተትን ለሟሟላት ደግሞ የግዴታ ከዓለም አቀፋዊ ኢንስቲቱሽኖች ብድር
መጠየቅ ነበረባቸው። ኢትዮጵያና የተቀሩት የኒዎ-ሊበራልን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ያደረጉ አገሮች
በሙሉ የዕዳ ወጥመድ ውስጥ በመግባት በቀላሉ ሊፈቱ የማይችሉትን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውስ
ማምረት ችለዋል። ይህም ማለት በዓለም የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ ግፊት ተግባራዊ የሆነው
የገበያ ኢኮኖሚ እነዚህን አገሮች ስርዓት ወዳለውና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ወደ ተመሰረተ ሁለ-ገብ
የኢኮኖሚ አወቃቀር እንዲያመሩ አላደረጋቸውም። በተከታታይ ተግባራዊ በሆነው ገንዘብን ዝቅ
የማድረግ ፖሊሲ ምክንያት የተነሳ በተለይም የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ $ 17 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ
የንግድ ሚዛን መዛባት ሲደርስበት፣ የውጭ ዕዳዋ ደግሞ ወደ $ 30 ቢሊዮን ወይም ከዚያ በላይ እንደሆነ
ይታወቃል። የውጭው ዕዳው አገሪቱ በዓመት ከምታመርተው ጠቅላላ ምርት $ 80.5 ቢሊዮን ውስጥ
38% የሚሆነውን ይይዛል። በሌላ አነጋገር፣ በተደጋጋሚ ተግባራዊ የሆነው የፀረ-አብዮታዊ ዲሞክራሲ
የኢኮኖሚ ፖሊሲ አገራችንን የባሰውኑ እያራቆታት ነው ማለት ነው። በዚያው መጠንም የተወሰነው
የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ሲሆን፣ በደሃና በሃብታም መሀከል ያለው ልዩነት እየሰፋ እንደመጣ
መገንዘብ እንችላለን። ይህ ሁሉ የሚያረጋግጠው አገዛዙ እስካሁን ድረስ ይከተል የነበረው የኢኮኖሚ
ፖሊሲ ሳይንሳዊ ባህርይ ያለውና ችግርን ፈቺና አገርን መገንቢያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሳይሆን፣ አገርን
አውዳሚና ህብርተሰብን-የሚያዘበራርቀውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ማለት ነው።

ከዚህ ስንነሳ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሰረታዊ የሆኑ የህዝብ ፍላጎቶችን ያሟላና
ሊያሟላም የሚችል አይደለም። እንደትላንትናው ዛሬም ከ27 ዓመት በኋላ አብዛኛው ህዝባችን ንፁህ
ውሃ የመጠጣትና የማግኘት ዕድል የለውም። በወዳደቁ ቤቶችና ጎጆ ቤቶች ውስጥ ነው የሚኖረው።
ትምህርትቤቶች የፈራረሱ ናቸው። ህክምና እንደልብ አይገኝም። አብዛኛዎቹ ከተማዎችና መንደሮች
የሰው ልጅ የሚኖርባቸው አይደሉም፤ አይመስሉምም። ሁሉም ከተማዎች በዕቅድ ከረጅም ጊዜ አንፃር
ተብለው የታቀዱና የተገነቡ አይደሉም። የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲው የሰውን ጤንነት ያቃወሰና
የሰውም ኃይል አዲስ ዕውቀት በመገብየት ህብረተሰብአዊ ሀብት እንዳይፈጠር መሰናክል የሆነ ነው።
በመሰረቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲውና ፖለቲካው አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚያሰኘው ሳይሆን ፀረ-አብዮታዊና
ፀረ-ዲሞክራሲ ነው። አብዮታዊነቱ ለጥቂት ሰዎች የመጣ ነው ማለት ይቻላል። ህዝባዊ ባህርይ የሌለውና
ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ ያስቻለ አይደለም። ጥቂቶች በጉልበት የነጠቁትን ሀብትና የተቀዳጁትን
ኃይል በመጠቀም ከፍተኛ ዘረፋ በማካሄድ ሊደልቡ የቻሉበት ሁኔታ ነው በጉልህ የሚታየው። ስለሆነም
ይህ ዐይነቱ አብዮት ለጥቂቶች ብቻ የተካሄደ እንጂ ለኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም። በጎሳ የበላይነት ላይ
የተመሰረተ የዚያው በዚያው የሀብት ሽግሽግና በሀብት መደለብ የተካሄደብትን ሁኔታ ነው አብዮታዊ
ዲሞክራሲ እየተባለ በመጠራት ትልቅ ወንጀል የተሰራውና የተፈጸመው።

የኒዎ-ሊበራል የገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ 27 ዐመታት ሲጠጋው በዚህ ዘመን
በአገራችን ምድር ከፍተኛ የሆነ የባህል ውድመት ሊከሰትና የህብረተሰብአችንን እሴትና ባህል
ሊበጣጥሰው ችሏል። ወጣት ሴት ልጆች በለጋ ዕድሜያቸው መሸት ሲል መንገድ ላይ በመቆም ለሴተኛ
አዳሪነት እንዲጋለጡ ተደርገዋል። ቀደም ብሎ በትንሽ የሚታወቅ ወይንም ደግሞ ምንም ነገር የማይሰማ
በወንዶች መሀከል የሚፈጸም የወሲብ ስራ በመስፋፋት የጠቅላላውን ህዝባችንን እሴት አናግቶታል።
በተለይም በዕርዳታ ስም የገቡ የውጭ አገር ሰዎችና ለንግድ የሚመላለሱ አረቦች የአገራችንን ህዝብ ደሃ
መሆን በመጠቀም ብልግና እንዲስፋፋ ለማድረግ በቅተዋል። ይህ ሁሉ ይደረግ የነበረውና የሚደረገው
በመንግስት ዕውቀት ነው። ስለሆነም ባለፉት 27 ዓመታት የአባለ-ዘር በሽታና የኤይድስ ቫይረስ
በመስፋፋት ህዝባችንን አቅመ-ቢስና በሽተኛ አድርገውታል። ከዚህ በተጨማሪ የዕጽ ማጨስና የጨአት
መቃም በመስፋፋታቸው ወጣቱ ትውልድ ሱሰኛ እንዲሆን ተደርጓል። ገበያው በሊበራልዚም ስም
ለውጭ ኃይሎች ክፍት በመሆኑ የውጭ ኃይሎች በወጣቱና በአገራችን ላይ የዕጽ ጦርነት(Opium War)
ሊከፍቱ ችለዋል። የአገር እሴትና ባህል ሲፈራርስ ለመዋጋትና ለማጋለጥ የሚችል የሲቪል ማህበረሰብ
እንቅስቃሴ ባለመኖሩና፣ ተማርኩ የሚለውም ነገሩን ዝም ብሎ ስለሚመለከት አገራችንና ህዝባችን
ወዴት አቅጣጫ እንደሚጓዙ የማያውቁበት ደራጃ ላይ ደርሰዋል። እንደሚታቀው ስለ አገር አንድነትና
ዕድገት በሚወራበት ጊዜ ይህንን አደገኛ የእሴት መበጣጠስ ከቁጥር ውስጥ በማስገባት የአገራችንን
ሁኔታ ለመመርመር የማንችል ከሆነ ስለአገርና ባንዲራ ዝም ብለን ነው የምናወራው ማለት ነው። ሞራሉ
የተከሰከስና በዕጽ ናላው እንዲዞር የተደረገ ወጣት ኃይል ሊያስብና ሊፈጥር ስለማይችል ይህንን ሁኔታ
ዝም ብሎ ማየት የድርጊቱ ተባባሪ እንደመሆን ይቆጠራል። ከዚህ በተረፈ ወላጆች ሊረዷቸው የማይችሉ
በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች በየበረንዳው ተጥለውና ምግብ ከቆሻሻ መከማቻ ቦታ እየፈለጉ እንዲበሉ
እንደተደረጉ እንመለከታለን። ከዚህም ባሻገር አጠቃላዩ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከሳይንስና
ከፍልስፍና አንፃር ያልታቀደ በመሆኑ አገራችን የቆሻሻ መከማቻ ልትሆን በቅታለች። ከአውሮፓና ከሌሎች
አገሮች የሚመጡ የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎች፣ ያረጁ መኪናዎችና የፕላስቲክ ከረጢቶች በየቦታው
ተበትነውና ተከማችተው በመገኘት ለጤንነት መቃወስ ምክንያት ሊሆኑ ችለዋል። ስለሆነም ከዚህ ቀደም
የማይታወቁ በሽታዎች በአገራችን ምድር በመስፋፋት በተለይም ወጣቱ ትውልድ የልዩ ልዩ ዐይነት
በሽታዎች ሰለባ ሊሆን በቅቷል። ይህ ሁሉ ከላይ የተዘረዘረው ነገር የሆነውና የሚሆነው በመንግስት
የሚደገፍ የልማት ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ተደርጓል በሚባልበት አገርና፣ የኢኮኖሚው ዕድገትም
በ10%ና ከዚያ በላይ አድጓል በሚባልበት አገር ወስጥ ነው።

ይህንን ትተን ወደ ሌላ ጉዳይም ስንመጣም የአገራችን ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ እናያለን። ባለፉት
ሃያ ዐመታት በመንግስት ስር የሚተዳደር ቢሮ በመክፈት ወጣት ሴት ልጆቻችን ወደ አረብ አገሮች
እንዲሸጡና ገረድ እንዲሆኑ ተደርገዋል። ሰሞኑን የመንግስት ተወካዮች ይህንን የሴት ልጆችን ሽያጭ
አስመልክቶ ከመንግስት ውጭ በጥቁር ገበያ በመሰማራት ወደ አረብ አገሮች የሚልኩ የተደራጁ ኃይሎች
እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል። የመንግስቱን ተወካዮች ገለፃ፤ለሰማ ይህንን ተግባር ሊፈጽም የሚችለው
መንግስት ብቻ እንደሆነ አረጋግጠውልናል። የሚነሳስው ጥያቄ፣ ለመሆኑ በአገሪቱ ህገ-መንግስት ውስጥ
መንግስት ከውጭ አገሮች ጋር በመስማማት ሴት ልጆችን ለመሸጥ ወይም ለመላክ የሚችል አንቀጽ አለ
ወይ ? ቢኖርስ እንኳ አንድ ህዝብን እወክላለሁና አስተዳድራለሁ የሚል መንግስት ክውጭ መንግስታት
ጋር በመስማማት ወጣት ሴት ልጆችን በግርድና የመላክ ተፈጥሮአዊ መብት አለው ወይ? ያም ሆነ ይህ
ገንዘብ ለማኘትና ቤተሰብን ለመርዳት በሚል ሰበብ በታዳጊ ትውልድ ላይ እንደዚህ ዐይነት ወንጀል
መፈጸም ከታሪክ ተጠያቂነት የሚያድን አይሆንም። ስለሆነም በአረብ አገሮች ተሰማርተው በግርድና
የሚሰሩ ልጆቻችን ጥቂት የማይባሉት ህይወታቸውን እንዲያጡ ሲደረግ፣ ሌሎች ደግሞ በመደብድብ
አካለ ስንኩላን ለመሆን በቅተዋል። የሶስት ሺህ ዐመት ታሪክ አለን የምንል ህዝብና በባንዲራችን
የምንኮራ አንድ አገዛዝ ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበር እንደዚህ ዐይነቱን የመሰለ የታሪክ ወንጀል ሲፈጽም
ዝም ብሎ ማየት አሁንም ቢሆን ከተጠያቂነት ሊያድነን በፍጹም አይችልም። ኢትዮጵያኖች ብቻ
በመሆናችን ሳይሆን ነፃ ፈላጊና ለመብት ተቆርቋሪ እስከሆን ድረስ እንደዚህ ዐይነት ወንጀል ሲፈጸም ዝም
ብሎ መመልከት በቀጥታ በአገራችን ላይ እንደመዝመት ይቆጠራል።

በአጠቃላይ ሲታይ በአገራችን ምድር በመንግስት የሚደገፍ ጠቅላላውን ህዝብ የሚጠቅም ሁለ-ገብ
ልማት ተግባራዊ በመሆን ላይ ነው እየተባለ ባለማወቅ ዝም ብሎ የሚናፈሰው ፅንሰ-ሃሳብ በተለይም
ታዳጊውን ወጣት በማሳሳት ላይ ይገኛሉ። በአገራችን ምድር አብዮታዊ ዲሞክራሲና በመንግስት
የሚደገፍ ልማት ሲካሄድ ታይቶ አይታወቅም። ይህንን ሁሉ ትተን በአገዛዙ ዘንድ ያለውን የዲሞክራሲ
ባህላዊ ውይይት ጉዳይ በምንመረምርበት ጊዜ በኢህአዴግ አገዛዝ ውስጥ የፖሊሲ ክርክር ሲካሄድ
ሰምተን አናውቅም። በመሀከላቸውም የሀብት ዘረፋንና መደለብን አስመልክቶ ክርክርና ውይይት
ተካሂዶ አያውቅም። ዕድገትም በዚህ መልክ ነው የሚገለጸው ? ብለው ጠይቀውና ተከራክረው በፍጹም
አያውቁም። ከዐመት ዐመት የገንዘብ ቅነሳ ፖሊሲ በማካሄድና የፕላንቴሽን ኢኮኖሚ በማስፋፋት አገሪቱን
ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከተዋታል። የአገራችንን ትላልቅ የእርሻ መሬቶች አበባና ሸንኮራ አገዳ
እንዲተከልባቸው በማድረግ የካፒታሊስት አገሮችን የባሰ በሀብት ክምችት እንዲደልቡ እያገዙ
ነው። በአንፃሩ ግን ሶቭየትህብረት በሌኒንም ሆነ በስታሊን ጊዜ፣ እንደዚሁም በቻይና የአብዮት ወቅት
በእነ ማኦሴቱንግና በዴንግ ሲያዎፒንግ መሀከል የኢኮኖሚ ፖሊሲንም አስመልክቶ የጦፈ ክርክር ይካሄድ
ነበር። አብዮትን ያካሄዱና አብዮታዊ ዲሞክራሲን ተግባራዊ ያደረጉ እነዚህ አገሮችና ሌሎች የምስራቅ
አውሮፓ አገሮች የአገሮቻቸውን የእርሻ መሬቶች ወደ ፕላንቴሽን ኢኮኖሚ በፍጹም አለወጡም።
ስለሆነም የድሮውን አገዛዝ የዲሞክራሲያዊ አብዮታዊ መንግስት እያልን ከመጥራት ይልቅ በምዕራቡ
ዓለም የሚደገፍ ፀረ-ዲሞክራሲና ፀረ-ዕድገት አገዛዝ እያልን ብንጠራው ለትግል የሚያመች ይሆናል።
ከተጨባጩ ሁኔታ ጋር የማይስማማ ፅንሰ-ሃሳብ የምንጠቀምና የምናራግብ ከሆነ የችግሩን ምንጭ
በሚገባ ልንረዳ አንችልም ማለት ነው። ዋናውን ችግር ካልተረዳን ደግሞ ፍቱን የሆነ መፍትሄ ማቅረብ
አንችልም። ስለሆነም ስለአንድ ህብረተሰብ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀውስ በምናወራበት ጊዜ መሰረታዊ
ችግሩን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። ይህንንም በቲዎሪ በሚገባ መተንተን አለብን፤ ምክንያቱም
ካለቲዎሪ ድርጊት ወይም ተግባር ሊኖር አይችልምና።

የልማታዊ መንግስት ይዘት !


በኢኮኖሚክስ ሊትሬቸር ውስጥ ልማታዊ መንግስት(Developmental State) በመባል የሚታወቁት
ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ሲንጋፖርና ታይዋን ናቸው። ይህ ዐይነቱ የልማታዊ መንግስት የኢኮኖሚ ፖሊሲ
ዋና ዓላማው በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ የውስጥ ገበያን ማስፋፋት ሲሆን፣ ከዚህም ባሻገር ለውጭ
ከረንሲ ማግኚያ በማለት ስትራቴጂክ በሆኑ መዋዕለ-ነዋዮች ላይ መረባረብ ነበር። በተለይም የጃፓንና
የደቡብ ኮሪያ አገዛዞች በመንግስት፣ በትላልቅ ኢንዱስትሪዎችና በባንኮች መሀከል መደጋገፍ እንዲኖር
በማድረግ፣ ከውስጥ የኢኮኖሚውን ዕድገት በማፋጠን ቀስ በቀስ ደግሞ በኤሌክትሮኒክስ፣ በመኪናና
በብረታ ብረት ምርቶች መንጠቀው በመሄድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነትና ከጥገኝነት በመላቀቅ ወደ
ውጭ ደግሞ ሊከበሩ በቅተዋል። የመንግስትም ሚና ጥቂት ሰዎችን ማደለብ ሳይሆን ከውስጥ
የተሰተካከለ ዕድገትን በማምጣት ኢኮኖሚው ብሄራዊ ባህርይ እንዲኖረው ማድረግና በጠንካራ መሰረት
ላይ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ነው። ስለሆነም ለዚህ ዐይነቱ በመንግስት የተደገፈ ሁለ-ገብ ዕድገት ሳይንስና
ቴክኖሎጂ ቁልፍ ቦታ ሲኖራቸው፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገት ደግሞ ሁለ-ገብ በሆነ ልዩ ዕውቀት
የተደገፈ ነው።

በእነዚህ አገሮች ውስጥ ተግባራዊ የሆነው በመንግስት የተደገፈ የልማት ፖሊሲ የኒዎ-ሊበራልን የኢኮኖሚ
ፖሊሲ የሚቃወምና፣ መንግስታቱም አንድም ጊዜ ይህንን ዐይነቱን ሀብት አውዳሚና በዕዳ ተብታቢ
የሆነውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲያደርጉ አልታየም። በተጨማሪም የውጭ
ንግዳቸውን በመቆጣጠር ኢንዱስትሪዎቻቸው እንዲያድጉ የዕገዳ ፖሊሲ(Protectionism) ያካሂዱ ነበር፤
አሁንም ያካሂዳሉ። በተለይም ጃፓን የእርሻ መስኳን በከፍተኛ ደረጃ ትከላከላለች። እንደዚህ ዐይነቱ
በመንግስት የተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በ17ኛው ፣ በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ-ዘመን በተለያዩ የአውሮፓ
አገሮችና አሜሪካንም ጭምር በሌላ መልክ ተካሂዷል። የምዕራብ አውሮፓ አገሮች በመንግስት የተደገፈ
ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚና የአገር ግንባታ ፖሊሲ ባያካሂዱ ኖሮ የኋላ ኋላ የገበያ ኢኮኖሚ የሚባለው
መዳበር ባልቻለ ነበር። በታሪክ ውስጥ መንግስት ጣልቃ ሳይገባበት በግለሰብ ተሳትፎ ብቻ ያደገ
የካፒታሊስት አገር ኢኮኖሚ የለም። የመንግስት ጣልቃ-ገብነት በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት
በኋላ ጎልቶ የወጣበት ዘመን ሲሆን፣ እንደ ጀርመን የመሳሰሉት በጦርነቱ ከ80% በላይ የሚሆነው
ኢኮኖሚያቸውና ከተማዎቻቸው የወደሙባቸው አገሮች በመንግስት በተደገፈ ፖሊሲና በልዩ የብድር
ሲስተም (Credit System) በመመካት ነው በ15 ዓመት ጊዜ ውስጥ ከተማዎችን እንደገና መገንባት
የቻሉት፤ ኢንዱስትሪዎቻቸውንም በመጠጋገን ሰፊ የስራ መስክ መክፈት የቻሉት። በዚህ መሰረት ቀስ
በቀስ በሁሉም አቅጣጫ የውስጥ ገበያን ሲያስፋፉ፣ በሁሉም የፌዴራል ግዛቶች ውስጥ የተስተካከለ
ዕድገት ሊስፋፋና ሊዳብር ቻለ። በተለይም ትላልቅ የሳይንስና የቴክኖሎጂ የምርምር ጣቢያዎች
በመንግስት የሚደጎሙ ሲሆኑ፣ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችም ለቴክኖሎጂ ምርምር የበኩላቸውን ገንዘብ
ይመድባሉ። ስለሆነም ልማታዊ የመንግስት ፖሊሲ በተለያዩ አገሮች በተለያየ መልክ የተካሄደና
የሚካሄድም ነው። በተለይም ወደ ኋላ በቀሩ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገሮች በመንግስት የተደገፈ ሁለ-
ገብ ፖሊሲ ማካሄዱ ኢኮኖሚዊና ታሪካዊ ግዴታ ነው። ይህ ካልሆነ አገራችን የማደግ ዕድሏ የመነመነ
ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አገርና ህብረተሰብ የመኖር ዕድሏም እየተበላሸ ይሄዳል። ይህ በራሱ ደግሞ ማህበራዊ
ውዝግብንና የእርስ በርስ ጦርነትን ያስከትላል። ስለሆነም ሰፋ ያለ ሁለ-ገብ የአገር ግንባታ ኢኮኖሚያዊ
ክንዋኔ አማራጭ የሌለው ፖሊሲ ነው ማለት ይቻላል።

ወደ አገራችን የልማታዊ መንግስት ፖሊሲ ስንመጣ ላይ ለማብራራት እንደሞከርኩት የተፈጥሮንና


የህብረተሰብን ህግ የሚፃረር ነው። ለዘረፋ የሚያመችና ጥቂቶችን የሚያደልብ ነው። ከጥገኝነትና
ከለማኝነት የሚያላቅቅ አይደለም። ያልተስተካከለ ዕድገትና ዝርክርክነት ስር እንዲሰዱ ያደረገና
የሚያደርግ ነው። ሰፋ ያለ በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ የስራ-ክፍፍል እንዳይዳብር ያደረገና የሚያደርግ
ነው። በኢንዱስትሪዎች መሀከል በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በኢንዱስትሪዎችና በተቀሩት
የኢኮኖሚ መስኮች መሀከል መተሳሰር( Linkages or Value-added chain) እንዳይኖር ያደረገና
የሚያደርግ ነው። ስለሆነም ስራ ለሚፈልገው ሰፊው ህዝብ የስራ መስክ ሊከፍት ያልቻለና የሚችልም
አይደለም። ይህ ዐይነቱ ልማታዊ የመንግስት ፖሊሲ እንደሰሊጥ፣ ኑግ፣ ተልባና ሌሎችም የዘይት
ጥራጥሬዎች በአገር ውስጥ እየተጨመቁና እየታሸጉ ለህዝቡ እንዲዳረሱ የሚያደርግ አይደለም።
በተቃራኒው ግን እነዚህ የዘይት ቅባት እህሎች በጥሬ መልካቸው ወደውጭ በመላክ ሀብት
እንዲወድም ሊደረግ በቅቷል። በዚያው መጠንም አገዛዙ ከውጭ አገር ጤንነት የሚያቃውስ ዘይት
እያመጣ በመሸጥ የውጭው ንግድ ሚዛን እንዲዛባ አድርጓል ። ይህንን ዘርፍና እጣንን፣ እንዲሁም ቡናና
ሻይን ጥቂቶች ባለሀብታሞች የሚቆጣጠሯቸው ናቸው።

ከዚህ ስንነሳ ይህንን ዐይነቱን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የልማታዊ መንግስት ፖሊሲ እያሉ
መጥራት አላዋቂነት ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ወንጀልም እንደመስራት ይቆጠራል። ከዛሬ ጀምሮ
በኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ቆሜያለሁ፣ ለዲሞክራሲ እታገላለሁ የሚል ሁሉ ይህንን ዐይነቱን አገር ጎጂና
ህዝብን የማይጠቅም ፖሊሲ ልማታዊ እያለ መጥራት አይገባውም። ከዚህ ስህተት መቆጠብ አለብን።
ዝምብለን ሳናውቅ የምናራግበው መፈክር ግልጽ ለሆነ ፖሊሲ የሚያመች አይደለም። ወደፊት ሰፊውን
ህዝብ የሚጠቅም በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ የሆነና ድህነትንና ረሃብን ለአንዴም ለመጨረሻም
ጊዜ የሚያወድም ፖሊሲ ተግባራዊ እንዳይሆን የሚያግድ ነው። በዚህ ላይ መስማማት ካለ ኢኮኖሚክስ
የሚለውን መሰረተ-ሃሳብ በመጠኑም ቢሆን ላብራራ። ስለኢኮኖሚክስ ምንነት ግልጽ ሲሆን ብቻ ነው
ስለኢኮኖሚ ዕድገት ወይም ስለልማት ማውራት የሚቻለው።

ኢኮኖሚክስ ማለት ምን ማለት ነው ?


በአገራችን የተልምዶ አጠራር ኢኮኖሚክስ ማለት የምጣኔ ሀብት ትምህርት እየተባለ ነው የሚጠራው።
የታወቀው የግሪክ ፈላስፋ አርስቲቶለስ ደግሞ ኢኮኖሚክስ ማለት የቤተሰብ ማስተዳደሪያ( Household
Management) እያለ ይጠራዋል። በአገራችን የተለመደው አጠራር ስለኢኮኖሚክስ የተሟላ ነገር ሊነግረን
በፍጹም አይችልም። በሌላ ወገን ግን አርስቲቶለስ ኢኮኖሚክስን የቤተሰብ ማስተዳደሪያ ዘዴ ነው ብሎ
ቢጠራው የሚያስገርም አይደለም። በጊዜው የግሪክ ህዝብ በተለይም በከተማዎች ውስጥ ይኖር የነበረው
እንደዛሬው ሰፋ ባለመልክ የሚገለጽ የህብረተሰብ አወቃቀር አልነበረውም። አብዛኛው የኢኮኖሚ ክንዋኔ
በትናንሽ መስክ የሚካሄድ ስለነበር ሰፋ ያለ የገበያ ኢኮኖሚ የዳበረበት ዘመን አልነበረም። ይሁንና
አርስቲቶለስም ሆነ ፕላቶ ስለንግድ ልውውጥ፣ ስለስራ-ክፍፍልና ስለገንዘብ ምንነትና አስፈላጊነት
በሰፊው አትተዋል። የእነዚህንንም ትርጉምና በአንድ አገር ውስጥም ሰለሚኖራቸው የዕድገት ሚናና
ለህብረተሰብ መተሳሰር አስፈላጊ እንደሆኑ በሚገባ አብራርተዋል።

አገሮች ቀስ በቀስ ወደ ህብረ-ብሄር ሲሸጋገሩና ማዕከላዊ መንግስታት ሲቋቋሙ ይታወቅ የነበረው


ኢኮኖሚክስ ሳይሆን ፖለቲካል ኢኮኖሚ በመባል ነው። ይህም ማለት ከፖለቲካ ጋር የተያያዘና የአንድን
ህዝብ ዕድል መወሰኛ ዘዴ በመሆኑ ነው። ስለሆነም ስለኢኮኖሚክስ ሲወራ ስለብሄራዊ ኢኮኖሚ
ማውራት እንጂ በጠያቂና በአቅራቢ መሀከል የሚገለጽ አልነበረም። በተለይም በጀርመን ምድር
በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሰጠው የኢኮኖሚክስ ትምህርት እንደ አሜሪካንና እንግሊዝ ኢኮኖሚክስ
እየተባለ የሚጠራ ሳይሆን ብሄራዊ ኢኮኖሚ(National Economy) እየተባለ ነው። በ18ኛውና በ19ኛው
ክፍለ-ዘመን በጀርመን ምድር ፍልስፍናና የህብረተሰብ ሳይንስ በሰፊው በመስፋፋታቸው በጊዜው
የተነሱት ምሁራን ኢኮኖሚን ከማህበራዊና ከብሄራዊ ባህርይው ነጥለው አያዩትም ነበር። በእነሱም
ዕምነት የኢኮኖሚ ዕድገት የማህበራዊ ጥያቄዎችንም(The Social Question) የሚያካትትና የሚፈታ
መሆን አለበት። እነ አዳም ስሚዝም ቢሆኑ ስለ ስራ-ክፍፍል አስፈላጊነት፣ ስለማሺነሪና ሰለሰፊ ገበያ
በማተት ኢኮኖሚ ብሄራዊ ባህርይ እንዳለው ለየት ባለመልክ ሊገልጹ ችለዋል። በመሀከላቸው ያለው
ልዩነት ግን ነፃ ንግድ በሚለውና ልቅ የገበያ ኢኮኖሚ መስፋፋት የለበትም ወይም አለበት በሚለው ላይ
ነው። በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ብቅ ያሉት የጀርመን ፈላስፎችና ሳይንቲስቶች የአንድን
ህብረተሰብ ዕድገት ይመለከቱ የነበረው በተናጠል ሳይሆን ሁለንታዊ በሆነ መልክ ስለነበር እንደዚህ
ዐይነት የመንግስትን ሚና አጉልቶ የሚያሳይ የኢኮኖሚ ፖሊሲና የህብረተሰብ ግንባታ አካሄድ ቅድሚያ
መስጠታቸውና መሆንም እንዳለበት ማመልከታቸውና ማስተማራቸው የሚገርም አይደለም።

የኢኮኖሚክስ ፅንሰ-ሃሳብ እየተኮላሸ የመጣው የኒዎ-ክላሲካልስ ወይም የኒዎ-ሊበራል ምሁሮች ከ19ኛው


ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ፅንሰ-ሃሳቡን እያዛነፉ በመምጣታቸው ነው። በእነሱ ዕምነትም፣ የተመጠነ ሀብት
ተግባራዊ የሚሆንበት(The Allocation of Scarce Resources)፣ የአቅራቢና የጠያቂ ጉዳይ(Supply and
Demand) የፍጆታ ጉዳይ፣ አንድን ተመጥኖ የሚገኝ ሀብት አማራጭ በሆኑ ወይም በሚያዋጣ ነገር ላይ
ማዋል፣ የመሳሰሉትን በማስፋፋትና የትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ ሊትሬቸሮችን በማጣበብ ከሳይንሳዊ
ባህርይው ተነጥሎ እንዲታይ አድርገውታል። ስለሆነም ኢኮኖሚክስና ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ በማሰብ
ኃይልና አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ የሚዳብር ሳይሆን፣ ከላይ በተገለጹት መልኮች ብቻ ነው። ከዚህም
በላይ ይህ ዐይነት የኢኮኖሚክስ ፅንሰ-ሃሳብ ስለኢንስቲቱሽን አስፈላጊነትና ስለፈጠራ(Innovation)፣
እንዲሁም ስለህብረተሰባዊ አደረጃጀት በፍጹም አያወራም። ማንኛውም ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ በግለሰቦች
መሀከል የሚካሄድ(Methodological Individualism) ሲሆን፣ ህብረተሰብአዊ ባህርይ የለውም። አንድ
አገር የየግለሰቦች ድምር ውጤት እንጂ፣ እንደማህበረሰብና ህብረተሰብ የሚታይ አይደለም። እያንዳንዱ
ግለሰብ በራሱ ዓለምና ለራሱ ብቻ የሚኖር ነው። በተለይም ከ20ኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ
የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ በማቲማቲክስ እያሸበረቀ በመምጣቱ፣ አንዳንድ የኢኮኖሚክስ ምሁራንና
እንደ ሚሮቭስኪ የመሳሰሉት የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎች ይህ ዐይነቱን አካሄድ የማቲማቲክስን
ችግር ለመፍታት የሚደረግ ጥረት እንጂ የአንድን ህብረተሰብ ችግር ሊፈታ እንደማይችል አረጋግጠዋል።
ሰልሆነም በኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚክስ ምሁሮች ዕምነት ኢኮኖሚክስ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ፣ እንዲህም
ከምርት ክንዋኔ ጋር የሚያያዝ ሳይሆን፣ በንጹህ መልኩ ከንግድና ከፍጆታ ጋር ብቻ የሚያያዝ ነው።
በንጹህ መልኩም የአንድን ሰው በፍጆታ መርካትንና፣ በሌላ ወገን ደግሞ በምርት ክንውን ውስጥ
የሚሳተፈው ባለሀብት ትርፍን ለማትረፍ የተቻለውን ሁሉ የሚያደርግ ነው። ይህ ዐይነቱ አገላለጽ
በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደቫይረስ በመስፋፋቱ በተለይም በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ድህነትና
መዝረክረክ የሚስፋፋበት መሳሪያ ሊሆን በቅቷል። በየአገሮቹ ውስጥ የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሀብት እያለ
ይህንን በማውጣትና በመለወጥ ወይም በማምረት ለመጠቀም ያልተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በተለይም ዶላርና ኦይሮ የዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥና የሀብት ማከማቻ መሳሪያዎች(Exchange and
Reserve Currency) ናቸው ተብሎ ተቀባይነት በማግኘታቸው ብዙ አገሮች ኢኮኖሚያቸውን ካለዶላርና
ካለኦይሮ ማሳደግ የማይችሉ እየመሰላቸው የባሰ የዕዳ ወጥመድ ውስጥ በመግባት ህዝቦቻቸውን
እያደኸዩና ኋላ-ቀርነት ስር እንዲሰድ እያደረጉ ነው። በሌላ ወገን ግን ስልጣኔዎች በሙሉ ሊስፋፏና ሊዳብሩ
የቻሉት ካለዶላርና ካለኦይሮ ነው። የግብጽ፣ የግሪክ፣ የሮማውያንና የቻይና ስልጣኔዎች በሙሉ ዕውን
የሆኑት በሰው የማሰብ ኃይልና ስራ ብቻ ነው። በመሆኑም በታላላቅ ፈላስፋዎችና ኢኮኖሚስቶች
ምርምር መሰረት ማለትም በፊዞክራቶች፣ በመርካንትሊስት የኢኮኖሚ ምሁራን፣ በክላሲካል
ኢኮኖሚስቶችና በካርል ማርክስም ጭምር የሰው ልጅ ጉልበትና የተፈጥሮ ሀብት ብቻ ናቸው ዋናው
የሀብት ወይም የዕድገት ምንጮች። ገንዘብ ይህንን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚውል መሳሪያ ብቻ ነው።
ገንዘብም ራሱ የሰራ-ክፍፍልና የገበያ ዕድገት መዳበር ውጤት እንጂ በራሱ ለዕድገት ቅድመ-ሁኔታ
አይደለም።

ወደ ዋናው መሰረተ-ሃስብ ስንመጣ ኢኮኖሚክስ ማለት ሌላ ነገር ሳይሆን አንድን ነገር በሰው ጉልበት፣
በማሽንና በኃይል(Energy) አማካይነት መለወጥ ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ ማንኛውም የጥሬ ሀብት
ጠቀሜታ ላይ ከመዋሉ በፊት ካለበት ሁኔታ ወደ ሌላ ነገር መለወጥ አለበት። ለምሳሌ ብረትን
ከማግኘታችን በፊት በእሳትና በማሽን አማካይነት ማቅለጥ አለብን። እንዲሁም በማሽን አማካይነት
የተለያየ ቅርጽ በመስጠት የምርት መሳሪያዎችን ለመስራት እንችላለን። ሌሎች የጥሬ-ሀብትና እህሎችም
በዚህ ዐይነት የክንውን ዘዴ ነው ለጠቀሜታ የሚውሉት። ሌላ ምስጢር የላቸውም። ይህም ማለት
ኢኮኖሚክስ ካለሳይንሳዊ ምርምር፣ ካለቴክኖሎጂና ካለምርት ክንዋኔ ሊታሰብ በፍጹም አይችልም።
ኢኮኖሚክስም ከጠቅላላው ከአንድ አገር ዕድገት ጋር የሚያያዝ ሲሆን፣ የአንድ አገር ጥንካሬና ድክመት
በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ተመስርቶ በሚካሄድና፣ ሳይንሰ-አልባ በሆነ መልክ በሚገለጽ ተራ የሸቀጣ
ሸቀጥ ኢኮኖሚክስ አማካይነት ነው። በሌላ አነጋገር ኢኮኖሚክስን ከፖለቲካ፣ ከማህበረሰብ፣ ከባህል፣
ከሳይንስ፣ ከቴክኖሎጂ፣ ከማኑፋክቱርና ከማሽን ነጥሎ ማየት እጅግ አደገኛ ነው። አንድ አገር በባህል
ልትበለጽግ የምትችለውና ውብ ውብ ከተማዎችንና መንደሮችን መገንባት የምትችለው ኢኮኖሚክስ
በሁለመንታዊ ጎኑ ከታየ ብቻ ነው። ስለሆነም የኒዎ-ክላሲካልና የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ ፖሊሲዎች
በሙሉ ይህንን ዐይነቱን ሁለ-ገብ የሆነ የአገር ግንባታ ዘዴ የሚጻረሩ ናቸው ። ስለዚህ ነው በአገራችን
ምድር ባለፉት ስድሳ ዐመታት ድህነትና ረሃብ እየተስፋፉ የመጡት። በዚህ ዐይነቱ አካሄድ ነው ዕውነተኛ
ብሄራዊ ሀብት መፍጠርና አገርን ሁለ-ገብ በሆነ መልክ መገንባት ያልተቻለው። የአገርንም የሰውን
ጉልበትና የጥሬሀብቶችን በስርዓት መጠቀም ያልተቻለው አገዛዞቻችን የተሳሳተ የኢኮኖሚክስ ፖሊሲ
በመከተላቸው ነው። ከዚህ ስንነሳ አገራችንን በፀና መሰረት ላይ መገንባት ከፈለግናና ለተከታታዩም
ትውልድ የሚመካበት ነገር ጥለን ለመሄድ ከፈለግን ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክና
በአጠቃላይ ሲታይ ከዓለም ኮሙኒቲው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚክስ ፖሊሲ መላቀቅ አለብን። ይህ
አንደኛው ሲሆን፣ አሁን ያለውንና አፍጦ አግጦ የሚታየውን ድህነትና ረሃብ፣ እንዲሁም የስራ-አጥነት፣
የከተማዎች በስርዓት አለመገንባትና ሀብትም ወደ አንድ አቅጣጫ መፍሰስ ስንመለከት የእርስዎ አገዛዝ
ደረጃ በደረጃ መውሰድ ያለባቸው እርምጃዎች አሉ። እንዚህን በቅደም ተከተል እንመልከት።

ኢኮኖሚክስና የኢኮኖሚ ፖሊሲ መፍታት ያለባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች !


በመጀመሪያ ደረጃ በአውሮፓ ህብረተሰብ የግንባታ ታሪክ ውስጥ ቅድሚያ የተሰጣቸው እንደምግብና
መጠለያ እንዲሁም ንጹህ ውሃ የመሳሰሉትን መሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶች ማሟላት ነው። በተለይም
የምግብን ችግር ለመቅረፍ በእርሻው መስክ ሳይንሳዊ ጥናት በማካሄድና ለምርታማነት የሚያገለግሉ
የምርት መሳሪያዎችንና ማዳበሪያዎችን በማቅረብ ቀስ በቀስ የምግብ ችግርን መቅረፍ ተቀዳሚው
ተግባር ነበር። እንደሚታወቀው አንድ ሰው ሊሰራና የበለጠ ምርታማ ሊሆን የሚችለው አስፈላጊውን
የምግብ ዐይነቶች ሲያገኝ ብቻ ነው። ይህንን መሰረታዊ ነገር ሳንፈታና፣ በተጨማሪም ገጠሩን የመኖሪያና
የመዝናኛ ቦታ ለማድረግ ስነ-ስርዓት ያለው የልማት ስራ ማካሄድ ካልቻልን የአገራችን የረጅም ጊዜ ችግር
ወደፊትም ይቀጥላል። እንደሚታወቀው ገበሬው ነው በስንት ልፋት በጠዋት እየተነሳና ረጅም ጉዞ
በመጓዝና በመድከም አርሶ አፍርቶ የከተማውን ህዝብ የሚመግበው። የሰው ልጅ ባህርይ ሆኖ ከተማ
ውስጥ የሚኖር ወይም በመንግስት ተቋማት ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ አንድን ህዝብ ለመመገብ ገበሬው
የቱን ያህል እንደሚደክም ግንዛቤ ውስጥ አለማስገባት ነው። በዚህም የተነሳ እርሻና የገበሬው ልፋት
እንዳልባሌ በመታየታቸው በዚህ መስክ መደረግ ያለበት ርብርቦሽ በጣም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
ስለሆነም ገጠሩን፣ የእርሻ ምርት መለገሻ፣ ለማገዶና ለልዩ ልዩ ቁሳቁሶች የሚውሉ ዛፎችን ማብቀያ፣
የአውሬዎችና የልዩ ልዩ ወፎችና እንሴክቶች መኖሪያና፣ የንጹህ አየር መተንፈሻ መሆኑን ተገንዝቦ
በተለይም የእርሻ ሚኒስተር አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ መንግስትዎ እንዲከታተል አጥብቄ
አሳስባለሁ። በዚህ አጋጣሚም በተለይም የደን ልማት መካሄድ ያለበትና ዛፎችም ካለጥናት እንዳይቆረጡ
የእርሻ ሚኒስተር አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ አለበት። ለማገዶ፣ ለሳንቃና ለቤት ስራ፣ እንዲሁም
አካባቢውን ለመጠበቅ የሚያገለግሉ ዛፎች ተለያይተው በአንድ አካባቢ ቢተከሉና እንክብካቤ
ቢደረግላቸው ሚዛናዊ ስራ መስራት ይቻላል። ሰፊው የገጠር ህዝብ ለማሞቂያ ወይም ለመቀቀያ ሲል
ዛፍን ስለሚቆርጥ በላፉት 27 ዓመታት የዛፍ ውድመት ተስፋፍቷል። ይህንን በሚመለከት የርስዎ
መንግስት ልዩ የደን ጥበቃና ልማት ህግ እንደሚያወጣ ተስፋ አደርጋለሁ።

በሁለተኛ ደረጃ የንጹህ ውሃ ማግኘትን ጉዳይ ነው። ይህን ጉዳይ በሚመለከት ልክ እንደምግብ
ተከታታይ የኢትዮጵያ አገዛዞች አስፈላጊውን ትኩረት መስጠት አልቻሉም። ስለሆነም ከሰማንያ በመቶ
በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ንጹህ ውሃ የማግኘት ዕድል የለውም። በተለይም የገጠሩ ህዝብ ብዙ
ርቀት ያለው መንገድ በመጓዝ ነው ከወንዝ ውሃ እየቀዳ ተሸክሞ የሚያመጣው። አሁንም የገጠሩ ህዝብ
እንደማዕከለኛው ዘመን የሚኖር ነው የሚመስለው። የንጹህ ውሃ ማግኘትን ጉዳይ በሚመለከት ወደ
ከተሞችና መንደሮች ስንመጣም እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። በየክልሉ ወረዳዎችና ምክትል ወረዳዎች
ያሉ አስተዳዳሪዎች ብቃትነት ስለሌላቸው ይህንን መሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎት ማሟላት
አልቻሉም። በዋና ከተማችን በአዲስ አበባ ውስጥም የንጹህ ውሃ ማግኘት ችግር አፍጦ አግጦ የሚታይ
ነው። ባለፉት 27 ዓመታት በአዲስ አበባ ውስጥ ካለዕቅድ ብዙ ሁቴል ቤቶችና ትላልቅ ህንጻዎች
በመሰራታቸው ውሃንና መብራትን በከፍተኛ ደረጃ እየተጋሩና ሰፊው ህዝብ በንጹህ ውሃ እጦትና
በመብራት መቆራረጥ እንዲቸገር ተደርጓል። ስለሆነም ማንኛችንም ንጹህ ውሃ ሳንጠጣ አንድም ቀን
ማደር እንደማንችል ተገንዝበን ሰፊው ህዝብ ንጹህ ውሃ ሊያገኝ የሚችልበት ሁኔታ መጠናት፣ መታቀድና
ተግባራዊ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው። ስለልማት ሲወራ በመጀመሪያ ደረጃ እንደዚህ ከመሳሰሉት
መሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶች መነሳት ያስፈልጋል።

በሶስተኛ ደረጃ መፈታት ያለበት መሰረታዊ ጥያቄ የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ነው። እንደምናየው ህዝባችን
አሁንም ቢሆን እንደማዕከለኛው ዘመን የሚኖር ነው። በአገራችን ውስጥ ሰብአዊነትን የተላበሰ ምሁራዊ
እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ለሰው ልጅ ያለን አመለካከት እጅግ የተዛባ ነው። ደካማውንና ደሃውን እንደሰው
አለማየትና፣ ፍላጎትና ምኞት እንደሌለው ሰው አድርጎ መቁጠር በአገራችን የተለመደ ነው። ይህ ዐይነቱ
ችግር በአገራችን ብቻ ያለ ሳይሆን በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የተንሰራፋና ሰፊውን ህዝብ እንደሰው
የማይታይበት ሁኔታ ተፈጥሯል። እንደሚታወቀው አንድ ህዝብ አገሩን አገሬ ብሎ የሚጠራው መኖር
ሲችል ብቻ ነው። የሰው ልጅም መሰረታዊ ነፃነት የሚለካው በአኗኗሩ ነው። ከዚህ ስንነሳ የህዝባችንን
የአኗኗር ዘዴ ለመለወጥ የግዴታ ሁለንታዊ በሆነ መልክ መወሰድ የሚገባቸው ነገሮች አሉ። በተለይም
በከተማ አገነባብ ዕቅድና በአርክቴክቸር የሰለጠኑ ሙያተኞች ከሶስዮሎጂስቶች፣ ከፈላስፋዎችና ከህሊና-
ሳይንስ ተመራማሪዎች ጋር በመመካከር ህዝባዊ ባህርይ ያላቸውና ዘላቂነት የሚኖራቸው የቤት አሰራሮች
በአገራችን ምድር መለመድ አለባቸው። ከተማዎች በደንብ ከታቀዱና ሰውም መኖሪያ ካገኘ አንዳንዱ
ከአመጽ ይቆጠባል። እንደሚታወቀው ማንም ሰው አመጸኛ ሆኖ አይወለድም። በአንድ አገር ውስጥ
ብዙም ሳይታሰቡ ተግባራዊ የሚሆኑ ነገሮች ዲሲፕሊንነት እንዳይኖር ያደርጋሉ። በስርዓት ያልታቀደና
ግልጽ የአሰራር ስልትን ያለመደ ማህበረሰብ ጤናማና ኃላፊነት የሚሰማውን ዜጋ ማፍራት አይችልም።

በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥ የሚሰሩ ትላልቅ ህንፃዎች ከህብረተሰቡ ፍላጎት ጋር የሚጣጣሙ
አይደሉም። በአርቆ አስተዋይነትና በጥበብ የተሰሩ አይደሉም። በተለይም የኮዴምንዩም የቤት አሰራሮች
ለጌቶ(Ghetto) የሚያመቹ ናቸው። አመጽንና ብልሹ ባህልን ሊያስፋፉ የሚችሉ ናቸው። የቤቶቹ አሰራሮች
ከአገራችን ባህል ጋር የሚጓዙ አይደሉም። በተለይም ሽማግሌዎችንና አሮጊቶችን ግንዛቤ ውስጥ
በማስገባት የተሰሩ አይደሉም። ወደ ውስጥ የደረጃዎቹ መወጣጫዎች መሰረታዊ ህግን የጠበቁ
አይደሉም። ሰውን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ናቸው። ከዚህም በላይ ቤቶቹ ጓሮ የላቸውም። የልጆች
መጫወቻዎችም አንድ ላይ አልተሰሩም። በተለይም ብዙ ህዝብ በአንድ አካባቢ እንዲኖር ሲደረግ የግዴታ
አብረው መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። በአካባቢው የቆሻሻ መጣያና ሌሎች ለአካባቢው ንጽህና
የሚያስፈልጉ ጉዳዮች በሙሉ ታስበው መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው። እንደሚታወቀው ማንም
ሰው በዚህች ዓለም ላይ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የሚኖረው። ሲኖር ደግሞ ደስታን ይፈልጋል።
እንደየአሰራራቸው መኖሪያ ቤቶችና አካባቢዎች የደስታ መግለጫዎች ናቸው። ወደ ሌሎች ትላልቅ
ህንጻዎች ስንመጣ እንደዚሁ አስቸጋሪ ሁኔታ እናያለን። አብዛኛዎች ከአራት ፎቅ በላይ ያላቸው ህንጻዎች
የግዴታ መወጣጫ ሊፍት ያስፈልጋቸዋል። በየህንጻዎች ውስጥ ይህንን ማስገባት ብዙ ወጪን መጠየቁ
ብቻ ሳይሆን የውጭ ምንዛሪንንም ይጋራል። ሲበላሹም ጠጋኝ ያስፈልጋል። በዚህ ሙያ የሰለጠነ ሰው
ለማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው። ከዚህም በላይ ሊፍቶች በመብራት የሚንቀሳቀሱ ስለሆነ የግዴታ
መብራትን ይጋራሉ። ያም ተባለ ይህ የመኖሪያ ቤቶችም ሆነ የንግድና የመንግስት መስሪያቤቶች ከአገሪቱ
የሀብት ሁኔታ፣ ከባህልና ከታሪክ ጋር እየተመዛዘኑ ቢገነቡ ይሻላል። ከዚህም ባሻገር ዘላቂነት ያላቸውና
ለማደስም የሚያስቸግሩ መሆን የለባቸውም። የዘላቂነታቸው ጉዳይ ደግሞ በማቴሪያሉ ዐይነት
የሚወሰን ነው። የቤት አሰራሮች ከብሎኬት ይልቅ በጡብና በዲንጋይ ቢሰሩ ጤናማና ለአገራችን አየር
የሚስማሙና እንደ አየሩ ሁኔታ ራሳቸውን የሚያቀናጁ ናቸው።

በአራተኛ ደረጃ መፈታት ያለበት ጉዳይ አጠቃላዩን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚመለከት ነው። ያለፉትን ስድሳ
ዐመታት የአገራችንን የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ስንመለከት ከህዝብና ከአገር ግንባታ ጋር ተያይዘው የታቀዱ
ባለመሆናቸው በአገራችን ምድር በተለያየ መልክ ለተገለጹትና ለሚገለጹት ውስብስብ ችግሮች እንደዋና
ምክንያቶች ሊቆጠሩ ይችላሉ፤ ናቸውም። የብሄረሰብ ችግርና በየቦታው የሚታየው የአመጽ ሁኔታ
ከኢኮኖሚ ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው። ማንኛውም ሰው የሚሰራ ከሆነና አስተማማኝ የገቢ ምንጭ ካለው
ቤተሰብ መስርቶ ልጆት ወልዶ ደስታን መጎናጸፍ ይመኛል። ሁሉም ሰው በስራ ከተወጠረና የሚሯሯጥ
ከሆነ ሌላ መጥፎ ነገር አይታየውም። ስለሆነም ለአንድ አገር ሰላም መስፈን የግዴታ የኢኮኖሚ ጉዳይ
መፈታት አለበት።

እንደሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮችም በአገራችን ያለው ችግር የአገር ውስጥ ገበያ(Home Market)
የሚባለው መሰረታዊ ጉዳይ አለመታወቁ ነው። ስለሆነም መንግስታት የሚያተኩሩት የውጭ ከረንሲ
ለማግኘት ሲሉ ለውጭ ገበያ ላይ በሚቀርቡ የጥሬ-ሀብቶችና የእርሻ ሰብሎች ላይ መሰመራት ነው።
ይህንንም የሚያደርጉት በውጭ አገር ኤክስፐርቶች እየተመከሩ ነው። ስለሆነም የግዴታ ወደ ውስጥ
ያተኮረ(Inward-looking strategey) የኢኮኖሚ ፖሊሲ መከተሉ ለተስተካከለና ፍትሃዊነት ለሚኖረው
የኢኮኖሚ ዕድገት ይጠቅማል። ይህንንም በሚመለከት በተለይም እንደ ቻምበርስ ኦፍ ኮመርስና
የኢንቬስትሜንት ቢሮ ምን ምን ዐይነት ኢንዱስትሪዎች በየቦታው ቢቋቋሙ ሰፋ ያለ ብሄራዊ ሀብት
መፍጠር ይቻላል? ብለው ምርምርና በቂ ጥናት ማድረግ አለባቸው።

በአገራችን ያለው ሌላው ችግር ሀብት ወይም ገንዘብ ያለው ቴክኖሎጂ በሆኑ ነገሮች ላይ አለመሰማራቱ
ነው። አብዛኛው በተለያየ የኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ ከመሰማራት ይልቅ ቶሎ ቶሎ ትርፍ ወደሚያገኝበትና
ወደሚከብርበት ላይ ነው የሚሰማራው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ተደጋጋሚና ተመሳሳይ የኢኮኖሚ
እንቅስቃሴዎች በየቦታው ተስፋፍተው ይገኛሉ። ሁሉም ቡና አምራች መሆን ይፈልጋል። አንዱ ሆቴል ቤት
ሲሰራ ሌላውም ሆቴል ቤት ልስራ ብሎ ይነሳል። ይህ ዐይነቱ አካሄድ እንደባህል ሆኖ በመወሰዱ የአገር
ውስጥ ሀብት በከንቱ ይወድማል። የስራ መስክ ለሚፈልገውም በየቦታው በቂ የስራ መስክ መክፈት
አይቻልም።

ስለሆነም አንድ አገር ሊያድግና ሊያብብ የሚችለው፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ ፍትሃዊነት የሚኖረው ሰፊው
ህዝብና ሀብታሙ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ ሲሰማሩ ነው። እንደ ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች፣
ልዩ ልዩ መሳሪያዎችንና የቤት የፍጆታ ዕቃዎችንና ቁሳቁሶችን መስራትና ማምረት ኢኮኖሚውንም ሆነ
ህብረተሰቡን የበለጠ እንዲተሳሰሩ ያደርጋቸዋል። በኢኮኖሚክስ ሳይንስ መተሳሰርና(Linkages)
ተጨማሪ ምርት ማምረት(Value added) የሚባሉ መሰረተ-ሃሳቦች አሉ። እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች
በጭንቅላት ውስጥ ሲቋጠሩ ነው አንድን አገር በሁሉም አቅጣጫ መገንባት የሚቻለው። እንደምናየው
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ሳይንስን ያልተከተሉና ፈራቸውን እየለቀቁ
በመምጣታቸው በየአገሮች ውስጥ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እየታየ ነው። ስግብግብነትና ስልጣንን
መቀዳጀት እንደዋና ፈሊጥ እየታዩ በመምጣታቸው በየአገሮች ውስጥ ባህሎች እየፈራረሱ ነው። ባህላዊ
መሳሪዎችንና ዕቃዎችን ከመስራት ይልቅ ሁሉም ነገር ከትርፍ አንፃር ስለሚተለም በየአገሩ ያሉ ህዝቦች
ወዴት እንደሚጓዙ እንዳያውቁ ተደርገዋል። ለዚህ ሁሉ ተጠያቂዎች በየአገሩ ያሉ መሪዎች ሲሆኑ፣ ለዚህ
ዋናው ምክንያት ደግሞ ንቃተ-ህሊናቸው ዝቅተኛ ስለሆነ ነው። ስለሆነም ማህበራዊና ህብረተሰብአዊ፣
ታሪካዊና ባህላዊ እንዲሁም የኢኮሎጂ ኃላፊነት አይደሉም። ህብረተሰብም ምን ማለት እንደሆነ
የሚገባቸው አይደሉም።

ከዚህ በመነሳት በአገራችን ምድር በአንዳንድ ቦታዎች የሚቋቋሙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ብዙ ነገርችን
ያላገናዘቡና ዘላቂነትም ያላቸው አይደሉም። እንደሚታወቀው በየኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ
የሚመረቱት የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶችና ጫማዎች ለውጭ ገበያ ተብለው ነው። ይህም ማለት አንድን
አገር በሁሉም አቅጣጫ በማሳደግ የሚጫወቱት ሚና አልቦ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህም ባሻገር የውጭ
ገበያው ከተለያዩ አገሮች በሚመረቱ ምርቶች የተያዘ እንደመሆኑ መጠን የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች
በርካሽ የሚሸጡ ናቸው። ይህም ማለት የውጭ ምንዛሪን ችግር ለመቅረፍ አይቻልም ማለት ነው።

ከዚህ ዐይነቱ አካሄድ ይልቅ በማሺንና በማኑፋክቱር ላይ ያተኮረ የኢንዱስትሪ ፓርክ ማቋቋሙ የተሻለ
ነው። ይህንን በሚመለከት ከቻይና ይልቅ እንደ አውስትሪያ ከመሳሰሉት አገሮች ጋር ልዩ ስምምነት
በማድረግ የቴክኖሎጂ ልውውጥ ማድረግ ይቻላል።

በአምስተኛ ደረጃ በአገራችን ምድር ዕድገትን ለማፋጠን ከተፈለገ ከዩኒቨርሲቲዎች ይልቅ ተግባራዊነት
ያለው የተግባረ-ዕድ ትምህርት ቤት በየቦታው ቢከፈት ጥሩ ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ አማራጭነት
የሌለውና ለአንድ አገር ዕድገት ቁልፍና መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ይህንንም በሚመለከት ከአውስትሪያና
ከጀርመን ጋር ልዩ ስምምነት ማድረግ ይቻላል። ዋናው ቁም ነገር ግን ፍላጎት መኖሩና ዕድገት
የሚባለውን መሰረተሃሳብ መረዳት ነው።

በአገራችን ምድር ፍትሃዊነት ያለበትና ፈጣንና የተስተካከለ ዕድገት እንዲመጣ የምንፈልግ ከሆነ ከኒዎ-
ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የግዴታ መላቀቅ ይኖርብናል። ሁለ-ገብ የሆነ የአገር ግንባታ ፖሊሲ መከተሉ
እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ለዚህ ቁልፉ ደግሞ ሰፋ ያለ የማኑፋክቸር እንቅስቅሴ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ
ናቸው።

በስድስተኛ ደረጃ፣ የሚነሳው ጥያቄና መሰረተ-ሃሳብ ይህንን ሁሉ አጠቃላዩን የአገራችንን


ኢኮኖሚና የአገር ግንባታ ገንዘብ ከየት በማምጣት ነው ለመደጎም ወይንም ፋይናንስ ለማድረግ
የምንችለው? የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥና በአገር ግንባታ አካሄድ
ማንኛውም አገር ከምንም በመነሳትና በማሰብ ኃይሉ በመመራት ነው ተፈጥሮን በቁጥጥሩ ስር ማድረግ
የቻለውና በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ነገሮችን አውጥቶ በመለወጥ ለጠቀሜታ ያዋለው። እንደዚሁም
ገንዘብም የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ውጤት ሲሆን፣ ከስራ ክፍፍልና ከገበያ ማደግ ጋር የተያያዘ ነው።
ፓውንድና ዶላር ወይም ኦይሮ የዓለም አቀፍ የንግድ መለዋወጫና የሃብትም ማጠራቀሚያ ገንዘቦች
መሆን እስከቻሉ ድረስ እያንዳንዱ አገር በራሱ ገንዘብ ነው አገሩን ሊገነባ የቻለው። እንግሊዝ፣ ጀርመንና
አሜሪካን በራሳቸው ገንዘብ ነው የኢንዱስትሪ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት መሆን የቻሉት።
በካፒታሊዝም ዓለም አቀፋዊነት የተነሳ ሁሉ ነገር ተጣሞና ተዛብቶ ስለሚቀርብ በተለይም እንደኛ ያሉ
አገሮች ካለዶላርና ኦይሮ ማደግ የማይቻል ይመስላቸዋል። ስለሆነም የብድር ወጥመድ ውስጥ በመግባት
የማይወጡት ሁኔታው ውስጥ በመስመጥ በዕዳ ከፋይነት የአገራቸውን ሀብት እንዲያሰተላልፉ
ተገደዋል። የዚህ ሁሉ ችግር የገንዘብን አነሳስ ታሪክና ዕድገት፣ እንዲሁም ባህርይና ሚና ካለመረዳት የተነሳ
ነው። ይህ ማለት ግን የዓለም መገበያያ ገንዘብ አያስፈልገንም ማለቴ አይደለም። ለማለት የምፈልገው
ለአገር ውስጥ የውስጥ ገበያ(Home Market) ዕድገት ዶላርና ኦይሮ ሳይሆኑ የአገራችን ብር ነው ዋናው
የዕድገት አንቀሳቃሽ መሳሪያ ሊሆን የሚችለው።

ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ለማድረግና፣ በማዕከለኛና በአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ተሰማርተው


ለሚንቀሳቀሱ ገንዘብ ለማቅረብ የግዴታ በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚተዳደር የብድርና የቁጠባ ባንክ
መቋቋም አለባቸው። ይህ ዐይነቱ የባንኪንግ ሲይሰተም በህዝብ ዘንድ ያለውንና ጠቀሜታ ላይ
የማይውለውን ወይንም ባልባሌ ቦታ ላይ የሚሰማራውን ገንዘብ በምርት ላይ ለማዋል የግዴታ
የመንግስት ወረቀት(Bonds and Securities) በማቅረብ በዝቅተኛ ወለድ አማካይነት ከሰፊው ህዝብ
ገንዘብ በመሰብሰብና ይህንን በጥናትና በዕቅድ መሰረት እንደገና ለአምራቾችችና በመዋዕለ-ነዋይ
ለሚሰማሩ መልሶ በማበደር በገንዘብና በምርት መሀከል ያለውን ግኑኝነት ማጠንከር ይቻላል። ይህ ብቻ
ነው ፍቱኑ የዕድገት መንገድ። ከዚህ በተጨማሪ ወደ ውጭ የሚወጣውንና ወደ አገር ቤት ውስጥ
የሚገባውን የውጭ አገር ገንዘብ መቆጣጠር ያስፈልጋል። በዚህ መሰረት የሚሰበሰበው ገንዘብ የግዴታ
ማሽኖችንና ቴክኖሎጂዎችን ለማስመጣት ብቻ የሚውል መሆን አለበት። የቅንጦት ዕቃ ላይ
የሚሰማራውን የውጭ ገንዘብ የግዴታ መቆጣጠር ሲገባ፣ ከውጭ በሚመጡ የቅንጦት ዕቃዎች ላይ
ከፍተኛ ቀረጥ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው።

በሰባተኛ ደረጃ፣ ምግብ ለስራ የሚል ልዩ ፕሮግራም ማቋቋም ያስፈልጋል። መንገድን፣ ድልድይን፣
ተምህርት ቤቶችን፣ የገበያ አዳራሾችን፣ ካናል ሲይሰተሞችን፣ ጋርደኖችንና ዛፎችን ለመትከል የግዴታ
ስራ-ፈት የሆነውን ህዝብ በስራ ማሰማራት ያስፈልጋል። ምክንያቱም በስራ አማካይነት ብቻ ነው ብሄራዊ
ሀብት ሊፈጠር የሚችለው። የስው ጉልበትና የተፈጥሮ ሀብት ብቻ ናቸው የሀብት ዋናው ምንጮች።
ስለሆነም ይህንን ፋይናንስ ለማድረግ ማንኛውም አገር ቤት የሚኖረውም ሆነ ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ
በሙሉ ገንዘብ በማዋጣት መሳተፍ አለበት። ይህንን መንገድ የምንከተል ከሆነ ኢትዮጵያን በሃያና በሰላሳ
ዐመታት ውስጥ ልንቀይራት እንችላለን። ለሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ምሳሌ ልንሆን እንችላለን።

ስምንተኛ፣ የአገርን የተፈጥሮ ሀብትና የተትረፈረፈውን የሰው ኃይል በስራ ላይ ለማሰማራት የግዴታ
የተቀላጠፉና ዘመናዊ የሆኑ ተቋማትን(Institutions) በአገር አቀፍ ደረጃ መገንባቱ እጅግ አስፈላጊ ነው።
እንደሌሎች የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያም ዘመናዊና ብቃትነት ያላቸው፣ እንዲሁም ህዝብ
የሚመካባቸውና ብሶቱን የሚያሰማበት ተቋማት የላትም። ያሉት ተቋማት በጣም ደካማ ከመሆናቸው
የተነሳ በየክልሉና በየወረዳው እንዲሁም በትናንሽ ከተሞች ስራ ፈቶ የሚቀመጠውን የሰው ኃይል
ለማንቀሳቀስ በፍጹም አይችሉም። የአንድ አገር መኖርና ህብረተሰብም ተከታታይነት ሊኖረው
የሚችለው ዘመናዊና የተከበሩ ተቋማት ሲኖሩት ብቻ ነው። በየቦታው ያሉት የመንግስት መስሪያ ቤቶችና
ኢንስቲትሽኖች ግርማ ሞገስ የሌላቸው ናቸው። ለአንድ አገር ክብር የሚያሰጡ አይደሉም። ከዚህ ባሻገር
በየቦታው ብቃትነት ያላቸው ተቁማት ባለመኖራቸው የተነሳ የውጭ ኃይሎች በየቦታው በቀላሉ
ለመዘዋወርና የአገርን ብሄራዊ ነፃነት የሚያደፈርስ ስራ ሊሰሩ ይችላሉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ
ህዝባችን ሊከበርና እንደሰው ሊታይ የማይችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል ማለት ይቻላል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣
የጠንካራ ተቋማት መኖር ለሰላም መኖር በጣም አስተማማኝ ነው። ስለሆነም መንግስት በዚህ ላይ
ጠንከሮ ብሎ መስራት ያለበት ጉዳይ ነው።

ዘጠነኛ፣ ተቋማት ብቃት እንዲኖራቸው ከተፈለገ አዲስ የሰው ኃይል ማሰልጠን ያስፈልጋል። አዲስ
አስተሳሰብ ያለውና ውስጠ-ኃይሉ ከፍ ያለ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለአገር ግንባታ እጅግ ያስፈልጋል።
በግልጽ እንደሚታየው አንደኛውና መሰረታዊ ለአገር ዕድገት እንቅፋት የሆነው ጉዳይ ዲሲፕሊንነት
ያለው፣ ኃላፊነተ የሚሰማውና በተቀለጣፈ መልክ የሚሰራ ቢሮክራሲያዊ ኃይል አለመኖሩ ነው።
በአጠቃላይ ሲታይ በተለይም የሲቪል ቢሮክራሲው ብሄራዊ ስሜት የሌለውና እራሱን ከሰፊው ህዝብ
አግሎ የሚኖር ነው። ብሄራዊ ባህርይ የሌለውና ንቃተ-ህሊናው ደካማ የሆነ ቢሮክራሲ በሰፈነበት አገር
በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት አይቻልም። ጃፓን፣
ደቡብ ኮሪያና ቻይና በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳየትና ቴክኖሎጂን መቆጣጠር
የቻሉት በከፍተኛ ብሄራዊ ስሜት በመነሳሳት ነው። ራሳቸውን ላለማስደፈር ቀን ከሌት በመስራታቸው
ነው። በሌላ ወገን ግን በእኛ አገር ኃላፊነትን መወጣት ማለት ምን ማለት እንደሆነ በማይታወቅበት አገር
አንድ ሚኒስተርም ሆነ የበታች ሰራተኛ በቀን ከስምንት የስራ ሰዓት ውስጥ ጥቂቱን ብቻ ነው በስራ ላይ
የሚያውሉት። ከብሄራዊ ስሜት መጉደል ሌላ፣ ሌላው ምክንያት የአገራችን ኢኮኖሚ ውስጣዊ ኃይሉ
በጣም ደካማ በመሆኑ ቢሮክራሲው ላይ ጫና ማድረግ አይቻልም። ከዚህ ባሻገር አንድ ሚኒስተርም ሆነ
ሌሎች ባለስልጣናት ሚኒስተር መሆናቸውን ነው እንጂ የሚመለከቱት፣ የመቶ ሚሊዮንን ህዝብ ዕድል
በእጃቸው ላይ እንደተንጠለጠለ በፍጹም የገባቸው አይመስልም። ከዚህ ስንነሳ ስለዘመናዊ አስተሳሰብ
በሚወራበት ጊዜ የግዴታ ዘመናዊ አስተሳሰብ ያላቸውንና ኃላፊነት የሚሰማቸውን ሰዎች በተለይም
ቁልፍ ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች ማስቀመጥ ያስፈልጋል። አብዛኛዎቹ ሚኒስተሮች በተለይም የኢኮኖሚና
የገንዘብ ሚኒስተሮች የኢኮኖሚ ፖሊሲን ምንነት በቅጡ መረዳት አለባቸው። ከውጭ ኤክስፐርቶች
ምክርን እየተቀበሉ ተግባራዊ የሚያደርጓቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ወደ ውስጥ ያተኮረና
ድህነትን ሊቀርፉ የሚችሉ አይደሉም። በአንጻሩ ድህነትን ፈልፋይ በመሆን የሰው ጉልበትና የተፈጥሮ
ሀብት እንዲባክኑ ለማድረግ በቅተዋል። ይህ ጉዳይ ከአፄው አገዛዝ ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣና፣
ለድህነትና ለረሃብ ዋናው ምክንያት የሆነ የአስተሳሰብና የአሰራር ዘዴ ነው።፡ ባጭሩ እነዚህን ከላይ
የተዘረዘሩትን ዘጠኝ ነጥቦች ቀስ በቀስ ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ የተቀላጠፈ ዕድገት ማየት እንችላለን።
ህዝባችንም ብሄራዊ ስሜቱ መዳበሩ ብቻ ሳይሆን የበለጠ ይተሳሰራል። መልካም ግንዛቤ !!

ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ የዕድገት ኢኮኖሚክስ ምሁር ሲሆን፣ በርሊን በሚገኘው ፍሪ ዩኒቨርሲቲ፣በኢኮኖሚ ኮሌጅ፣
በመቀጠልም በቲክኒካልና በኢኮኖሚ ኮሌጅ ፣ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ፣ ስለዓለም አቀፍ ንግድ ፣ ስለ ዓለም አቀፍ
ገንዘብና ስለ ዕዳና ጠንቁ አስተምሯል። በተለያዩ ኢንስቲቱሽኖች ስለአፍሪካ የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ ስለ ዓለም አቀፍ
ተቋማት ሚና

በየጊዜው ሰሚናር ይሰጣል። በጀርመን አገር የሚገኙ ኢምባሲዎችን ያማክራል። በቅርቡ „African Predicaments

and the Method of Solving them Effectively“ የሚል መጽሀፍ ጽፏል። በተጨማሪም በአማርኛ „ካፒታሊዝም
„ በሚል አርዕስት ስለካፒታሊዝም ዕድገት መሰረተ-ሃሳቦችና አነሳስ ታሪክ መጽሀፍ ጽፏል። ከዚህ በተረፈ በብዙ
መቶዎች የሚቆጠሩ መጣጥፍፕችን ጽፎ ለአንባቢያን አቅርቧል። በተጨማሪም ለተለያዩ ውጭ አገር ለሚገኙ
የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያዎች ለብዙ ቃለ-መጠይቆች መልስና ማብራሪያ ሰጥቷል። በቅርቡ ለኢሳት የቴሌቪዥን
ጣቢያ „ሰው ለመኖር የሚችልባትንና ሰዎችን ለማስተናገድ የምትችል አገር እንገንባ“ የሚል ሁለት ሰዓት የፈጀ
የቃለ-መጠይቅ ማብራሪያ ሰጥቷል።

fekadubekele@gmx.d

ንድ አገር ታሪክ የሚሰራበት መድረክ እንጂ የጦርነት


መድረክ አይደለም !!
ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

ህዳር 4 ፣ 2018

መግቢያ

ያለፉትን አርባ ዓመታት በአገራችን ምድር በፖለቲካ ስም የተፈጸመውን ግፍና አገርን የማፈራረስ
ድርጊት ስንመለከት በአብዛኛው የፖለቲካ ተዋናይ ነኝ ባይ መንፈስ ውስጥ የተቀረጸው አርቆ-አስተዋይነት
ሳይሆን ስሜታዊ አስተሳሰብ እንደሆነ መገንዘቡ ከባድ አይሆንም። በተለይም የግዴታ ስልጣን ላይ
መውጣት አለብን ብለው በደመ-ፍላት ይታገሉ የነበሩና አሁንም የሚታገሉ ኃይሎች የተወሰነውን
የህብረተሰብ ክፍል፣ በተለይም ወጣቱን በመፈክር ጋጋታና በጥላቻ መንፈስ በመመረዝ በቀላሉ ሊፋቅ
የማይችል መፈራራትና ጥርጣሬ እንዲስፋፋ አድርገዋል። በተጨማሪም ለብዙ መቶ ሺህ ወጣቶች
መሞት፣ መገረፍ፣ እስር ቤት መጣልና ወደ ውጭ አገር መሰደድ ምክንያት ሊሆኑ በቅተዋል። በአገራችን
ምድር በህቡም ሆነ በይፋ፣ መንግስትንም ጨምሮ የፖለቲካ መድረኩን የያዙት ኃይሎች በሙሉ ፖለቲካ
የሚባለውን ጽንሰ-ሃሳብ የተገነዘቡት ታሪክን መስሪያ ሳይሆን፣ መሸወጃና ማስፈራሪያ፣ እንዲሁም
ተንኮልን በመሸረብ ስልጣን ላይ መወጣጫ እንደሆነ ነው። አብዛኛው ታጋይ ነኝ የሚል ኃይል ግልጽ በሆነ
ፍልስፍናና የህብረተሰብ ርዕይ የሚመራ ሳይሆን የራሱን የተደበቀ ዓላማ ብቻ ተግባራዊ ለማድረግ
የሚሯሯጥ ነው የሚመስለው። በመሆኑም ሁሉም በየፊናው ድርጅት ፈጠርኩ እያለ ህብረተሰብአችንን
የሚያተራምስ እንጂ ኃይሉን በመሰብሰብ ለመሰረታዊና ዘላቂነት ለሚኖረው ለውጥ የጋራ ግምባር
በመፍጠር የተከበረችና የምትፈራ አገር ለመገንባት አይደለም። ይህ ዐይነቱ በቡድን በቡድን እየተሰባሰቡ
ወደህና ወዲያ ማለት እንዳየነውና የአገራችንም ሁኔታ እንደሚያረጋግጠው ሰብአዊነትን ለተላበሰ ነፃነትና
ለዲሞክራሲ የሚደረገውን ትግል በማደናቀፍ ላይ ይገኛል። የህዝባችንን ስቃይ እያራዘመውና ህልሙን
እያጨለመው እንደሆነ ነባራዊው ሁኔታ ያረጋግጣል።

Videos From Around The World


በአገራችን ምድር የተፈጠረውን መወዛገብና የአገርን ህልውና መዳከም በምንመለከትበት ጊዜ
መብታችንና የማንነታችን ጥያቄ ይክበር ብለው የብሄረሰብን አርማ ይዘው በተነሱ ኃይሎች ላይ ብቻ
የሚሳበብ አይደለም። በአርባ ዓመት የውድቀትና የአገር መፈረካከስ ትግል ውስጥ አውቀውም ሆነ
ሳያውቁ በተለይም ከአማራ፣ ከትግሬ፣ ከኤርትራና ከኦሮሞ ብሄረሰብ የተውጣጡ ስልጣን ለእኛ ይገባናል
ባይ ኤሊቶችና „የማርክሲዝምን ሌኒንዝምን“ አርማ አንግበው የሚታገሉ ሁሉ ዛሬ አገራችን ለደረሰችበት
አደገኛ ሁኔታ በአብዛኛው መልኩ ወይም መቶ በመቶ ተጠያቂዎች ናቸው ብል የምሳሳት አይመስለኝም።
እዚህ ላይ ግን መያዝ ያለበት ጉዳይ፣ ችግሩ የመነጨውና የሚመነጨው 95% ከሚሆነው የአማራ ፣
የትግሬ፣ የኤርትራና የኦሮሞ ህዝብ ሳይሆን፣ ተምሬአለሁ፣ ተገልጾልኛል፣ ስለዚህም የብሄረሰቤን መብትና
የማንነት ጉዳይ ማስጠበቅ አለበኝ ከሚለው በፐርሰንት ሲለካ 5% በታች ከሚሆነው „ኤሊት“ ነው። ይህ
ችግር በአገራችን ብቻ ያለ ጉዳይ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በተለይም በላቲን፣ በማዕከለኛው
አሜሪካና በአፍሪካ አገሮች ጎልቶ የሚታይ ጉዳይ ነው። ይህም ማለት በአገራችንና በሌሎች በማደግ ላይ
ባሉ አገሮች ውስጥ የሚታየው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውስ፣ እንዲሁም
የባህልና የአካባቢ ውድመት ዋናው ምክንያት ኤሊቱ ነው ማለት ይቻላል። ወደ አገራችን ስንመጣ
ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች የተነሱትና የጎሳ ጉዳይ ቀሰ በቀስ ስር እየሰደደ የመጣው በጊዜው
መወሰድ ያለባቸው በሳይንስ ላይ የተመሰረቱ ፖለቲካዊ መፍትሄዎች ባለመታወቃቸውና፣
የፖለቲካና ከጎሳ ጋር የተያያዙ የመብት ጥያቄዎች ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋ ግንዛቤ ውስጥ
ባለማስገባት ነው። በሌላ ወገን ደግሞ የመብት ጥያቄዎችን ያነሳው ከዚህም ሆነ ከዚያኛውም ብሄረሰብ
የተውጣጣው ኤሊት በፍልስፍና ሳይንስ መነጽር ሲመረመር ችግሩን ለመፍታት የሄደበት መንገድ እጀግ
አደገኛና፣ እንደምናየው ችግሩን የበለጠ ውስብስብ ያደረገና በቀላሉም መፍትሄ እንዳይገኝለት በሩን የዘጋ
አካሄድ ነው ማለት ይቻላል።፡

የአገራችንን ሁኔታ ጠጋ ብለን ስንመለከት እስከዛሬ ድረስ የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው የታገሉና
የሚታገሉ ጨቋኝ ከሚባለውም ሆነ ተጨቁኜአለሁ ከሚለው የህብረተሰብ ክፍልና ብሄረሰብ
የተውጣጡትን ሁኔታ ስንመለከት ሁሉም የመማር ዕድል ያገኙና ዩኒቨርሲቲ መግባት የቻሉ ናቸው።
ከዚያም አልፈው ስኮላርሺፕ ተፈልጎላቸው በመንግስት ወደ ውጭ አገር የተላኩ ናቸው። አብዛኛዎቹ
ደግሞ በኢኮኖሚም ሆነ በማህበራዊ ስታተሱ ሻል ብሎ ከሚገኝ የህብረተሰብ ክፍል የተወለዱ ናቸው።
በመሰረቱ አንድ ልጅ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ስታተሱ ሻል ካለ የህብረተሰብ ክፍል ከተወለደ አርቆ
የማሰብና የማመዛዘን ኃይሉም ከፍ ያለ ነው ብለን እንገምታል። ስለሆነም ባገኘው ዕውቀትና እንክብካቤ
ታሪኩንና የህብረተሰቡን ዕድገት የመረዳት ኃይሉ ከፍተኛ ይሆናል ብለን እናስባለን። ይሁንና ግን
ያለፉትን ሃምሳ ዓመታት የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ስንመመረምር መማርና ከተሻለ የህብረተሰብ ክፍል
መውጣት የግዴታ አርቆ አስተዋይነትን ከጭንቅላት ጋር ያዋሀደ አይደለም። ይህ ማለት ግን ከላይኛው
ወይም ከተሻለ የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጣ ኤሊት በሙሉ እርኩስ ዓላማ አለው ማለት አይደለም።
ጥቂቶች በአርቆ-አስተዋይነትና በአገር ወዳድነት ስሜት ለህዝባቸውና ለአገራቸው እንደታገሉና
እንደተሰውም የሚታወቅ ጉዳይ ነው። የአውሮፓውን የህብረተሰብን ታሪክና የሳይንስን ዕድገት
ስንመለከት ለሰው ልጅ መሻሻል ከፍተኛውን አስተዋጽዖ ያበረከቱት ከላይኛው የህብረተሰብ ከፍል
የመጡና የተማሩ ሊቃውንት እንደነበሩ ማረጋገጥ ይቻላል። ሳይንሳዊ ግኝቶችና ፍልስፍናዎች በሙሉ
የተፈጠሩት ከአሪስቶክራሲው የህብረተሰብ ክፍል ከመጡ ምሁራን ነው። እንደነዚህ ዐይነት ሊቃውንቶች
ባይፈጠሩና ለዕውቀትም ከፍተኛውን ቦታ ባይሰጡ ኑሮ የሁላችንም እጣ እንደእንስሳ መኖር ይሆን ነበር።
ወደ አገራችን ስንመጣ ግን ጉዳዩ ለየት ይላል። በፖለቲካ መድረክ ውስጥ ገብቶ ተዋናይ የሆነው ወይም
ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለው ውዝግብ ከመፍጠር ይልቅ ፈጣሪና፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገትን አራማጅ
መሆን በፍጹም አልቻለም። የአገራችንንም ችግር በህብረተሰብ የሳይንስ መነፅር በመመርመርና ውጣ
ውረድነቱን በመገንዘብ ሳይንሳዊ መፍትሄ ሊሰጥ አልቻለም። በየጊዜው የሚያነሳቸው ጥያቄዎችና
የሚያስተጋባቸው መፈክሮች ህብረተሰብአዊ ቅራኔዎችን የሚያሰፉ እንጂ በማጥበብ ህዝባችን ለአንድ
ዓላማ እንዲነሳ የሚጋብዙ አይደለም። ከዚህ ስንነሳ አባዛኛውን ጊዜ ህዝባችን የሚጠይቀውና ግራ
የሚጋባው የመማር ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው ? እያለ ነው። መማር ማለት አገርን ማፈራረስ ከሆነ ይህ ዐይነቱ
ትምህርት ቢቀር ይሻላል እያለ ብሶቱን ይገልጻል። መማር ማለት ግልጽነትን መቀዳጀትና ለአንድ ችግር
መፍትሄ ለማግኘት የሚረዳ ወይስ በአለው ችግር ላይ ሌላ ችግር በመፍጠር አንድን ህብረተሰብ
የሚያዘበራርቅ ነው ? እያለ ጥያቄዎችን ያነሳል።

ከተማረ ሰው ወይም ምሁር ነኝ ከሚል የሚጠበቅ መሰረታዊ ነገር !

በመሰረቱ አንድ ሰው ትምህርት ቤት የሚሄደው ዕውቀትን ለመገብየት ነው። አንድ ሰው


ትምህርት ከመቅሰሙ በፊት በቀላሉ ሊገባውና ሊረዳው የማይችላቸውን ነገሮች ሲማር ራሱንና ማንነቱን
የበለጠ ማወቁ ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮንና የህብረተሰብንም ህግ ሊረዳ ይችላል የሚል ግንዛቤ አለ።
በዚህም መሰረት የኑሮን ትርጉምና የሰው ልጅስ ለምን በዚህች ዓለም ላይ ተፈጠረ፣ ሚናውስ ምንድነው
ብሎ ማውጣትና ማውረድ ይችላል ተብሎ ይታመናል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ስነ-ምግባርንና ግብረገብነትን
በመማርና ከመንፈሱ ጋር በማዋሃድ ላልተማረውና ለታዳጊው ትውልድ አርአያ በመሆን ህብረተሰቡ
በአንድነት ተነስቶ ታሪክን እንዲሰራ ያደርገዋል። አለኝታው በመሆን ከእርስ በእርስ ሽኩቻና ከማያሰፈልጉ
ግብግቦች በመቆጠብ ተግባሩን በሙሉ ወደ ስራና ወደ ጥበብ እንዲያዘነብል በማድረግ አገሩን በጸና
መሰረት ላይ እንዲገነባ መንገዱን ያሳየዋል። ባጭሩ የተማረ ሰው ላልተማረው ብርሃን ነው። ከጨለማ
የሚያወጣው፣ ከማያስፈልጉ ድርጊቶች እንዲቆጠብ የሚያደረገውና፣ ችግሮች ሲፈጠሩ በውይይት
መፍታት እንደሚችል ትክክለኛውን መንገድ ያሳያል ተብሎ ይገመታል።

በመሆኑም የተማረ ሰው ይጠይቃል፣ ያወጣል፣ ያወርዳል፣ ወደ ውስጥ ጭንቅላቱን ያያል፤ ወደ


ውጭ ደግሞ የነገሮችን መተሳሰርና መደጋገፍ ይመለከታል። አንዱ ካለሌላው መኖር እንደማይችል
በመረዳትና፣ ይህም የተፈጥሮ ህግ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ በማስቀመጥ ታሪክን በመስራት ለመጭው
ትውልድ ያስተላልፋል። በሌላ ወገን ግን የአንድ ሰው አርቆ የማሰብና ያለማሰብ፣ ታሪክን የመስራትና
ያለመስራት ጉዳይ በተለያዩ ነገሮች የሚወሰን ነው። በአንድ አገር ውስጥ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ
የተለመዱ አሰራሮች፣ አብዛኛውን ጊዜ እንደባህል የሚወሰዱ አነጋገሮችና አሰራሮች፣ እንዲሁም
ህብረተሰብአዊ ግኑኝነቶችና በምድር ላይ የሚታዩ የተዘበራረቁ ነገሮች፣ የአንድን ሰው የማሰብና
ያለማሰብ ኃይል ሊወስኑ ይችላሉ። ከዚህም ባሻገር አንድ ሰው ትምህርትቤት ውስጥ የሚቀስመው
ትምህርት የጭንቅላቱን መዳበርና አለመዳበር ይወስናሉ። የአንድ ሰው ንቅታ-ህሊና የዕድገት ደረጃዎች
ያሉት ሲሆን፣ የንቃተ ህሊናውም ማደግ በሚያደርገው ጥረት የሚወሰን ነው። ሰውነታችን
ለመንቀሳቀስና ለመስራት፣ እንዲሁም ከባድ ነገሮችን ለማንሳት ልምምድ እንደሚያስፈልገው ሁሉ
ጭንቅላትም እንዲዚሁ ጂምናስቲክ ያስፈልገዋል። ለአዕምሮ መዳበር አስፈላጊው ነገር ከትክክለኛው
ዕውቀት ጋር መተዋወቅ ሲሆን፣ በተጨማሪም የማያቋርጥ ጥያቄ መጠየቅና ጭንቅላትን ለጥሩ ነገር
ማዘጋጀትና በየጊዜው የሳይንስ፣ የፍልስፍናና ልዩ ልዩ ስነ-ጽሁፎችን ማንበብ የማሰብ አድማስን ያሰፋል።
ቡድናዊ ስሜትንና ወገናዊንትን ያስወግዳል። ማንኛው ሰው በአምላክ ምስል የተፈጠረ መሆኑን ግንዛቤ
ውስጥ ያስገባል።

ከዚህ ስንነሳ አንዳንድ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ታሪክንና የህብረተሰብን ዕድገት በደንብ


ሳያገናዝቡ የሚያናፍሷቸው አሉባልታዎች ተፈጥሮአዊ ወይንም አንድ ሰው ሲወለድ ይዞት የሚመጣው
አይደለም። የችግሮቹ ምንጭ ጭንቅላት በሚገባ ስላልዳበረና አንድን ነገር ከሁሉም አቅጣጫ የማየት
ኃይሉ በጣም ደካማ ስለሆነ ብቻ ነው። በተጨማሪም የጥቂት ብሄረሰቦችና የአንዳንድ ግልሰቦችም ችግር
አይደለም። ስለሆነም እንደነዚህ ዐይነት ሰዎችም ሆነ ቡድኖች በንቃተ-ህሊና ማነስ ተግባራዊ የሆኑ
ፖሊሲዎችንና ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን አንድን ብሄረሰብ ለመጉዳት እንደተወሰደ እርምጃ በመቁጠር
ተጨማሪ ህብረተሰብአዊ ቅራኔ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። እንደነዚህ ዐይነት ግልሰቦችም ሆነ ቡድኖች ደግሞ
በውጭ ኃይሎች በመደገፍ ቅራኔው እንዲባባስ ያደርጋሉ። የውጭ ኃይሎችም ዋና ዓላማ አንድ ህዝብ
የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት እንዳይሆንና የተረጋጋ ማህበረሰብ እንዳይገነባ ለማድረግ ስለሆነ
እንደነዚህ ዐይነት ግለሰቦችን በጥቅም በመግዛት የርስ በርሱ ሽኩቻው እንዲጧጧፍ የማይፈነቅሉት
ዲንጋይ የለም። በዚህ መልክ አርቀው ማሰብ የማይችሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ወጣቱንና ለውጥ መጣ
ብሉ የሚደናበረውን ኃይል በመቀስቀስ አንድን አገር የታሪክ መስሪያ መድረክ ከማድረግ ይልቅ ወደ ጦር
አውድማነት ይለውጡታል።

ወደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ ትልቁ ችግራችን የህብረተሰብአችንን ታሪክና እንደ


አወዛጋቢ የሚቀርቡትን፣ የሚሰነዘሩትን ጥያቄዎችና ሃሳቦች በሳይንስና በፍልስፍና መነጽር ለማየት ጥረት
አለማድረጋችን ነው። በተለይም ባለፉት አርባ ዐመታት የህብረተሰብአችንን ዕድገትና በየጊዜው
የሚከሰቱትን ፖለቲካዊ ችግሮች ለመቃኘት ከሚያስችሉን ሳይንሳዊ መሰረተ-ሃሳቦች ጋር ለመተዋወቅ
ጥረት ባለማድረጋችን ታሪካችንን እንደፈለገን እንተረጉመዋለን። አብዛዎቻችን ፖለቲካ የሚባለውን
መሰረተ-ሃሳብ ከሌሎች ለአገር ግንባታ ከሚያስፈልጉ ዕውቀቶች ነጥለን በማውጣት አስተሳሰባችን
በተወሰነ ክልል ብቻ እንዲሽከረከር ለማድረግ በቅተናል። ፖሊቲካ ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት የሚሰራበት
መሳሪያ መሆኑን ካለመገንዘብ የተነሳ ኃይላችንን በማያስፈልጉ ነገሮች ላይ አባክነናል። ንቃተ-ህሊናችንን
በማዳበር የህብረተሰብአችንን ችግሮች በሙሉ ከሁሉም አቅጣጫ በመመርመር በዚህ ዘዴና በልዩ ዐይነት
ሳይንሳዊ መሳሪያ ልንፈታው እንችላለን የሚል ሃሳብ ለማቅረብ አልቻልንም። በተወሰኑ መፈክሮችና
ከታሪክና ከህብረተሰብ ህግ ጋር ሊጣጣም የማይችል በወገናዊነት ላይ ያተኮረ ትግል የሚሉትን ፈሊጥ፣
ግን ደግሞ ርዕዩና ሳይንሳዊ መሰርቱ የማይታውቅ በማካሄድና ስልጣንን ለመያዝ በመቻኮል
የተወሳሰበውን የህብረተሰብአችንን ችግር ልንፈታ የምንችል መስሎን ዓለምን አዳርሰናል። የብዙ
አገሮችን መዝጊያዎች በማንኳኳት ድረሱልን እያልን እርስ በእርስ ግብግብ ውስጥ ገብተናል። ስለሆነም
ከአስመራ እስከካይሮ፣ ከካርቱም እስከ ሪያድና ከዚያም እስከዋሽንገተንና ለንደን ድረስ በማምራት ችግሩ
ውስብስ እንዲሆን አድርገናል። የውጭ ኃይሎች ለነፃነታችን የቆሙ ስለመሰለን እንዲከፋፍሉንና
በጥርጣሬ ዐይን እንድንተያይ መንገዱን አመቻችትን ሰጥተናችዋል። በዚህ ዐይነቱ ጠባብ አመለካከትና
የህብረተሰብን ጥያቄዎች በሚመለከቱ መሰረታዊ ነገሮች ላይ ከመወያየት፣ ከመከራከርና አብሮ
በማጥናትና አንድ የጋራ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ መፈክሮችንና የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን በመሰንዘር
በተለይም የተወሰነውን ወጣት ማሳሳታችን ብቻ ሳይሆን ጠቅላላው ህዝባችን ግራ እንዲጋባ ለማድረግ
በቅተናል። እንደሰውና እንደማህበረሰብ ተስማምቶ እንዳይኖርና ታሪክን እንዳይሰራ ለማድረግ
በቅተናል።

ቀደም ብሎም ሆነ ዛሬ በመሀከላችን ያለው ችግር አንድ ዐይነት አመለካከት ወይም ፍልስፍና
ይዘን ለመታገል አለመቻላችን ነው። ከአርባ ዐመት በላይ የፈጀ መላቅጥ የሌለው ትግል በኋላ ዛሬም
እንደትላንትናው ጭንቅላታችን ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ለማየት አለመቻልና ሎጂካል በሆነ መንገድ
የአገራችንን የተወሳሰቡ ችግሮች ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ለማየት አለመቻል ነው። ለዚህ ሁሉ ችግር ደግሞ
ትግል የሚባለውን ዘዴ የጠነሰሱት ሰዎች አሁንም በህይወት መኖራቸውና
„የየድርጅቶቻቸው“ አመራር እንደ ግል ሀብታቸው መቆጣጠራቸው ነው። እንደሚታወቀው ባለፉት
አርባ ዐመታት ብዙ አገሮች በሳይንስና በቴክኖሎጂ ቀድመው ሄደዋል። ለዚህ ዐይነቱ መሰረታዊ ለውጥ
ደግሞ ዋናው መሰረቱ የአመራር ለውጥ መካሄዱ ብቻ ሳይሆን፣ የአስተሳሰብና የአሰራር ለውጥም
በመደረጉ ነው። በተጨማሪም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን የግዴታ በአዲስ ዕውቀትም
በመመራት ነው። ወደ እኛ አገር ስንመጣ ግን ድርጅት አለን የሚሉ መሪዎች የአስተሳሰብ ለውጥ ማካሄድ
አለማቻላቸው ብቻ ሳይሆን፣ ለምን ዐይነት ህብረተሰብም እንደሚታገሉም በግልጽ ቋንቋ ለማስቀመጥ
አለማቻላቸውና አለማወቃቸው ነው። ግልጽነት እስከሌለ ድረስና ጠብመንጃን አስቀምጦ ወደ ውጭ
በመውጣት ህብረተሰብአችንን በሚመለከቱ ነገሮች ላይ ክርክርና ጥናት ለማድረግ ዝግጁነት
እስከሌለ ድረስ ያሉንን ችግሮች ከማባባስ በስተቀር የምናመጣው ፋይዳ የለም።

ችግርን ከመፍጠር ወደ መፍታት መሸጋገር !


ያለፉትን አርባ ዓመታት በፖለቲካ ዙሪያ የተደረገውን ትግል የሚባለውን ነገር በምንቃኝበት ጊዜ
ታሪካችን የጦርነት ታሪክ ነው ማለት ይቻላል። የምናድረገው ትግል ለፖለቲካ ነፃነት ነው ቢባልም እንደዚህ
ዐይነቱ በጦርነት ላይ ያመዘነና በማቸነፍና በመሸነፍ ላይ ያተኮረ ትግል ከፖለቲካ ጋር ምንም
የሚያገናኘው ነገር የለም። በታሪክ እንደተረጋገጠው በስልጣን ላይ ያለን አንድን ጨቋኝ አገዛዝ ለመጣል
ተብሎ የሚደረግ የርስ በርስ ጦርነት በፍጹም ነፃነትን አያቀዳጅም። በጦርነት ትግል ላይ የሚሰማሩ
ድርጅቶች ጭንቅላታቸው እንዳለ በጦርነት መንፈስ ስለሚሸፈን ሳያውቁት በግድ አምባገነናዊ ባህርይን
ይለምዳሉ። በድርጅታቸው ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ክርክሮች፣ ሂሲና ግለስሂስ፣ እንዲሁም ዕውቀትን
ያዘሉና ለአንድ አገር ግንባታ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ እንደፍልስፍና፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የመሳሰሉት ቦታ
ስለማይሰጣቸው ድልን ከተቀዳጁ በኋላ የአንድን አገር የተወሳሰበ ችግር ለመፍታት አይችሉም። ስልጣን
ላይ በሚወጡበት ጊዜ አገርን አፍራሽ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተልና ራሳቸውን በማበልጸግ ሰፊውን
ህዝብ ደግሞ ወደ ድህነት ዓለም ውስጥ ገፍትረው በመጣል እንዲሰቃይ ያደርጉታል። ይህን ዐይነቱን
ሁኔታ ከሞዛምቢክ እስከ ዝምባብዌ፣ ከአንጎላና እስከ ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም እስከ ኤርትራ ድረስ
ያየነውና የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። በሌላ ወገን ግን ሞዛምቢክና ዝምባብዌ እንዲሁም አንጎላና ደቡብ
አፍሪካ ከቅኝ አገዛዝ ለመላቀቅ የተደረጉት የጦርነት ትግሎች ትክክል ናቸው።

በመሆኑም የፖለቲካ ትግል በፍልስፍና፣ በሳይንስና በቲዎሪ እስካልተደገፈ ድረስና፣ በአንድ


ድርጅት ውስጥም ሆነ በተለያዩ ድርጅቶች መሀከል ዲሞክራሲያዊ ውይይትና ክርክር እስካልተካሄደ ድረስ
አንድ ህዝብም ሆነ አንድ ብሄረሰብ በምንም ዐይነት ዕውነተኛ ነፃነታቸውን ሊቀዳጁ በፍጹም አይችሉም።
በፍልስፍና የተደገፈ ወይም ፍልስፍናን መሰረቱ ያደረገ የፖለቲካ ትግል የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ
የሚመለከት ሳይሆን በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን ጠቅላላውን ህዝብ የሚመለከት ጉዳይ እንደመሆኑ
መጠን የመጨረሻ መጨረሻ ዕውነተኛ ነፃነትን የማቀዳጀት ኃይሉ ከፍ ያለ ነው። ይህም ማለት አንድ
ህዝብ ከየት እንደመጣ፣ ለምን በዚህች ዓለም እንደሚኖርና ወዴትስ እንደሚያመራ እንዲገነዘብ
ስለሚያደርገው አመለካከቱን በአንድ ክልል ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ሁሉንም እንደወንድሙና እንደእህቱ
በመመልከት በአንድነት በመነሳሳት ታሪክን ለመስራት ያስችለዋል።

ከዚህ ስንነሳ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እስከዛሬ ድረስ አገራችንና ህዝባችን ችግሮችን


እንዲያስተናግዱ አድርገናል። ሀዝባችን አርባ ዐመት ያህል እፎይ ብሎ የኖረበት ጊዜ የለም። ሁሉም
በየፊናው ታጋይ ነኝ በማለት ህዝባችንን ሲያዋክብና ግራ ሲያጋባ ነበር፤ ዛሬም ግራ እያጋባ ነው። አንዳንድ
አገሮች በሰላሳና በአርባ ዐመታት ውስጥ የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን ወደ ኃያል መንግስትነት ሲያመሩ፣
እኛ ግን አሁንም እንደትላንትናው መንፈሳችንን በማዋከብና ለጦርነት በመዘጋጀት ወደ መተላለቅና
አገርን ወደ መበታተን እያመራን ነው። ስልጣን ላይ ለመውጣት የሚደረገው ትግል ደግሞ ብሄራዊ
ነፃነታችንን ከሚቀናቀኑና እንድንበታተን ከሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበርና ከእነሱ ድጋፍ
በማግኘት ነው። ሳናውቀው የራሳችንን መቃብር እየቆፈርን ነው። ነፃ እናወጣዋለን የምንለውንም ህዝብ
የመጨረሻ መጨረሻ ተበታትኖ እንዲቀር መንገዱን ሁሉ እያዘጋጀን ለመሆናችን በፍጹም የሚታየን
አይመስልም።

ስለሆነም ከዚህ ዐይነቱ ራስንና አገርን፣ እንዲሁም ባህልንና ታሪክን ከሚያወድም አካሄድና
የጦርነት ትግል ተቆጥበን ወደ ገንቢ አስተያየት መምጣቱ ታሪካዊ ግዴታ ነው። የምንፈልገውንም ነገር
በግልጽ ማስቀመጡ መፍትሄ ለመፈለግ ያመቻል። በተጨማሪም ስልጣን ከተያዘስ በኋላ አፍጠው
አግጠው የሚታዩትን ድህነትን፣ የንጹህ ውሃ ማግኘትን፣ የቤት ችግርን መቅረፍ፣ ህክምናን የማግኘት
ጉዳይና፣ ሌሎች መሰረታዊ ነገሮችን በመፍታት እንዴት አድርገን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረት
ማህበረሰብ እንደምንገነባ ማሳየት መቻል አለብን። ይህንን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው ለነፃነት
የሚደረገው ትግል መልክ የሚይዘው። ሃሳባችንን ግልጽ ሳናደርግና ለመወያየት ዝግጁ ሳንሆን
የምናደርገው መሯሯጥ ኃይልን ማባከኑ ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ህዝብ ረጋ ብሎ እንዳይሰራ ያግዳል።
እንደሚታወቀው አንድ ህዝብ በስራ አማካይነት ብቻ ነው ብሄራዊ ሀብት ሊፈጥርና ተደስቶ ለመኖር
የሚችለው። አንድ ህዝብ ከፍርሃትና ከጦርነት መንፈስ መላቀቅ ሲችል ብቻ ነው ዕውነተኛ ነፃነትንና
ሁለንታዊ ዕድገትን ሊቀዳጅ የሚችለው። ስለሆነም ተማርን የምንልና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን የምናነሳና
ማብራሪያም ለመስጠት የምንሞክር ሁሉ የአገራችንን የተወሳሰቡ ችግሮችና የተደቀነብንን አደገኛ ሁኔታ
ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ታሪካዊ ግዴታችን መወጣት አለብን። መልካም ግንዛቤ !
fekadubekele@gmx.de

አንድ አገር ሊወድቅና ሊነሳ የሚችለው፣ ወይም ደሃና


ጠንካራ አገር
የሚሆነው መንግስት ተግባራዊ በሚያደርገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ
አማካይነት ነው !!

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

ጥቅምት 02 ፣ 2011

Human dignity is offended when persons are denied the opportunity to participate in their
own development, when development “takes place over their heads.”( Yuengert M.
Andrew, What is “Sustainabel Prosperity for all” in the Catholic Social Tradition ?
in: The True Wealth of Nations- Catholic Social Thought and Economic Life.(Oxford,
2010)

መግቢያ
አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ነፃነትን ከተቀዳጁ ከሃምሳ ዓመት በኋላ በድህነት ዓለምና በጥገኝነት ውስጥ
የሚገኙ ናቸው። በአብዛኛዎቹ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የተትረፈረፈ የጥሬ ሀብትና
እንዲሁም ለነዳጅ የሚሆን ዘይትና ጋዝ ቢኖርም ህዝቦቻቸው በድህነት ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ናቸው።
መሬታቸው በጣም ለምለም የሆኑና ብዙ ውሃ ቢኖራቸውም ገበሬዎቹ ከእጅ ወደ አፍ በሚሆን የእርሻ
ምርት ላይ የተሰማሩ ናቸው። በዚህም ምክንያት የተነሳ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ከውጭ ስንዴና
ሌሎች ለምግብ የሚሆኑ የእርሻ ውጤቶችን ያስመጣሉ። ወደ ደቡቡ የአፍሪካ ክፍል ስንሄድ ደግሞ
በአብዛኛዎቹ አገሮች ውስጥ፣ ሞዛምቢክ፣ አንጎላ፣ ዚምባብዌና ደቡብ አፍሪካ ዋናው ምግባቸው በቆሎ
ነው። መሬታቸው፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላና ዘንጋዳ፣ እንዲሁም ሌሎች ሰብሎችንና ጥራጥሬዎችን
አያበቅሉ ይመስል ህዝቦቹ በቆሎን ብቻ በማምርትና ዋናው ምግባቸው በማድረግ የተመጣጠነ
ምግብ(Diet) እንዳያገኙ ሆነዋል። በተለይም የቅኝ ገዢዎች የእነዚህን አገሮች የአስተራረስና የአመጋገብ
ዘዴ በማበላሸትና፣ መሬቱ በቆሎና ትምባሆ ብቻ እንዲያመርት በመደረጉ መሰረታዊ የእርሻ ባህል
እንዳይስፋፋ ሆኗል። በዚህም ምክንያት የተነሳ አብዛኛው ህዝብ ዕውነተኛ የሆነ የአስተራረስ ባህል
እንዳያዳብርና የተመጣጠነ የምግብ ዐይነት እንዳያገኝ ተደርጓል።

Videos From Around The World አብዛኛዎቹ


የአፍሪካ አገሮች የፖለቲካ ነፃነትን ከተቀዳጁ እ.አ ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ የገበያ ኢኮኖሚ የሚባለውን ፖሊሲ
በተከታታይ ተግባራዊ ቢያደርጉም ሰፋ ያለ በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረተና፣ እርስ በእርሱ ወደ ተያያዘና
ግልጽ ወደ ሆነ የገበያ ኢኮኖሚ ሊሸጋገሩ አልቻሉም። ሁሉም የአፍሪካ አገሮች፣ ኢትዮጵያንም ጨምሮ
በመጀመሪያ ደረጃ የምትክ ኢንዱስትሪ ፖሊሲ፣ (Import Substitution Industrialization) የሚባለውን፣
ቀጥሎ ደግሞ „መሰረታዊ ፍላጎቶችን የሚያሟላ“ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣(Basic Needs Economic
Policy)ከዚያ በኋላ የተቅዋም ማስተካከያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ(Structural Adjustment Economic
Policy) ተግባራዊ ቢያደርጉም ከድህነትና ከልመና ሊላቀቁ በፍጹም አልቻሉም። ተግባራዊ
የሚያደርጓቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ በዕዳ የሚተበትቧቸው፣ የንግድ ሚዛናቸውን
የሚያዛቡባቸው፣ በአንድ ወይም በሁለት የጥሬ ሀብት ብቻ እንዲመኩ የሚያደርጓቸው፣ በተጨማሪም
ወደ ውስጥ የማምረት ኃይላቸውን የሚያዳክሙና፣ በዚህም የተነሳ ከሰፊው ህዝብ ጋር የማይመጣጠን
የፍጆታ አጠቃቀም እንዲስፋፋ በማድረግ አሁንም ቢሆን ህዝቦቻቸው ሰፋ ባለና አስተማማኝ በሆነ
የኢኮኖሚ መሰረት ላይ እንዳይመረኮዙ ተደርገዋል።

በአንዳንዶች፣ በተለይም ክስተታዊ(Empiricist) የፖለቲካ አመለካከት ካላቸውና፣ የኒዎ-ክላሲካልንና


የኒዎ-ሊበራልን ርዕዮተ-ዓለምን በሚያራምዱ ተንታኞች ዕምነት ለዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ቀውስና አገሮች
መዝረክረክና ሀብት መባከን ዋናው ምክንያት አምባገነናዊ አገዛዞች ስልጣን በመያዛቸው ነው።
ከአገራቸውና ከህዝባቸው ይልቅ የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ጥቅም ያስቀድማሉ የሚል ቀላል
ምክንያት ይሰጣሉ። የአፍሪካን አገሮች የተወሳሰቡ ችግሮች በዚህ ዐይነቱ ሳይንሰ-አልባ አቀራረብ መረዳት
በፍጹም አይቻልም። የችግሩን ጥልቀትና ውስብስብነት መረዳት የሚቻለው ከህብረተሰብ አገነባብ
ታሪክ፣ ከንቃተ-ህሊና መዳበርና አወቃቀር ጋር የተያያዘና፣ በተለይም ደግሞ የውጭ ኃይሎች በተለያዩ
የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የተጫወቱትን አሉታዊ ሚናና እስካሁን ድረስ ተግባራዊ የሆኑትን የኢኮኖሚ
ፖሊሲዎች ከቁጥር ውስጥ ያስገባን እንደሆን ብቻ ነው። የሌሎችን የአፍሪካ አገሮችንና የአገራችንን
የህብረተሰብና የኢኮኖሚ ቀውስ ከቀላል ፎርሙላ ባሻገር በማየት ጠለቅ ያለ ሳይንሳዊ ትንተና ለመስጠት
ካልቻልንና መፍትሄም ለመስጠት የማንሞክር እስከሆነ ድረስ በግልጽ የሚታየው ችግር ከመቶና ከሁለት
መቶ ዐመት በኋላም በተመሳሳይ ሁኔታ ወይንም ከዚህ በተበላሽ መልክ ሊገኝ እንደሚችል ማወቁ ብዙም
ሳይንሳዊ ምርምር የሚያስፈልገው አይመስለኝም። ስለሆነም የማንኛውም ምሁር ታሪካዊ፣ ሞራላዊ
ግዴታና ኃላፊነት መሰረታዊ ችግሩንና አነሳሱን በመረዳት የተሟላና ሳይንሳዊ መፍትሄ ለመስጠት
መቃጣት እንጂ፣ ቁንጽል አስተሳሰብን በማስፋፋት ሰፊውን ህዝብና፣ በተለይም ደግሞ ወጣቱን ትውልድ
ማሳሳት መሆን የለበትም። ከዚህ በመነሳት አንዳንድ መሰረታዊ ነገሮችንና የተሳሰቱ ፅንሰ-ሃሳቦችን ግልጽ
ለማድረግ እሞክራለሁ።

ከፖሊሲ በፊት መቅደም ያለበት ጉዳይ !!


በሶሻል ሳይንስ ትምህርት ውስጥ የአንድን ህብረተሰብ የማቴሪያል ሁኔታ፣ የፖለቲካና መንግስታዊ
አወቃቀር፣ የህዝብን የአኗኗር ሁኔታና፣ በአጠቃላይ ሲታይ የኢኮኖሚ አወቃቀርን ጉዳይ (Economic
Structure) ለመመርመርና ለመረዳት የሚያግዙን የዕውቀት መሳሪያዎች አሉ። የመጀመሪያው አንድን
ነገር ወደ ውስጥ ገብቶና በተለያዩ ነገሮች መሀከል ያለውን መተሳሰርና፣ አንደኛው በሌላው ላይ ተፅዕኖ
የሚያደርግ መሆኑን መመርመሪያ መሳሪያ ነው። ስለሆነም የአንድን ነገር ወይም ችግር ዋና ምክንያት
ወይም ምንጭ ወደ ውስጥ ገብቶ ለመርመርና ለመረዳት የሚያስችል ሲሆን፣ በአንደኛው ክፍል ላይ
የሚከሰት ችግር የግዴታ በሌሎች ክፍሎችም ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ወይም ሆኔታዎች እንዲበላሹ
ያደርጋል። ለምሳሌ በአንድ አገር ውስጥ ስልጣንን የጨበጠው ኃይልና መንግስት ንቃተ-
ህሊናው(Consciousness) በጣም ዝቅተኛ ከሆነ የሚመራበትን የህብረተሰብና የኢኮኖሚ ፖሊሲ
ለመረዳት አይችልም። በዚህም ምክንያት የተነሳ የሚያወጣቸውና ተግባራዊ የሚያደርጋቸው
የማህበራዊና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረቱ መሆናቸው ቀርቶ
ህብረተሰቡን በሚያዘባራርቁ የንግድና የአገልግሎት መስኮች ላይ በመረባረብ የአገርን ዕድገት ያዛንፋል፤
ህብረተሰብአዊ ሚዛንም እንዳይኖር ያደርጋል። ይህም ማለት አንድ መንግስት በሳይንስና በፍልስፍና ላይ
የተመሰረተ ፖለቲካ ከሌለው ሌሎች ፖሊሲዎቹ ሁሉ እንደዚሁ ፍልስፍናና ሳይንሰ-አልባ ይሆናሉ ማለት
ነው። በአጭሩ በዚህ የኢኮኖሚ ፍልስፍና መሰረት የአንድ አገር ችግር በተናጠል መታየት ያለበት ሳይሆን
ሁለንታዊ በሆነ መልክ ብቻ ሲሆን፣ አፈታቱም ሁሉኑም ነገር የሚያካትትና በዕውቀት ኃይል ብቻ
የሚፈታ ነው። የንቃተ-ህሊና ጉዳይን ስንመለከት በጭንቅላታችን ውስጥ አንድ ቦታ ላይ የተቀመጠ
ሳይሆን፣ በልምድና፣ አንድ ህብረተሰብ ውስጥ በሚገኙ የማቴሪያል ሁኔታዎችና ባህሎች ሊቀረጽ የሚችል
ሲሆን፣ በተራ የአካዴሚክስ ዕውቀት ሊገኝ እንደማይችል የኳንተም ቲዎሪ፣ የኖይሮ ባዮሎጂስት
ተመራማሪዎችና ፈላስፋዎች ያስረዳሉ። ስለሆነም የንቃተ-ህሊና መዳበርና አለመዳበር የአንድን አገር
በሁሉም አቅጣጫ ማደግና ወደ ኋላ-መቅረት የሚወሰን ጉዳይ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ፣ አንድን ነገር ከውጭው በመመልከት ብቻ መገምገምና መረዳት የሚቻልበት መሳሪያ
ነው። በዚህ ዐይነቱ ፍልስፍና መሰረት የሰው ልጅ ጭንቅላት እንዳልተጻፈበት ነጭ ወረቀት(Tabula Rasa)
ሲሆን፣ አንድ ሰው የሚቀስመው ዕውቀት በምርምር ላይ የተመሰረተና ከሁሉም አቅጣጫ የሚገመግም
ሳይሆን ከውጭ የሚመጣለትን የሚስብ ብቻ ነው። በዚህ ዐይነቱ የዕውቀት ዘርፍ የሰለጠነ ሰው
መጠየቅና መተቸት አይችልም። የተሰጠውን ብቻ ዝም ብሎ በመሸምደድ ተግባራዊ የሚያደርግ በመሆኑ
የአንድን ህብረተሰብ ችግር ዋና ምክንያት ለመመርመር አይችልም። የአንድን ችግር ዋና ምክንያት
ለመረዳት በቁጥር የሚለኩ ነገሮችን ብቻ በመውሰድና ከዚያ በመነሳት በአንድ መስክ የተከሰተውን
ቀውስ መተንተንና መፍትሄም ለመስጠት መጣር አለበት። ይህንን ዐይነት የአሰራር ስልት በሚከተሉ
ምሁራን ዕምነት መሰረት በፖለቲካ፣ በመንግስትና በሌሎች ህብረተሰብአዊና ማህበራዊ ጉዳዮች መሀከል
ግኑኝነት ስለሌለ፣ ለምሳሌ ፖለቲካው በኢኮኖሚውና በማህበራዊ መስክ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር
አይችልም። ስለሆነም መስተካከል ያለበት ጉዳይ የፖለቲካው ጉዳይና መንግስት የሚመራበት ፍልስፍናና
ሳይንስ ሳይሆኑ፣ የኢኮኖሚው ፖሊሲ ብቻ ነው። በአጭሩ ሌሎች ነገሮች እንዳሉ ሆነው ኢኮኖሚው ለገበያ
ተዋንያን ከተተወ ገበያው በሂደት ውስጥ ሚዛናዊ በመሆን በኢኮኖሚ መስክ ላይ የሚታዩ ችግሮች
በሙሉ፣ ለምሳሌ እንደስራ-አጥ ችግሮች በቀላሉ ሊቀረፉ ይችላሉ ይለናል። ወደድንም ጠላንም፣
በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በአጠቃላይ ሲታይ በዓለም አቀፍ ደረጃና በየአገሮች ውስጥ የሚካሄዱት
ትግሎች በእነዚህ ሁለት የሳይንስ ፈለግ ዙሪያ ነው። በተለይም በኢኮኖሚክስ ትምህርት የሰለጠኑ
ምሁራን ሳያውቁት የሁለተኛው ሳይንስ መሰል ሰለባ በመሆን የብዙ አገሮችን ወይም ህብረተሰቦችን
ዕድል ወሳኝ በመሆን ለድህነትና ለአገሮች መዝረክረክ፣ እንዲሁም በውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ስር መውደቅ
ምክንያት ሊሆኑ ችለዋል።

በተለይም በአለፉት አርባ ዐመታት በኢምፕሪሲዝም አመለካከት ላይ የሚመረኮዘው የኒዎ-ሊበራል


የኢኮኖሚ ፖሊሲ በአሸናፊነት ከወጣበት ጊዜ ጀምሮና የሁሉንም አገሮች ዕድል የሚወስን ዓለም አቀፋዊ
አገዛዝ (World Governance) ከተመሰረተ ወዲህ እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉት እጅግ ወደ ኋላ የቀሩ
አገሮች የሚከተሉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሳይንስንና የቴክኖሎጂ ዕድገትን የሚቀናቀነውን የኒዎ-ሊበራል
የኢኮኖሚ ፖሊሲን ነው። በኒዎ-ሊበራል ምሁራን ዕምነት የእያንዳንዱን አገር ችግር ከታሪክ፣ ከባህልና
ከሌሎች ልምዶች አኳያ ማየትና መመርመር አያስፈልግም። የገበያ ኢኮኖሚ ከነዚህ ነገሮች ባሻገር
መታየት ያለበት እንደመሆኑ መጠን፣ በሁሉም አገሮች ውስጥ ተግባራዊ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው።
የገበያ ኢኮኖሚ እንደሂደት የሚታይና ከታች ወደ ላይ እያደገና እየተወሳሰበ የሚመጣና አንድን
ህብረተሰብ የሚያዳርስ ሳይሆን ያለና ዘለዓለማዊነት ያለው ነው። ይህ ዐይነቱ ተራ የገበያ የኢኮኖሚ
ፖሊሲ አመለካከት በየትምህርትቤቱ በመሰጠቱና በዓለም አቀፍ ደረጃም በመስፋፋቱ ወደድንም
ጠላንም ብዙም ሳናወጣና ሳናወርድ ሁላችንም የዚህ ዐይነቱ የተሳሳተ ፖሊሲ ሰለባ በመሆን አገርን ገንቢ
ከመሆን ይልቅ አፍራሽ ለመሆን ችለናል ብል የምሳሳት አይመስለኝም። ከዚህ ባሻገር ዛሬ በዓለም አቀፍ
ደረጃ የተስፋፋው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን የሚያራምዱ ምሁራንና ፖሊሲ አውጭዎች ሌሎች
ተወዳዳሪና ከሱ የተሻሉ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎችና ፖሊሲዎች እንዳሉ በፍጹም ሊቀበሉ አይፈልጉም። በእነሱ
ዕምነት በሌሎች ምሁራን ተጨባጭ ሁኔታዎችን በማንበብ የዳበሩ ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ሊትሬቸሮች
ተቀባይነት የላቸውም። በዚህ መልክ የካቶሊክ ሃይማኖት በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን የበላይነትን
በተጎናጻፈበት ዘመንና ሳይንስንና ፍልስፋናን አጥብቆ እንደተዋጋውና የጨለማውን ዘመን እንዳራዘመው
ሁሉ፣ በአሁኑ ዘመን የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲ አራማጆችም ሌሎች የኢኮኖሚ ቲዎሪዎችንና
ፖሊሲዎችን አጥብቀው በመዋጋት በዓለም አቀፍ ደረጃ ድህነትና ድንቁርና እንዲሰፋፋ እያደረጉ ነው።
የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም የአፍሪካ አገሮች አገዛዞች የኒዎ-ሊበራልን የኢኮኖሚ ፖሊሲ
ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጫና በማድረግ ወደ ውስጥ ያልተስተካከለ ዕድገት እንዲፈጠርና ሀብት ወደ ወጭ
እንዲወጣ በማድረግ ሰላም እንዳይሰፈን ምክንያት ሊሆኑ ችለዋል።

ያም ተባለ ይህ አንዳች ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ በአንድ አገር የኢኮኖሚ
አወቃቀር ላይ፣ በማህበራዊና በባህላዊ ጉዳዮች ላይና፣ እንዲሁም በአካባቢና በፖለቲካ ላይ ተፅዕኖ
ማሳደሩ የማይቀር ጉዳይ ነው። እንደ ፖሊሲው ዐይነት አንዱ የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ሲሆን፣ ሌላው
ደግሞ ሊጎዳ ይችላል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ማህበራዊ ውዝግቦች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ማንኛውም
የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ የአንድን ህብረተሰብ ችግር ለመቅረፍ ተብሎ መነደፍ ያለበት በመሆኑ
የቀውሱን ምክንያት ከሁሉም አቅጣጫ መመርመር ያስፈልጋል። የቀውሱን ወይም የበሽታውን ዋና
ምክንያት በበቂው ሳይመረምሩ የሚወጡና ተግባራዊ የሚሆኑ ፖሊሲዎች ለችግሩ መፍትሄ ከመሆን
ይልቅ ጥልቀት በመስጠት እንዳይፈታ ያደርጉታል። በሌላ ወገን ደግሞ ከውጭ የሚመጣን ፖሊሲ
በጭፍኑ ተግባራዊ የሚያደርጉ መንግስታት ተስፋ የሚያደርጉት ነገር አለ። ይኸውም ኢኮኖሚውን
በማሳደግ እንደስራ-አጥ የመሳሰሉትን ችግሮች ለመቅረፍ እንችላለን ብለው ያምናሉ ወይም ይገምታሉ።
እስካሁን ድረስ እንደተረጋገጠው ይህ ዐይነቱ የየመንግስታቱ ተስፋ ከዕድገት ይልቅ ወደ ተወሳሰበ ችግርና
ወደ ጥገኝነት እንደከተታቸው እንመለከታለን። በአለፉት ሰላሳና አርባ ዐመታት የተለያየ ስም
እየተሰጣቸው በአፍሪካ ምድር ውስጥ ተግባራዊ የሆኑትን የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ስንመለከትና በምድር
ላይ ያለውንም ተጨባጭ ሁኔታ ስንመረምር አንድም የአፍሪካ አገር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ
የተመሰረተ ሰፋ ያለ ገበያ እንዳልገነባ እንመለከታለን። በኢኮኖሚ ፖሊሲ ውስጥ ያለውን አወዛጋቢ ሁኔታ
ለመረዳት በንፅፅር(Analagoy) መልክ እያወዳደሩ መመልከቱ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን
አወዛጋቢነት እንድንገነዘብ ይጠቅመናል።

አንድ ሰው አሞት ሃኪም ቤት ሲሄድ አንድ ተስፋ የሚያደርገው ነገር አለ። ይኸውም ሃኪሙ ከበሽታዬ
ይፈውሰኛል ብሎ በማሰብ ወይም በመገመት ነው። ሃኪሙም በሽተኛውን በሚገባ ሳይመረምር ዝም
ብሎ መድሃኒት አያዝለትም ወይም ህክምና አያደርግለትም። መድሃኒት ከማዘዙ በፊት ምን
እንዳመመውና የትስ ቦታ ላይና ከመቼ ጀምሮ በሽታ እንደሚሰማው ይጠይቀዋል። ከዚያ በኋላ በዝርዝር
የህይወት ታሪኩንና፣ ከአባቱም ሆነ ከእናቱ የወረሰው በሽታ እንዳለ ይጠይቀዋል። ቀጥሎም በልጅነቱ
በበሽታ ይጠቃ አይጠቃ እንደነበር፣ አሞት ከነበረ የበሽታውን ዐይነት ለማወቅ ይፈልጋል። በተጨማሪም
በጊዜው ምን ዐይነት ህክምና እንደተደረገለትና፣ ከበሽታው ተፈውሶ እንደሆነ ለመስማት
ይሻል። በመቀጠልም ስለአኗኗሩ፣ ስለ አመጋገቡና፣ አልክሆል ይጠጣ አይጠጣ እንደሆነ ወይም ደግሞ
ሲጋራ ያጨስ አያጨስ እንደሆን ይጠይቀዋል። ከዚህም ባሻገር ስፖርት ይሰራ ወይም አይሰራ እንደሆን
ጥያቄ ያቀርብለታል። በዚህ መልክ በዝርዝር ከጠየቀ በኋላ በመሳሪያው ይመረምረዋል። እንደ
አስፈላጊነቱና እንደበሽታው ዐይነት የሰገራ፣ የሽንትና የደም ምርመራ ያደርጋል። ይህንን ሁሉ አድርጎ
በሽታው ከሱ አቅም በላይ ከሆነ ወደ ሌላ ስፔሺያሊስት ጋ ይልከዋል። በዚህ መልክ ብቻ ነው አንድ ሀኪም
ወይም ሀኪሞች ለበሽተኛው አስፈላጊውን ህክምና የሚያደርጉለት።

ወደ አንድ አገር ወይም ህብረተሰብ ሁኔታ ስንመጣም አንዳች ዐይነት ፖሊሲ ከመውጣቱ ወይም
እንደመፍትሄ ከመቅረቡ በፊት የሚመለከተው አገር ኢኮኖሚያዊና ህብረተሰብአዊ አወቃቀር መሰረታዊ
በሆነ መልክ መመርመር አለበት። በተጨማሪም ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ወይም የተደራጁ የሙያ
ማህበሮች ጋር በበቂው መወያየትና መከራከር ያስፈልጋል። ሁሉም ተዋንያን ኃይሎች ተመሳሳይ ግንዛቤ
እንዳላቸው ለማወቅም ሆነ ለመረዳት የፖለቲካው አወቃቀር፣ የመንግስታዊ መኪና አወቃቀር፣ የሀብት
ይዞታና የሀብት ክፍፍል ጉዳይ፣ የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔና በዚህ ውስጥ የሚሳተፉ በየደረጃው ያሉ
የኢኮኖሚ ተዋንያን ሁኔታና ችሎታ፣ እንዲሁም የዕውቀት ጉዳይ፣ የኢኮኖሚው መሰረት፣ ማለትም
ቴክኖሎጂያዊና የኢንዱስትሪ ጉዳይ ወይም የእርሻ መስኩ ጉዳይ፣ በየመስኩ ተሰማርቶ የሚሰራው የሰው
ኃይል ጉዳይ፣ በአንድ አገር ውስጥ ያለው የኢንዱስትሪዎች ዐይነትና ስርጭት፣ በከተማና በገጠር ያለው
ሁኔታ፣ .... ወዘተ. ለምርምርና ለውይይት እንዲሁም ለክርክር መቅረብ አለባቸው። ከዚህም ባሻገር
የህዝቡ አኗኗር፣ ማለትም የቤት አሰራር ጉዳይ፣ የከተማዎችና የመንደሮች አገነባብ ጉዳይ፣ የቆሻሻ ፍሳሽና
የጽዳት ጉዳይ፣ እነዚህ ሁሉ መጠናትና በደንብ መመርመር አለባቸው። ምክንያቱም ማንኛውም
የኢኮኖሚ ፖሊሲና እንቅስቃሴ ከሰው ህይወት ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ መጠንና፣ በቦታና በጊዜ(Space
and Time) ውስጥ የሚካሄድ እንደመሆኑ መጠን አንድ አገር ለኢንዱስትሪ ተከላና ለሌሎች የኢኮኖሚ
እንቅስቃሴዎች የሚያመች የከተማ አገነባብና የመገናኛና የመመላለሻ አወቃቀሮች ይኖራት አይኖራት
እንደሆን በሰፊው መጠናት አለበት። ከዚህም ባሻገር ጠለቅና የተወሳሰበ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ
የሚታይ ከሆነና አብዛኛው ህዝብ በድህነት የሚኖር ከሆነ በየጊዜው ተግባራዊ የሚደረጉት የኢኮኖሚ
ፖሊሲዎች ለምን ህብረተሰብአዊ ሀብት ሊፈጥሩ አልቻሉም? ድህነትን ለመቅረፍ አልቻሉም? ሰፋ ያለ
የስራ መስክም ሊከፍቱ አልቻሉም? ብሎ መጠየቅና በቂ ምርምር ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ከመሆኑ
በፊት ዝም ብሎ በጭፍን ተግባራዊ የሚሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲ አንድን አገር ሊወጣው የማይችለው
ቀውስ ውስጥ ነው የሚከተው።

ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ መንግስት ተግባራዊ የሚያደርገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በምድር ላይ ከሚታየው


ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ሊጣጣም የሚችልና፣ ተግባራዊ በሚሆንበትም ጊዜ ሊያስከትል የሚችለውን
አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ውጤት በሚገባ መጠናት አለበት። ይህንንም በንፅፅር(Analagoy)
እንመልከተው። ለምሳሌ አንድ መሬት ላይ አንድ ዘር ከመዝራታችን በፊት መሬቱ ያንን የዘር ዐይነት
ይቀበል አይቀበል፣ አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ-ነገሮች ይኑሩት አይኑሩት በሚገባ መመርመር አለበት። ከዚህም
ባሻገር ዝናብና ፀሀይ በበቂው መገኘት ለአንድ ሰብል ፍሬ ማፍራትና የፍሬው መብዛት ወሳኝ ሚናን
ይጫወታሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን ለአንድ ሰብል ወይም ለተለያዩ ሰብሎች መብቀል የአንድ አገር
መልክዓምድርና የጠቅላላው አየር ሁኔታ እንደዚሁ ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። ለምሳሌ እንደቡናና ሌሎች
የትሮፒካል ፍራፍሬዎች በአውሮፓ ምድር ውስጥ በፍጹም አይበቅሉም። አንድ ሰው ዘሮቹን አምጥቶ
አውሮፓ ውስጥ ልሞክራቸው ቢል በፍጹም ፍሬ ሊያፈሩ አይችሉም። ሊያፈሩ የሚችሉት በልዩ
እንክብካቤ ከፕላስቲክ በተሰራ በሞቃታማ ቤት(Green House) ውስጥ ብቻ ነው። ይህ ዘዴ ደግሞ ብዙ
ምርምርንና ወጪን የሚጠይቅ ስለሆነ ምርትን በብዛት ማምረት በፍጹም አይቻልም።

ይህ ማለት ምን ማለት ነው ? ወደ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ስንተረጉመው በአንድ የበለጸገ የካፒታሊስት አገር


ውስጥ ተግባራዊ የሚሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ በሌላ በሁሉም አቅጣጫ ወደ ኋላ በቀረ አገር ውስጥ
ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ የተስተካከለና ጤናማ የሆነ ዕድገት ከማምጣት ይልቅ ተቃራኒውን ነው
የሚያስከትለው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሁለቱም የተለያየ የህብረተሰብ አወቃቀር፣ የአደረጃጀት ልምድና
ስልት፣ እንደዚሁም ለየት ያለ የህሊና አወቃቀር ስላላቸው በአንድ የካፒታሊስት አገር ሲሰራበት የነበረውን
ፖሊሲ በሌላ አገር ውስጥ በደፈናው ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም። በሁለተኛ ደረጃ፣ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ
አገሮች የሰውንና የተፈጥሮን ሀብት በስነ-ስርዓትና በተቀላጠፈ መልክ በየመስኮቹ እንዲሰማሩ(allocate)
የሚያደርጉና ብቃት ያላቸው ተቋማት የላቸውም። በሶስተኛ ደረጃ፣ በካፒታሊስት የህብረተሰብና
የኢኮኖሚ አገነባብ ታሪክ ውስጥ አብዛኛዎቹ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች እንደዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበና
በቴክኖሎጂ ምጥቀት የሚገለጽ የዕድገት ደረጃ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ተግባራዊ ያደረጉት ፖሊሲ ተራ
የሆነ የገበያ ኢኮኖሚ ወይም የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሳይሆን፣ ሁለ-ገብ(Holistic) የሆነ የአገር ግንባታ
ፖሊሲ ነው ያካሄዱት። በዚህ ዘዴ ነው ቀስ በቀስ ድህነትንና ኋላ-ቀርነትን ሊቀርፉ የቻሉት። ለዚህ ዐይነቱ
ሁለ-ገብ የአገር ግንባታ መሰረት ደግሞ የተፈጥሮ ሳይንስ ግኝት ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል።
እንዲያውም ፖለቲካ ኢኮኖሚክስ እንደ አገር መገንቢያ ፖሊሲ ከመታወቁ በፊት ሳይንሳዊ ግኝቶች፣ የዕደ-
ጥበብ ስራዎችና ከነዚህ ጋር የተያያዘ የንግድ እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም የከተማዎች መገንባትና የሰዎች
ከገጠር ወደ ከተማ ፍሰት ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል።

ይሁንና ግን በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ ተመሳሳይ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተካሄደበት ወቅት
አልነበረም። እንደየዕድገት ደረጃቸው የተለያዩ የአውሮፓ መንግስታት በተለያየ የታሪክ ወቅት
ውስጥ(Historical Epochs) የተለያዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ አድርገዋል። ከፊዚዮክራቲክስ
የኢኮኖሚ ፖሊሲ አንስቶ እስከ መርከንታሊዝም ድረስ፣ በገበያ ኢኮኖሚ ላይ የተመሰረተ፣ ይሁንና ግን
ለካፒታሊዝም ዕድገት የሚያመች የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ቀጥሎ ደግሞ የኒዎ-ክላሲካልና የኒዎ-ሊበራል
የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች፣ ከ1930ዎች ዓመታት፣ በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የኬይኔሲያን
የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግና በመንግስት የሚደገፍ የብድር አሰጣጥ ዘዴ በማስፋፋት
ለካፒታሊዝም ምጥቀት አመቺ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል። በየጊዜው የሚታየው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኃይል
አሰላለፍ በፖሊሲዎችም ላይ የራሱን ጫና ለማድረግ እንደቻለ ከተደረጉት የርዕዮተ-ዓለም ትግሎች
መገንዘብ ይቻላል። የሰራተኛው እንቅስቃሴ ባየለበትና የተገለጸለት ምሁራዊ ኃይል ጎልቶ በወጣበት ዘመን
ህብረተሰብአዊ ውዝግብ እንዳይፈጠር መንግስታት ተግባራዊ ለማድረግ የሚገደዱት የኢኮኖሚ ፖሊሲ
ማህበራዊ ባህርይ አለው። በተቃራኒው የካፒታሊስቶች፣ በተለይም የፋይናንስ ካፒታል ኃይል አይሎ
በሚወጣበትና ከመንግስት መኪና ጋር በሚቆላለፍበት ጊዜ መንግስታት የሚያወጡትና ተግባራዊ
የሚያደርጉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ አብዛኛውን ህዝብ የሚጎዳ ይሆናል። ይህ ዐይነቱ ወደ አንድ ወገን ያደላ
የኢኮኖሚ ፖሊሲ በተለይም ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ በሰፊው
ተግባራዊ ለመሆን ችሏል።

ያም ሆነ ይህ በዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበና የተሳሰረ የአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ መንግስታት በአፍላው
ወቅት ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል። ኢኮኖሚው እያደገ ሲመጣና የስራ-ክፍፍል ሲዳብር
የተከፈተውን ሰፊ ሜዳ በመጠቀም ግለሰቦች የኢኮኖሚ ተዋንያን ለመሆን በቅተዋል። ነገር ግን እነዚህ
የተለያዩ ፖሊሲዎች ተግባራዊ ከመሆናቸው በፊት በተለይም በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ሰፋ ያለና ጠለቅ
ያለ የጭንቅላት ተሃድሶ ተካሂዷል። በመሆኑም በእየአንዳንዱ የታሪክ ወቅት ተግባራዊ የሆኑት የኢኮኖሚ
ፖሊሲዎች በሙሉ የረጅም ጊዜ የምሁራዊ ትግልና ክርክር ውጤቶች ናቸው። በማንኛውም የአውሮፓ
አገር ውስጥ የተለያየ ግንዛቤና አመለካከት ባላቸው ምሁራን ዘንድ ክርክርና የሃሳብ ልውውጥ ሳይደረግ
አንድ ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክት በጭፍን ተነድፎ ተግባራዊ ሆኖ አያውቅም።

ከዚህ ስንነሳ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ከ15ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ፣ በተለይም የፖለቲካ ኢኮኖሚ
መሰረታዊ ጉዳይ ሆኖ መታየት ከጀመረበት ከ18ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ይዋቀር
የነበረው ከህብረ-ብሄርና(Nation-State) ከህብረተሰብ ምስረታ ጋር በመያያዝ ነበር። ሁሉም አገሮች
ከተማዎችንና መንደሮችን፣ መንገዶችንና የባቡር ሃዲድ መመላለሻዎችን ከመገንባታቸውና
ከመስራታቸው በፊት የገበያ ኢኮኖሚ እያሉ በመጮህና በማስተጋባት በጭፍን የተጓዙበት ጊዜ
አልነበረም። ከህብረተሰብ አወቃቀር ጋርና ከህዝብ ደህንነት ጋር የተያያዙ የቤት አሰራሮችና አደጋ
መከላከያዎች፣ እንዲሁም ከፍተኛ የተፈጥሮ አደጋ በሚደርስበት ጊዜ ይህንን በአጭር ጊዜ ውስጥ
ለማስወገድ የሚያስችሉ መሳሪያዎች ማዘጋጀት የኢኮኖሚው አንድ አካል ናቸው። ይህም ማለት
በአውሮፓ የኢኮኖሚ ፖሊስና የህብረተሰብ አገነባብ ታሪክ ውስጥ አንድ ህብረተሰብ ወደ ገበያነት ተቀንሶ
የሚታይ ነገር ሳይሆን በተሟላ መልክ በቴክኖሎጂና በማኑፋክቱር፣ እንዲሁም በሳይንስና ሰፋ ባለ
በተለያየ የባህል ክንዋኔ የሚገለጽ ነው። በተግባር ሲታይ ተማሪዎች ትምህርት ቤት የሚማሩት የማክሮና
የሚክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ቦታ የላቸውም ማለት ነው። በሌላ ወገን ግን ማክሮና ሚክሮ ኢኮኖሚክስ
ካፒታሊዝም ከፍተኛው የዕድገት ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ በ20ኛው ክፍለ-ዘመን የዳበሩና ለትምህርት
የተዘጋጁ መማሪያዎች ናቸው። በመሰረቱ ማክሮና ሚክሮ ኢኮኖሚ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ እንዴት
ከታች ወደ ላይ ቀስ በቀስ እያደገ ሊመጣ እንደቻለና፣ ከአገሮች አልፎ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ሊወስድ
እንደቻለ አይነግሩንም፤ ወይም መተንተኛ የቲዎሪ መሳሪያዎች አይደሉም። ይህ ብቻ ሳይሆን ማክሮና
ሚክሮ ኢኮኖሚ የካፒታሊስት ኢኮኖሚን ውስጣዊ እንቅስቃሴና የሚመራበትን ህግ
አያብራሩም። ይህም ማለት በአብዛኛው የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ባለፉት ስድሳ ዓመታት ተግባራዊ
የሆኑት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ የካፒታሊዝምን ወይም የተሟላ የገበያ ኢኮኖሚን ዕድገት የሚፃረሩ
ናቸው። የአፍሪካ አገሮች እንደ ህብረተሰብና ማህበረሰብ ብቃት ያላቸው ተቋማት(Institutions)
እንዳይገነቡ መንገዱን የዘጉና የሚዘጉ ናቸው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነት
የሚሰማቸውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ልሂቃን ማፍራት አልተቻለም። የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አሳሳችና
ሀብት እንዲወድም ወይም ደግሞ የአንድ አገር ሀብት ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲፈስ በማድረግ ቀስ
በቀስ ከታች ወደ ላይ የሚያድግ(Organic Growth) የኢኮኖሚ ዕድገትና የህብረተሰብ አወቃቀር
እንዳይፈጠር ያደረገና የሚያደርግ ነው። የካፒታሊዝምን ውስጣዊ ህግና ውስጣዊ-ኃይል የሚፃረር ነው።
ማለትም ውድድርና ቴክኖሎጂያዊ ምጥቀቶች የማይታይባቸው፣ ሰፋ ያለ የስራ-ክፍፍል(Division of
Labour) የሌለበት፣ ሰፋና ግልጽ የሆነ ገበያ የማይታይበት፤ (Transparent Market Structure) ስለሆነም
የአንድ አገር ሀብት የሚባክንበትና በተከታታይ የሰው ልጅ ወደ ድህነት የሚገፈተርበት ነው። በዚህም
መልክ በየአገሮች ውስጥ ተግባራዊ የሆኑት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ አብዛኛውን ህዝብ ወደ ድህነት
ሲገፈትሩ፣ ጥቂቶች ደግሞ ሳይሰሩ የናጠጡ ሀብታም ለመሆን በቅተዋል።

ከዚህ ባሻገር በአፍሪካ አገሮች ውስጥ በተጨባጭ የሚታዩት የኢኮኖሚ ቀውሶች ምክንያትና
በካፒታሊዝም ውስጥ አልፈው አልፈው የሚከሰቱት ቀውሶች ምክንያቶቻቸው ይለያያል። በአፍሪካ
አገሮች ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ በተቋም ቀውስ(Structural Crisis) ሲገለጽ፣ በካፒታሊስት
አገሮች ውስጥ አልፎ አልፎ የሚከሰተው ቀውስ ከምርት በብዛት መመረት(Over production) ጋርና፣
የሚመረተው ምርት በቂ ገዢ ካለማግኘት ጋር የሚከሰት ነው። በተጨማሪም አብዛኛው ህዝብ
የተመረተውንና ገበያ ላይ ወጥቶ ለሺያጭ የሚቀርበውን የተለያየ ምርት ለመግዛት
በማይችልበት(Underconsumption) ጊዜ ፋብሪካዎች የምርት ክንውናቸውን ለማቀዝቀዝ ይገደዳሉ። ይህ
በራሱ ደግሞ የሰራተኞችን መባረር ሊያስከትል ይችላል። ከዚህ ባሻገር ግን ከውጭ ንግድ መቀዝቀዝ
ጋር፣ ከጥሬ ሀብት መወደድ ጋር፣ የብድር ወለድ መጨመር፣ እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች ሲደመሩ፣
ለካፒታሊስት ኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪም ለአየር በአየር ንግድ
ሲባል(Speculation) ካፒታል ከተጨባጭ መስኩ (Real Economy) ይልቅ ወደ ፋይናንስ ገበያ ላይ
በሚሽሸበት ጊዜ በተጨባጩ ኢኮኖሚ ላይ ሊውል የሚችል የመዋዕለ-ነዋይ እጥረት ሊከሰት ይችላል።
በዚህም ምክንያት የተነሳ ውስጣዊ የሆነ ቀውስ(Systemic Crisis) ይፈጠራል። ስለሆነም የስራ-አጥ
ቁጥር መጨመር፣ የፋብሪካዎች በምርት ክንውን መቀዝቀዝና፣ የሚመረተው ምርት ገዢ በማጣት
ለቀውሱ ጥልቀት ይሰጡታል። ከዚህ ዐይነቱ ውስጣዊ ቀውስ ለመውጣት መንግስታት ተግባራዊ
ለማድረግ የሚገደዱት ፖሊሲ በተቅዋም ቀውስ ከሚሰቀያው እንደኛው አገር ካለው ኢኮኖሚ በዐይነት
ይለያል። በሌላ ወገን ግን ካፒታሊዝም የዓለምን ገበያ ስለሚቆጣጠር በብዛት የሚመረቱት ምርቶች
በዓለም ገበያ ላይ ስለሚራገፉ፣ በዛሬው ወቅት በአንዳንድ የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ አልፎ አልፎ
የሚከሰተው ቀውስ ከስድሳኛው፣ ከሰባኛውና ከሰማኒያኛው ዓመተ ምህረት ይለያል።

በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በግልጽ የሚታዩት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች ስር
ከሰደደ የተቋም ቀውስ ጋር የተያያዙ ናቸው። ይህ ዐይነቱ የተቋም ቀውስ በድህነት፣ በቆሻሻ መኖሪያ
ቦታዎች፣ በድብቅና ግልጽ በሆነ መልክ የሚገለጽ የስራ-አጥነት፣ በከተማዎች መጨናነቅና በንጹህ ውሃ
እጦት የተነሳ ጎልቶ የሚታይ ነው። ለዚህ ዐይነቱ የተቋም ቀውስ ምክንያቶች፣ 1ኛ) የውስጥ ገበያው
አለመዳበር፣ 2ኛ) የተሳሳተ የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ ማካሄድና፣ በመጀመሪያ ደረጃ በቅደም ተከተል
ተግባራዊ መሆን ያለበትን የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ ግንዛቤ ውስጥ አለማስገባት፣ 3ኛ) ከህዝብ ፍላጎት
ውጭ የሆነ የመዋዕለ- ነዋይ እንቀስቃሴ ማካሄድ፤ በዚህም ምክንያት የተነሳ ለሚመረቱት ምርቶች በቂ
ገዢ (Effective Demand) አለማግኘት፣ 4ኛ) በተለያዩ የኢንዱስትሪ መስኮች ዘንድ መተሳሰር አለመኖር፣
5ኛ) በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ርብርቦሽ አለማድረግ፣ ወይም አንድን ነገር ለመፍጠር መሰረታዊ
የምርምር ስራ(Basic Research) አለማካሄድ፣ 6ኛ) በኢንዱስትሪዎችና በባንክ መሀከል ግኑኝነት
አለመኖር፣ 7ኛ) አብዛኛው ህዝብ ብሄራዊ ሀብት ሊፈጥሩ በማይችሉ መስኮች ላይ
መሰማራት(Subsistence and Informal Sectors)፣ 8ኛ) የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሲባል በአንድ ወይም
በሁለት የጥሬ-ሀብቶች ላይ ብቻ መመካት፤ እነዚህን በፋብሪካ ውስጥ ለፍጆታ በሚያመች መልኩ
ሳይለውጡ ወደ ውጭ መላክ፣ 9ኛ) በደንብ የታቀዱ የመኖሪያና የመገበያያ ቤቶችና ቦታዎች፣ እንዲሁም
ከተማዎችና የመናፈሻ ቦታዎች አለመኖር፣ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው በኢትዮጵያና በተቀሩት የአፍሪካ
አገሮች ውስጥ ጎልተው የሚታዩ የቀውሱ ክስተቶች(Manifestations) ናቸው። በመሆኑም ለዚህ ዐይነቱ
አንድን አገርና ህብረተሰብ የሚገዘግዝና እንደነቀርሳ በሽታ ስር የሰደደ ቀውስ መፍትሄው የኒዎ-ሊበራል
የገንዘብ ኢኮኖሚ ፖሊሲ(Monetary economic policy) ተግባራዊ ማድረግ ሳይሆን፣ እነዚህን የተቋም
ቀውሶች(Structural Crises) ለመፍታት ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚና የአገር ግንባታ ፖሊሲ ማካሄድ ነው።
አንድ አገር እንደ አገርና እንደ ህብረተሰብ ለመኖርና ለተከታታዩ ትውልድ ጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት
ሊጥል የሚችለው በዓለም ማህበረሰብ(International Community) የሚቀርበውን የኒዎ-ሊበራል
የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ሳይሆን ለአንዴም ለመጨረሻ ጊዜ ከዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ
የቫይረስ በሽታ ሲላቀቅ ብቻ ነው።

ከዚህ ዐይነቱ እጅግ አደናጋሪና የተወሳሰበ ሁኔታ ስንነሳ በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች
የተሰራውንና በተደጋጋሚ የሚሰራውን ስህተት እንመልከት። ይህ ዐይነቱ የፖሊሲ ስህተት እንደ ኤይድስ
ዐይነት ቫይረስ በመስፋፋት ብዙ አገሮችን፣ አገራችንንም ጨምሮ በቀላሉ መድሃኒት የማይገኝለት በሽታ
በመሆን ህብረተሰቦችን እያመነመነና እያመሰቃቀለ ነው። ሁሉም ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች
በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበረሰብ፣ በባህል፣ በስነ-ልቦናና በአካባቢ ቀውስ ውስጥ ዘፍቀው በመገኘት
መንግስታትና ልሂቃኑ ወዴት እንደሚያመሩ የሚያውቁ አይመስልም። ታዋቂው የአገራችን የአዕምሮና
የስነ-ልቦና ተመራማሪና ሃኪም የሆነው ዶ/ር ምህረት ደበበ „የተቆለፈበት ቁልፍ“ በሚለው መጽሀፉ
ውስጥ ቁልጭ አድርጎ እንዳስቀመጠው የአፍሪካ ህዝቦችና አመራሮቻቸው፣ አገራችንንም ጨምሮ
በኦቲዝም(Autism) እንዲሰቃዩ ተደርገዋል። በራሳቸው ዓለም ውስጥ የሚኖሩና የሚያደርጉትን
የማያውቁና፣ በህይወታቸውም ዕቅድ የሌላቸው ለመሆን በቅተዋል። በግልጽ የሚታዩ ነገሮችን እንዳያዩ
ተደርገዋል። ጥያቄ እንዳይጠይቁና እንደሰው እንዳያስቡ ታግደዋል። በግልጽ የሚታዩ የተወሳሰቡ
ችግሮችን በተራ የአስተሳሰብ ስሌት(Commonsense) ለመፍታት እንዳይችሉ ተደርገዋል። በዚህም
ምክንያት የተነሳ ድርጅታዊ አሰራር የጎደለበት፣ ለምንና ለማን፣ እንዴትስ እንደሚሰራ የማይታወቅበት
አህጉር በመሆን የሰው ጉልበትና የተፈጥሮ ሀብት እንዲባክኑ ተደርገዋል። በተለይም በኢኮኖሚክስ
የሰለጠነውና ፖሊሲ አውጭ የሆነው የአፍሪካ ልሂቅ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በማበርና የጥቅም ተገዢ
በመሆን አፍሪካን መቀመቅ ውስጥ ከቷታል፤ እየከተታትም ነው። የጥሬ ሀብቷ እንዲዘረፍና ህዝቦቿም
መንደሮቻቸውን እየለቀቁ እንዲሰደዱ በማድረግ ላይ ይገኛል። ከዚህ በመነሳት በየዘመኑ የተሰሩትን
የፖሊሲ ስህተቶች አጠር አጠር ባለ መልኩ እንመልከት።

ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ የተሰሩ የፖሊሲ ስህተቶችና አሉታዊ


ውጤታቸው !
1ኛ) የምትክ ፖሊሲ ጉዳይና ውጤቱ -ለአብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ኢኮኖሚስቶች በ1950 ዓ.ም
መጀመሪያ ላይ በዘመናዊነት ስም(Modernization) በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ
ፖሊሲ ዐይነት የቱን ያህል ግልጽ እንደሆነ የሚታወቅ ነገር የለም። ማለት የሚቻለው ከ1950 መጀመሪያ
ጀምሮ የማኑፋክቸር ተከላ ይካሄድ እንደነበረና፣ ኢኮኖሚውም በቁጥር ሲለካ የተወሰነ ዕድገት እንዳመጣ
ይወሳ ወይም ይጻፍ ነበር። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ የማኑፋክቸር ተከላ ሰፋ ላለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ
መሰረት ሊጥል ይቻል አይቻል፣ ለስራ-ክፍፍል መዳበር ያመች አያመች፣ ለፈጠራ፣ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ
ዕድገት ያመች አያመች፣ ለከተማዎች መገንባት ያመች አያመች እንደሆን... ወዘተ. በዝርዝር የተጠና
ጥናት የለም።

ያም ሆነ ይህ በኢትዮጵያ ምድር ከ1950 ጀምሮ፣ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ደግሞ ከ1960 መጀመሪያ
ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በምትክ የኢንዱስትሪ ተከላ ላይ ያተኮረ ነው። ይኸውም
በዘመናዊነት ስም(Modernization of the American Version) የፍጆታ ዕቃዎችን የሚያመርቱ
ኢንዱስትሪዎችን በተወሰኑ ወይም በተወሰነ ቦታ በመትከል በተለይም የንዑስ ከበርቴውን የህብረተሰብ
ክፍል የፍጆታ አጠቃቀም ማስለመድና „የአሜሪካንን ባህል“ ማስፋፋት ነበር። ስለሆነም እንደኮካኮላና
ፋንታ፣ ብስኩትና ስኳር፣ እንዲሁም ሲጋራ፣ በመቀጠልም የቢራ ፋብሪካና መጠነኛ የሆነ የጨርቃ ጨርቅ
ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ሰፋ ላለና ሁለ-ገብ ለሆነ፣ እንዲሁም ለህብረ-ብሄርና(Nation-State)
ለህብረተሰብ ግንባታ የማያመች ወይም መሰረት ሊሆን የማይችል የኢንዱስትሪ ተከላና የፍጆታ
አጠቃቀም ነው ተግባራዊ ሊሆን የቻለው። ይህ ሁኔታ ይበልጥ ለንግድ እንቅስቃሴ፣ በተለይም ወደ ውጭ
ለሚወጣና ወደ አገር ውስጥ ደግሞ ለሚገቡ ምርቶችና እቃዎች(Export and Import) አመቺ ሁኔታን
ሲፈጥር፣ በዚያው መጠንም በኢንዱስትሪ ተከላና በቴክኖሎጂ እንቅስቃሴ ላይ ሊሰማራ የሚችል የአገር
ውስጥ ከበርቴ ብቅ እንዳይልና ተወዳዳሪ እንዳይሆን አግዷል ማለት ይቻላል። ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው
በተወሰኑ ነገሮች ላይ ያተኮረ በመሆኑ ከአንድ አካባቢ በማለፍ በአገር ደረጃ የሚስፋፋና እርስ በርሱ
በመያያዝ ብሄራዊ ባህርይ ሊይዝ የሚችል አይደለም። ስለሆነም የስራ መስክ ለሚፈልገው ሊሰራ የሚችል
ኃይል በብዛት የስራ ዕድል በመክፈት አስተማማኝ የገቢ ምንጭ ሊሆን የሚችል አይደለም።
ኢንዱስትሪዎችም በመለዋወጫ ዕቃና በጥሬ-ሀብት በውጭ ጥገኛ በመሆናቸው፣ ወደ ውጭ የውጭ
ምንዛሪ ካላግባብ ይፈስ ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳና በኢንዱስትሪዎች ውስንነት ወይም ደግሞ
ለማደግና ለመስፋፋት አለመቻል የተነሳ ወደ ውስጥ ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ ሊዳብር አልቻለም። በአንፃሩ
መስፋፋት የጀመሩት ቡናቤቶች፣ መደነሻ ቦታዎች፣ ሴተኛ አዳሪነት፣ ሻይቤቶችና ሌሎች ከዕውነተኛ
የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አንፃር ሲታዩ እዚህ ግባ የማይባሉ „ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔዎች“ ናቸው። በዚህም
ምክንያት የተነሳ ገንዘብ በሰፊው ለመሽከርከርና እንደ ህብረተሰብአዊ ኃይልም(Social Power) ሆኖ
ሊወጣ በፍጹም አልቻለም። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በቁጥር እያደገና ፍላጎቱ እየጨመረ ከመጣው
የህዝብ ቁጥር ጋር ለመመጣጠን ባለመቻሉ ማህበራዊና ህብረተሰብአዊ፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ ቀውስ
ሊያስከትል ችሏል ። በአገራችንም ለአብዮቱ መፈንዳት የበኩሉን አስተዋፅዖ አድርጓል።

ይህንን ዐይነቱን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ይዘት በምንመረምርበት ጊዜ ከህዝብ ፍላጎት ጋር ምን ያያዘዋል ?


ለአንድ አገርስ ዕድገትና ለህብረተሰብ አወቃቀር ያመቻል ወይ ? በጊዜው እነዚህን የመሳሰሉትንና ሌሎች
ጥያቄዎችን አንስቶ የሚከራከር ምሁራዊ ኃይል ነበር ወይ? ወይስ ዝም ብለን ነው የምንነዳው ?
በመሰረቱ ከላይ እንዳልኩት በመጀመሪያ ደረጃ የህዝብን መሰረታዊ ፍላጎት ከፍተኛ ቦታ በመስጠት
የማይነደፍ ፖሊሲ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አይደለም። በሰፊው የሰራ መስክ ለመክፈትና የስራ-ክፍፍል
እንዲዳብር የማያስችል ፖሊሲ በመሰረቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አይደለም። የሰው ልጅም መሰረታዊ ፍላጎት
ኮካኮላ መጠጣትና ሲጋራ ማጨስ አይደለም። የምግብነት ባህርይም የላቸውም። እንዲያውም በአንፃሩ
በከፍተኛ ደረጃ ለጤንነት ጠንቅ የሚሆኑና በሰውነት ውስጥ የሚገኙ ንጥረ-ነገሮችንና ቪታሚኖችን
በስነስርዓት በሰውነታችን ውስጥ እንዳይዋሃዱ የሚያደርጉ ናቸው። ይህ መሆኑ እየታወቀና ከኢኮኖሚ
ዕድገት አንፃርም አሉታዊ ውጤቱ እንደሚያመዝን እየታወቀ ለምን ይህ ዐይነቱን ኢንዱስትሪ ማስፋፋት
ተጀመረ ? ከዚህ ስንነሳ በኢትዮጵያ ምድር የተቋቋሙት ኢንዱስትሪዎችና የተስፋፉት የአገልግሎት
መስጫ ኩባንያዎች፣ እንደ ባንክና አየር መንገድ የመሳሰሉት በራሳቸው ዓለም የሚኖሩ፣ ትችታዊ
አመለካከት ያላቸውና የተገለጸላቸው ኢኮኖሚስቶች የተገለሉ(Enclave) የኢኮኖሚ መስኮች እያሉ
የሚጠሯቸውና፣ እርስ በእርሳቸው ያልተያያዙ(Delinked) የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ናቸው። በዚህም
ምክንያት የተነሳ ከህዝቡ ጋር ግኑኝነት የሌላቸውና ህብረተሰብአዊ ሀብትም ሊፈጥሩ የሚያስችሉ
አይደሉም። በመሆኑም ድሮም ሆነ ዛሬ ኢትዮጵያና የተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ብሄራዊ ኢኮኖሚ
የላቸውም። ብሄራዊ ኢኮኖሚ የሌለው አገር ደግሞ እንደ አገርና እንደህብረተሰብ የመኖር ኃይል
የለውም። የተለያዩ ህብረተሰብአዊ እሴቶችን በማዳበር እርስ በእርሱ ሊተሳሰር አይችልም። ሰፋ ያለ
በሁሉም መልክ የሚገለጽ ምሁራዊ ኃይልም ሊዳበር አይችልም። ይህም ማለት እንደዚህ ዐይነቱ አገር
በቀላሉ በውጭ ኃይሎች ይጠቃል፤ ይታለላል። ስለሆነም የአገር ውስጥ የጥሬ-ሀብት በውጭ ኃይሎች
በመዘረፍ ሰፊው ህዝብ ወደድህነትና ወደለማኝነት እንዲገፈተር ይደረጋል። ዘለዓለማዊ ድህነትና ጥገኝነት
የአንድ አገር መለዮች ይሆናሉ።

2ኛ) የመሰረታዊ ፍላጎት ፖሊሲና ውጤቱ- በዘመናዊነት ስም የቋቋሙት የምትክ ኢንዱስትሪዎች


ውጤታማ ለመሆን ባለመቻላቸው አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች እንደገና በዓለም ባንክና በዓለም አቀፍ
የገንዘብ ድርጅት በመመከር መሰረታዊ ፍላጎትን ለማሟላት(Basic Needs Economic Policy) በሚል
የኋላ ኋላ ተግባራዊ ሊሆን ያልቻለ ፖሊሲ በመከተል ወደ ሌላ ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል።
ፖሊሲው በዕቅድ ደረጃ ትክክል የሆነውን ያህል፣ ተግባራዊ ለመሆን የግዴታ የቴክኖሎጂ መሰረትና
ዕውቀት እንዲሁም ገንዘብ በጣም አስፈላጊ ናቸው። ይሁንና እነዚህን በመሳሰሉት ላይ ቅድሚያ
ባለመሰጠቱና የመጀመሪያው ዕቅድ ለምን እንደከሸፈ ባለመመርመሩ የመሰረታዊ ፍላጎት ዕቅድ
የተጠበቀውን ውጤት አላመጣም። አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ህዝቦች፣ በቂ ምግብ፣ ንጹህ ውሃ፣ መጠለያ
ወይም ቤት፣ ህክምናና መሰረታዊ ትምህርት ማግኘት በፍጹም አልቻሉም።

3ኛ) የአረንጓዴው አብዮትና ውጤቱ- ከዚያ በኋላ ተግባራዊ የሆነው የአረንጓዴው አብዮት(Green
revolution) ተግባራዊ በሆነባቸው አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የተጠበቀውን ውጤት አላመጣም።
1ኛ) ፖሊሲው የየአገሩን ተጨባጭና ባህላዊ ሁኔታዎች ያላካተተ ነው። ይህም ማለት ዕቅዱ ተጠናቅሮ
ከውጭ የመጣ ነው። 2ኛ) ዘሮችና ማዳበሪያ እንዳሉ ከውጭ የመጡ ሲሆኑ የየአገሩን የአመጋገብ ባህል
ያካተተ አይደለም። 3ኛ) ፖሊሲው አራሹን ገበሬ የጠቀመ ሳይሆን፣ የተጠቀሙት ሀብታም ገበሪዎች
ሲሆኑ፣ በአገራችን ደግሞ ራቅ ብለው ይኖሩ የነበሩ የመሬት ከበርቲዎች(Absentee landlord) ነበሩ።
ስለሆነም ብድርና ከዚህ ጋር የተያያዙትን ነገሮች ያገኙት እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ናቸው። 4ኛ)
ፖሊሲው በጣም ዘመናዊ ከመሆኑ የተነሳ ገበሬውን ከመሬቱ እንዲፈናቀል ያደረገ ሲሆን፣ ዘመናዊ የእርሻ
ማሳ ውስጥ ተቀጥሮ መስራት ያልቻለው ወደ ከተማዎች እንዲሰደድና የስራ-አጥ እንዲሆን ያደረገ ነው።
ስለሆነም አረንጋዴ አብዮት በመባል የሚታወቀውና የምግብን ዕጥረት ለማስወገድ በሚል 1960ዎቹ
መጨረሻ ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው ፖሊሲ እንደተጠበቀውና እንደተነገረለት የአፍሪካን ህዝቦች የምግብ
ችግር የፈታ አይደለም።

4ኛ) የተቋም ማስተካከያ ዕቅድና ውጤቱ- እነዚህ ፖሊሲዎች በሙሉ የተጠበቀውን ውጤት
ባለማምጣታቸው በተለይም በዕዳና በዘይት ዋጋ መናር፣ እንዲሁም በጥሬ-ሀብት ዋጋ መውደቅ የተጎዱት
አብዛኛዎች የአፍሪካ አገራት ተግባራዊ ማድረግ የተገደዱት የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተቋም ማስተካከያ
ዕቅድ(Structural Adjustment Programm) በመባል የሚታወቀውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው። ይህ ዐይነቱ
ፖሊሲ ለመጀመሪያ ጊዜ ጋና(Ghana)ውስጥ ተግባራዊ የሆነ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች
ተግባራዊ በማድረግ የዕዳ ወጥመድ ውስጥ እንዲገቡ ተደርገዋል። የንግድ ሚዛናቸው ተዛብቷል።
የማምረት ኃይላቸው ተዳክሟል። ከተማዎች ወደ ቆሻሻ መኖሪያነትና መጣያነት ተለውጠዋል። ወደ
አገራችንም ስንመጣ የህወሃት አገዛዝ ስልጣን ከጨበጠ ከጥቂት ዐመታት በኋላ እ.አ.አ በ1993 ዓ.ም
በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና (IMF) የዓለም ባንክ(World Bank) በመመከርና በመገፋት ተግባራዊ
አድርጎታል። ውስጣዊ ይዘቱም፣ የብርን ዋጋ መቀነስ፣(Devaluation) የውጭ ንግዱን ክፍት ማድረግ፣
(Liberalization) በዋጋ ላይ የሚደረገውን ገደብ ማንሳትና ገበያው „በጠያቂና በአቅራቢ ህግ“ መሰረት
„እንዲገዛ“ ማድረግ፣ ለልዩ ልዩ የማህበራዊ ፕሮጀክቶች የሚወጣውን ባጀት መቀነስ፣ በመንግስት
ቁጥጥር ስር ያሉ የንግድ መደብሮችንና ኢንዱስትሪዎችን ወደ ግል ማዘዋወር፣(Privatization) እነዚህን
የመሳሰሉ ናቸው ተግባራዊ የሆኑትና ጥቂቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀብታም በማድረግ ሰፊውን ህዝብ
ደግሞ በማራቆት ወደ ድህነት ዓለም ውስጥ እንዲገፈተር ለማድረግ የበቁት። ይሁንና ግን በአጭር ጊዜ
ውስጥ ሀብታም የሆኑት ግለሰቦችና ድርጅቶች የመፍጠር ችሎታ የሌላቸውና አዲስ ዐይነት የአሰሪዎች
ባህል በማዳበር የስራ መስክ ለመክፈት የቻሉ አይደሉም። እነ አቶ መለሰ ዜናዊና የተቀሩት የወያኔ
አዛውንቶችና ተከታዮቻቸው ይህን ፖሊሲ „በመንግስት የተደገፈ የኢኮኖሚ
ፖሊሲ“ (Developmental State Policy) በማለት ሰፊውን ህዝብ ለማሳመን ሞክረዋል። አብዛኛውም
ወያኔን የሚቃወመውና የሚጠላው ኃይል በወያኔ ፖሊሲ ላይ ስምምነት አለው። ስለሆነም በአገራችን
ምድር ላይ ለሚታየው የኢኮኖሚ ቀውስ ዋናው ምክንያት በመንግስት የተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊስ ነው
የሚል ስምምነት አለ። ይህም የሚያረጋግጠው ተቃዋሚው ኃይል በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነውን
የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምንነት ለመረዳት እንዳልቻለና፣ የአገራችንን የተወሳሰበ ችግር ለመፍታት የሚያስችል
አማራጭ ፖሊሲ ለማቅረበ እንደማይችል ነው።

ስለሆነም ባለፉት 27 ዓመታትና ከዚያም በላይ የተደረገው ትግል ሁሉ ስልጣንን ለመያዝ በመሆኑ
ለሳይንስ፣ ለቴክኖሎጂ፣ ለኢኮኖሚና ለማህበራዊ ጥያቄዎች በፍጹም አትኩሮ አልተሰጣቸውም። ሁሉም
የሚመኘውና የሚምለው የአገራችንን የተወሳሰበ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግሮች በንጹህ የገበያ
የኢኮኖሚ ፖሊሲ መፍታት ይቻላል ብሎ ስለሚያምን መሰረታዊ የሆኑ የአገር መገንቢያ መሳሪያዎች
ሊረሱ ችለዋል። ይሁንና ግን የተወሳሰበው የአገራችን ችግር እንዴት በገበያ ኢኮኖሚ አማካይነት ደረጃ
በደረጃ እንደሚፈታ የሚነግረን የለም። ድህነትና ረሃብ ተወግድው ህዝባችን ክብር ያለው ኑሮ እንዴት
ለመኖር እንደሚችል የሚተነትንና መንገዱን የሚያሳየን የፖለቲካ ፓርቲ ነኝ የሚልና የፖለቲካ እንቅስቃሴ
መኖሩን እስካሁን የሰማሁት ነገር የለም። ስለሆነም ከተማዎችና መንደሮች እንዴት እንደሚገነቡ፣
ለሰፊው ህዝብ የሚሆኑ የተለያየ ደረጃና ስፋት ያላቸው የመኖሪያ ቤቶች እንዴትና በምንስ መንገድ
እንደሚገነቡ፣ በየቦታው የተለያዩ ህዝብን የሚያሰባስቡና፣ የአገርን የተፈጥሮ-ሀብትና የሰው ኃይልን
ለማንቀሳቀስ የሚያስችሉ ተቋማት(Institutions) እንዴት እንደሚገነቡና፣ ሰፊው ህዝብስ እንዴት በስራ
ላይ ሊሰማራ ይችላል? በሚሉት መሰረተ-ሃሳቦች ላይ እንደመፍትሄ የሚቀርብ ሃሳብ የለም። በመሰረታዊ
የአገርና የህብረተሰብ ጥያቄዎች ላይ ግልጽነት እስከሌለ ድረስ ስለኢትዮጵያዊነት ብቻ ማውራቱ ይህን
ያህልም ትርጉም ሊኖረው አይችልም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ልትገለጽ የምትችለው በህዝቦቿ
የአኗኗር ስልትና የኑሮ ደረጃቸው ስለሆነ የኢትዮጵያን ህዝብ የኑሮ ሁኔታና የዕድገት ደረጃቸውን
ያላካተተ ኢትዮጵያዊነት ትርጉም አይኖረውም። በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያዊነት በሳይንስና
በቴክኖሎጂ፣ በጥበብ፣ በአማሩ ከተማዎችና መንደሮች፣ እንዲሁም ከተማዎችና መንደሮች
በዘመናዊ የመመላለሻ መንገዶች ሲያያዙ በዚህ መልክ የሚገለጽ ነው።

የተቋም ማስተካከያ ዕቅድ በኢትዮጵያ ምድር ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት እ.አ.አ ከ 1993 ዓ.ም ጀምሮ
በተለይም በንግድ ሚዛኑ ላይ ያስከተለውን አሉታዊ ተፅዕኖና አገራችንን በዕዳ እንደትተበተብ ለማድረግ
መብቃቱን በሚከተለው ዲያግራም መመልክቱ ፖሊሲው ያስከተለውን ጠንቅ ለመረዳት ያስችለናል።

የውጭው ንግድ ሚዛን በቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር


በእኔ ዕምነት በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮችና ኢትዮጵያንም ጨምሮ ፖሊሲ ነክ በሆኑ ነገሮች ላይ ሳይንሳዊ
ክርክርና የቲዎሪ ግምገማና ጥናት አይደረጉም። የተለያዩ አንድን አገርና ህብረተሰብ የሚመለከቱ
ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የአካባቢ ጉዳዮችን ወደ ውጭ አውጥቶ መከራከር የተለመደ
አይደለም። የትምህርት ከሪኩለሞችም ከውጭ የሚመጡና ተግባራዊ የሚሆኑ ስለሆነ ተማሪውን
በሁሉም አቅጣጫና ወደ ውስጥ በመመልከት አገር ማለት ምን ማለት ነው? ህብረተሰብስ በምን መሰረት
ላይ ቢገነባ የተረጋጋ ሁኔታ ሊፈጠርና ለሚቀጥለው ትውልድ ሊተላለፍ ይችላል? ብሎ እንዲጠይቅ
የሚያስችለው አይደለም። የትምህርት አሰጣጡም የህብረተሰብን ጥያቄዎች ሊፈታ የሚችል ሆኖ
ስለማይዘጋጅ ተማሪዎች ትምህርት ጨርሰው በሚወጡበት ጊዜ በግልጽ የሚታዩ ህብረተሰብአዊ
ችግሮችን የመፍታት ችሎታ የላቸውም። ብቃት ያላቸው ተቋማትም ስለሌሉ ትምህርቱን ጨርሶ
የሚመረቀው አዳዲስ የሰው ኃይል በስራ በመሰማራትና በየአካባቢው የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት
በማንቀሳቀስ ህብረተሰብአዊ ሀብት ሊፈጥር አይችልም። ስለሆነም የየአገሩ መንግስታት ከዓለም አቀፍ
ማህበረሰብ (International Community) ጋር በማበር የነሱን አገር አፍራሽና ሀብት አውዳሚ ምክር
በመቀበል በየአገሮቹ ውስጥ የተዝረከረክ ሁኔታ ሲፈጠር ይህንን የሚቃወምና የሚያጋልጥ የተገለጸለት
ምሁራዊ ኃይል ስለሌለ ሰፊው ህዝብ ከፍተኛ በደል ይደርስበታል። ቢኖርም እንኳ ተደማጭነት
ስለሌለው፣ ገፍቶ የሄደው አይ ይታሰራል፣ ይገደላል፣ ካሊያም እንዲሰደድ ይደረጋል። በዚህ መልክ
ጠቅላላው ህዝብ የኑሮን ትርጉም እንዳይረዳ ሆኗል፤ ባህልና እሴቶች እንዲፈራርሱ ተደርገዋል። የስራ
እሴት ከመስፋፋት ይልቅ ብልግና እንዲስፋፋ መንገዱ ተመቻችቷል። በተለይም የሶስዮሎጂ፣ የፍልስፍናና
የስነ-ልቦና ጥናቶች ባልተለመዱበት እንደኛ ባለው አገር ደግሞ ጥቂቶች በመነሳት „ሁሉም አገሮች አንድ
ዐይነት የማክሮ ኢኮኖሚ ፓሊሲ ያስፈልጋቸዋል“ በማለት የአንድን አገር ውስጣዊ ኃይል ለማዳከም
ችለዋል፤ በታትነዋልም። ከዚህ ስንነሳ ባለፉት ስድሳ ዐመታት በተለያዩ የአፍሪካ አገሮችና በአገራችንም
ጭምር ከፍተኛ የታሪክ ወንጀል ተሰርቷል። ኢኮኖሚያዊ ፋሺዝም በመስፋፋት ወደ አንድ ቢሊዮን
የሚጠጋ ህዝብ እንዲሰቃይ ተደርጓል። ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ ዛሬም የቀጠለና አህጉሩን እየበታተነ ይገኛል።
በአገራችንና በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የሰፈነውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች ይበልጥ
ለመረዳት ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚባለውን ጽንሰ-ሃሳብና መቼና ለምን እንደፈለቀና እንዴትስ
ተግባራዊ ለመሆን እንደቻለ ጠጋ ብለን እንመልከት። በተጨማሪም በተራ የገበያ ኢኮኖሚና
በካፒታሊዝም መሀከል ያለውን ልዩነት እንቃኝ። በእነዚህ መሰረታዊ ነገሮች ላይ ግልጽነት ሲኖር ለአንድ
አገር የሚበጅ ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊስ ለመንደፍ ይቻላል የሚል ዕምነት አለኝ።

ማክሮ ኢኮኖሚ(Macroeconomy) ማለት ምን ማለት ነው ?


ማክሮ የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ ከግሪክ የመነጨ ሲሆን ትልቅ ወይም ረጅም ማለት ነው። ይህም ማለት
ብዙ ነገሮችን ያጣመረ ማለት ነው። ይሁንና ግን ወደዘመኑ የኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ ስንመጣ ማክሮ
ኢኮኖሚ በክስተት ደረጃ የሚታዩ ነገሮችን መግለጫ መሳሪያ እንጂ የካፒታሊስት ኢኮኖሚን ውስጣዊ
ህግና እንቅስቃሴ መተንተኛ መሳሪያ አይደለም። ስለሆነም እንደ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት፣(Inflation)
የስራ አጥ ሁኔታ፣(Unemployment) የውጭው አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴ፣(Balance of Payment)
አጠቃላዩ የኢኮኖሚ ዕድገት ጉዳይ፣ በተለይም ማደግና መቀዝቀዝ፣ የመንግስት ባጀት ጉዳይ፣...ወዘተ.
የማክሮ ኢኮኖሚ „ንጥረ-ሃሳቦች“ ናቸው ማለት ይቻላል። ማክሮ ኢኮኖሚ በፖሊሲ ደረጃ በመጀመሪያ
ጊዜ በታወቀው የእንግሊዙ ኢኮኖሚስት ኬይንስ በ1930ዎች መጀመሪያ ላይ የፈለቀ ነው።
እንደሚታወቀው በ1920ዎቹ መጨረሻ ላይ አብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች በከፍተኛ የኢኮኖሚ
ቀውስ(Depression) የተመቱበት ጊዜና፣ በብዛት የስራ-አጥ የሚታይበት ዘመን ነበር። በዚህም ምክንያት
የተነሳ በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ወደ ፖለቲካው ሊዛመት የሚችል ህብረተሰብአዊ
ግጭቶች ብቅ ብቅ ያሉበት ጊዜ ነበር። መንግስታትም ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደሚከተሉ ግራ
የተጋቡበት ወቅት ነበር። ቀውሱ እስከተከሰተ ጊዜና ወደ አጠቃላይ ሁኔታ እስከተሸጋገረበት ዘመን
አብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች መንግስታት በንጹህ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚመሩና፣ ሁሉንም ነገር
ገበያው ይፈታዋል(Laissez Faire) ብለው የሚያምኑ ነበሩ። ይሁንና ግን የቀውሱ ጥልቀት ከፍተኛ
በመሆኑና በብዙ መስኮች መዛባት ይታይ ስለነበር ችግሩን ገበያ በራሱ ውስጠ-ኃይል ሊፈታው
አልቻለም። በጊዜው በከፍተኛ ደረጃ በቀውሱ የተጠቃው ጀርመን አገዛዙ ይባስ ብሎ የአንጀት አጥብቅ
የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተሉ ቀውሱ በመባባስ ለፋሺዝም መነሳት በራሱ አንደኛው ምክንያት ሊሆን
በቃ። በሁኔታው የተደናገጠውና ተስፋ የቆረጠው ሰፊ ሰራተኛ ህዝብ ይበልጥ በናዚዎች ጉያ ስር
መመሸግን መረጠ።

ይህንን ሁኔታ የተገነዘቡት እንደአሜሪካን የመሳሰሉት አገሮች ፕሬዚደንት ሩዝቤልት በ1933 ዓ.ም
ሲመረጡ በመጀመሪያ ደረጃ በመንግስት የተደገፈ ፖሊሲ ማካሄድ ነው የጀመሩት። ይህ የኢኮኖሚ
ፖሊሲ አዲሱ ስምምነት(The New Deal) በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ በትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ያተኮረና
የስራ መስክ ለሚፈልገው ሰፊ የስራ-አጥ ኃይል የስራ መስክ የከፈተ ነበር። ፕሮግራሙ ከ1933-1939
ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ሲሆን፣ የስራ ዕድገትን የሚያስተዳድር ወይም የስራ መስኮችን
የሚያዘጋጅ መስሪያ ቤት በማቋቋም ለስራ ቦታ ፈላጊው ቅድመ-ሁኔታዎች ተነጠፉ። ከዚህም በላይ
የኢንዱስትሪዎችን ተከላና ስርጭት የሚያስተዳድር መስሪያ ቤትና ህግ በማውጣት የተቀላጠፈ ስራ
መስራት ተቻለ። ወጣቱና በኢንዱስትሪ መስክ ውስጥ ለመሰማራት የማይችለው በዛፍ ተከላና በልዩ ልዩ
የመንገድና የቤት ስራዎች ላይ በመሰመራት ሰራ-አጡን ወደ ስራ ዓለም እንዲመለስና ሀብት ፈጣሪ
እንዲሆን ተደረገ። ልዩ ልዩ ፕሮጀከቶችን ፋይናንስ ለማድረግና አጠቃላይ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት
ለማምጣት ደግሞ የባንኩን ዘርፍ በአዲስ መልክ ማዋቀር አስፈለገ። ስለሆነም በ1929/1930 ዓ.ም
የታየው ታላቅ የኢኮኖሚ ቀውስ(Depression) እንዳይደገም የአየር በአየር የቁማር ጨዋታ በሚጫወቱ
ኢንቬስትሜንት ባንኮችና በንግድ ባንኮች መሀከል(Glass-Steagall Act) ግልጽ የሆነና የማይገናኝ የስራ
ክፍፍል ተግባራዊ ተደረገ። በዚህም መሰረት የንግድ ባንኮች ለተጨባጭ የኢኮኖሚው መስክ፣ ማለትም
ለቤት ስራ፣ ለኢንዱስትሪ ተከላና ለሌሎች የኢኮኖሚውን ዕድገት የሚያፋጥኑና እርስ በእርሳቸው
ለሚያያዙ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ብድር በስርዓትና ግልጽ በሆነ መልክ የሚሰጥበት ሁኔታ ተዘጋጀ።
መንግስት ደግሞ በበኩሉ፣ ሰፋ ባለ የቤት ስራ፣ የመንገድና የድልድዮች ስራ፣ እንዲሁም አዳዲስ የባቡር
ሃዲዶችን መስራትና ያለውንም መጠገን፣ እንደቴኒሲ ሽለቆ በመሳሰሉት ትላልቅ የኃይል ማመንጫ
ፕሮጀክቶች ላይ በመሰማራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለብዙ ሚሊዮን ህዝብ የስራ መስክ ሲከፍት፣ በዚያው
መጠንም ኢኮኖሚው እያደገ መጣ። ይህ ዐይነቱ በመንግስት የተደገፈ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ
የንጹህ ገበያን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስህተትነቱን በማሳየት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተዓምር ሊፈጠር ቻለ።
ኢኮኖሚስቱ ኬይንስ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በውስጡ ተፈጥሮአዊ መዛባት ስላለውና ራሱን በራሱ
በማንቀሳቀስ ከቀውስ ለመውጣት ስለማይችል የግዴታ የመንግስት ጣልቃ-ገብነት እንደሚያስፈልገው
በማመልከትና በማረጋገጥ፣ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴም በምን መልክ በገንዘብ እንደሚደጎም ወይም
ፋይናንስ እንደሚሆን አሳየ። በሱም ዕምነት መንግስት የግዴታ ከባንክ በመበደር ኢኮኖሚውን
ማንቀሳቀስ አለበት። ማርክስ በ19ኛው ክፍለ-ዘመን እንዳረጋገጠውና ኬይንስም ተመራምሮ
እንደደረሰበት የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በዕድገትና በቀውስ የሚገለጽ ስርዓት እንደመሆኑ መጠን ቀውሱን
የሚያስወግድና ወደ ሚዛናዊነት ሁኔታ ሊያመጣ የሚያስችለው ውስጣዊ መሳሪያ ወይም ህግ የለውም።
ስለሆነም ቀውሱ ስር ከሰደደ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ማህበራዊ መናጋትን ስለሚያስከትል የግዴታ
መንግስት ጣልቃ በመግባት ኢንዱስትሪዎች በድሮ የማምረት ኃይላቸው እንዲያመርቱና የስራ መስክም
እንዲከፍቱ አስፈላጊ የሆኑ የመዋዕለ-ነዋይ ድጎማዎችን ማድረግ አለበት። በዚህ መልክ ብቻ በገንዘብና
በተጨባጭ ኢኮኖሚው መስክ ያለውን ግኑኝነት ማጠንከር ሲቻል፣ መንግስትም ከቀረጥ ገቢ ስለሚያገኝ
የተበደረውን ገንዘብ መክፈል ይችላል፤ የተቀረውን ደግሞ በልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ላይ በማዋል
ለኢኮኖሚው ዕድገት ልዩ ዕምርታን ይሰጠዋል።

ይህ ኬይንስ ያዳበረው የኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ ይበልጥ ተግባራዊ የሆነው ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት
በኋላ ነው። በጦርነቱ የተጎዱ አብዛኛዎቹ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች፣ በተለይም እንደጀርመን
የመሳሰሉት በመጠኑም ቢሆን በማርሻል ፕላን በመደገፍ፣ የተንኮታከውን ኢኮኖሚያቸውን አስራ
አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንደገና መልሰው ሊገነቡ ችለዋል። እዚህ ላይ ወሳኙ፣ የማርሻል ፕላን
ሳይሆን፣ ውስጣዊ ፍላጎት መኖር፣ የአደረጃጀት ስልትና አገርን ለመገንባት ቆርጦ መነሳት ዋናው
የኢኮኖሚው ዕድገትና የአገር ግንባታ መሰረተ-ሃሳቦች ናቸው። በመሆኑም ለትናንሽና ለማዕከለኛ
ኢንዱስትሪዎች፣ እንዲሁም ለሰፊው ህዝብ ቤቶችን ለመስራት ፋይናንስ የሚያደርግ በመንግስት
ቁጥጥር ስር ያለ ልዩ ዐይነት የብድር ባንክ(Credit Bank) በማቋቋምና፣ የቁጠባ ባንኮችን በማስፋፋት
ኢኮኖሚውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳደግ ችለዋል። በሰፊው የስራ መስክም በመክፈት በአጭር ጊዜ
ውስጥ በቴክኖሎጂ ለመመንጠቅ ችለዋል። በተለይም የተለያዩ የቴክኖሎጂ ማሰልጠኛ ኮሌጆችንና
የምርምር ጣቢያዎችን፣ እንዲሁም የተግባረ-ዕድ ማስልጠኛ ማዕከሎችን በማቋቋምና በተለያዩ ክፍለ-
ሃገራት በእኩል ደረጃ እንዲሰራጩ በማድረግ አፋጣኝ የሆነ ዕድገትን ማምጣት ችለዋል። በዚህም መሰረት
ልዩ ልዩ ምርቶችን በማምረት የህዝቦቻቸውን ፍላጎቶች ማርካት ችለዋል። በቅድሚያ ግን ተግባራዊ
ማድረግ የጀመሩት፣ የመኖሪያ ቤቶችን ችግር ወይም ጥያቄ መፍታት፣ የንጹህ ውሃን ጉዳይ ማስተካከልና
በየቤቱ እንዲገባ ማድረግ፣ የምግብና የመብራት እንዲሁም የማሞቂያና የምግብ ማብሰያ ችግሮችን
መፍታት የኢኮኖሚው መሰረተ-ሃሳቦችና ቅድሚያም የተሰጣቸው ናቸው። ምክንያቱም እነዚህ
መሰረታዊ ፍላጎቶች ሳይፈቱና ሳይሟሉ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ማውራት አይቻልምና።
ስለሆነም በአጠቃላይ ሲታይ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ቀድሞም ሆነ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ
ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ህብረተሰብንና አገርን በጠንካራ መሰረት ላይ ከመገንባት ተነጥሎ የሚታይ
አይደለም። ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴም በተራ ንግድ ወይም በችርቻሮ የሚገለጽ ሳይሆን፣ በሳይንስና
በቴክኖሎጂ እንዲሁም በጠራ ስራና ድርጅታዊ አዘገጃጀት ብቻ ነው። ከዚህም ባሻገር በሳይንስና
በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የጥበብንና የልዩ ልዩ ባህሎችን ዕድገትና
መዳበርን ያግዛል። እንደ ጥንታዊ የሙዚቃ ዐይነቶች፣ ድራማዎችና የፖለቲካ ቀልዶች፣ ሙዚየሞችና
ስዕሎች እንዲሁም ልዩ ልዩ የስፖርት ዐይነቶች በተወሰነ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በአገር ደረጃ የመስፋፋት
ዕድል ይኖራቸዋል። በዚህ ዐይነቱ የባህል እንቅስቃሴ ሰፊው ህዝብም የበለጠ የመተሳሰርና ራሱን በራሱ
የማግኘት ዕድል ያጋጥመዋል። ሰው መሆኑን በመረዳት የበለጠ ፈጣሪ ለመሆን ይችላል። በዚህ መልክ
ስለኢኮኖሚ ዕድገትና ስለአገር ወይም ስለህብረተሰብ ማውራት ይቻላል። ኢኮኖሚያዊ መሰረታቸው
ጠባብ የሆነና ህዝቡም ተዝረክርኮ የሚኖርባቸው አገሮች እንደህብረተሰብና እንደማህበረሰብ ወይም
እንደ አገር ሊቆጠሩ በፍጹም አይችሉም።

እንደገና ወደ ማክሮ ኢኮኖሚ ጽንሰ-ሃሳብ እንምጣ። ይህንን በንፅፅር (Analaogy) እንመልከተው። ከላይ
ለማሳየት እንደሞከርኩት ማክሮ ማለት ትልቅ ነገር ማለት ነው። እንደሚታወቀው ማንኛውም ግዙፍ
ወይም ትልቅ ነገር የትናንሽ ንጥረ-ነገሮች ክምችት ነው። ህይወት ያላቸውና ህይወት የሌላቸው ነገሮች
በሙሉ የመጨረሻ መጨረሻ የልዩ ልዩ አካሎችና ንጥረ ነገሮች ድምሮች ናቸው። ለምሳሌ ማንኛውንም
ሰው እንደማክሮ ልንወስደው እንችላለን። እንደሚታወቀው የሰው ልጅ ሁሉ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች፣
የነርቭ ሲስተምና በሌሎች የሚገለጽ ነው። ሰውን ሰው የሚያደርገው እንዲንቀሳቀስ፣ እንዲያስብና
እንዲሰራ፣ እንዲሁም አካባቢውን ወይም ተፈጥሮን እንዲለውጥ የሚያስችሉት ልዩ ልዩ የሰውነት አካሎች
ስላሉት ነው። እነዚህ ልዩ ልዩ ነገሮችን እንደሚክሮ ልንወስዳቸው እንችላለን። ይህም ማለት በተለያዩ
የሰውነት አካሎች መሀከል ባለው የስራ-ክፍፍልና ቅንብር ሰውነታችን መንቀሳቀስና ማሰብ ይችላል።
ይህንን ወደ ኢኮኖሚ ስንመነዝረውና ወደ ማክሮ ኢኮኖሚ ከመምጣታችን በፊት እዚህና እዚያ
የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርቱ ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም የንግድ
እንቅስቃሴዎች መኖር አለባቸው። በእነዚህ እዚህና እዚያ ተሰበጣጥረው በሚገኙ፣ ይሁንና ደግሞ
በገንዘብ አማካይነት የሚገናኙና፣ ከፍጆታ ዕቃዎች ባሻገር ለትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የሚሆኑ ልዩ ልዩ
የመለዋወጫ ዕቃዎችንና መሳሪያዎችን በሚያመርቱት መሀከል መተሳሰር ሲኖር ማክሮ ብለን
የምንጠራው ትልቁ ነገር ይፈጠራል። የካፒታሊዝምን ዕድገት ስንመለከት ትናንሽና የማዕከለኛ
ኢንዱስትሪዎች፣ እንዲሁም የዕደ-ጥበብ ክንውኖች ከመፈጠራቸው በፊት ማክሮ ብለን የምንጠራው
ትልቁ ነገር አልተፈጠረም። ስነስርዓት ያላቸው ከተማዎችና መንደሮች ሳይገነቡና በዕቅድ የሚካሄድ
የንግድ እንቅስቃሴ ከመዳበሩ በፊት ስለማክሮ ኢኮኖሚ ማውራትም በፍጹም አይቻልም። ይህንን
ዐይነቱን ከትንሽ ነገር ተነስቶ ከሌላው ጋር በመያያዝና ወደግዙፍነት የመለወጥን ሁኔታ በተፈጥሮ ውስጥ
የምንመለከተው የዕድገት ሂደት ነው። እንደየሁኔታው በተለይም ህይወት ያለው ነገር፣ ራሳችንም ሰዎች
ከትንሽ ነገር ተነስተን ነው እያደግንና የሰውነት አካሎቻችን ሁሉ ቅርጽና መልክ እየያዙ ሊመጡ
የሚችሉት። በተለይም ደግሞ ልዩ ዐይነት ጥንቃቄ የተሞላበት እንክብካቤ ከተደረገ፣ አትክልቶች ጥሩ ፍሬ
ሊሰጡ ይችላሉ፤ የሰው ልጅ ደግሞ በአካሉ ብቻ ሳይሆን በመንፈስም በመዳበር የማገናዘብ፣ የማወዳደር፣
ጠለቅ ብሎ የማሰብና የመመራመር፣ እንዲሁም አርቆ-የማሰብ ኃይሉ እያደገ ይመጣል።

ከዚህ ስንነሳ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች በአመንክዮ(Logically) ሳያስቡ በዓለም አቀፍ ተቋማትና
(International Insitituions) „በአማካሪ“ ኩባንያዎች(Consulting Companies) እየተመከሩ ተግባራዊ
የሚያደርጓቸው ፖሊሲዎች በሙሉ መቀመቅ ውስጥ የከተቷቸውና የሚከቷቸው ናቸው። ይህንን ከላይ
ለማሳየት የሞከርኩትን ከትንሽ ነገር ተነስቶ ወደ ትልቅ ነገር ማደግና፣ በሌላ ወገን ደግሞ አንድ ትልቅ ነገር
የተለያዩ ክፍሎች ጥምር መሆኑን ካለመረዳት የተነሳ ተግባራዊ የሚሆኑት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ
ከፍተኛ ህብረተሰብአዊ ውዝግብን እየፈጠሩና ለአካባቢ ቀውስ ምክንያት እየሆኑ ነው። የጥሬ-ሀብት
በተቆጠበና ስነ-ስርዓት ባለው መልክ ተቆፍሮ በመውጣትና በፋብሪካ ውስጥ በመፈበረክ ለአንድ ህዝብ
የሚጠቅም ህብረተሰብአዊና ብሄራዊ ሀብት(National Wealth) እንዳይፈጠር እየተደረገ ነው። ሌላው
አደናጋሪው ነገር ካፒታሊዝም በፍጥነት ዓለም አቀፋዊ ባህርይ መውሰድ ከጀመረ ጀምሮ ተፈጥሮአዊ
የሆነውን የሰውን ልጅና የህብረተሰብ ዕድገት እንዲዛነፍ ወይም እንዲሳሳት በማድረጉ እንደኛ የመሳሰሉ
በተለይም በምሁር ደረጃ ያልዳበሩ አገሮች የማያስፈልግ የኢንዱስትሪ ተከላ በማካሄድ አጠቃላዩን
የህብረተሰብ ዕድገት እንዲረበሽና ምስቅልቅሉ እንዲወጣ ለማድረግ በቅተዋል። በተፈጥሮና በሰው ልጅ
መሀከል ያለው ጤናማ ግኑኝነት እንዲረበሽ በማድረግ ከተማዎች ወደ ምድረበዳነት
ተለውጠዋል። ከተማዎች ከህንፃዎችና ከመንገዶች በስተቀር ዛፎችና ወንዞች የሌሉባቸው በመሆን የሰው
ልጅ አኗኗር ስልትና ባህርይ ሊናጉ ችለዋል። ከመጀመሪያውኑ መቅደም ከሚኖርበት ነገር ላይ ከመነሳት
ወይንም እዚያ ላይ ከመረባረብ ይልቅ የማይሆን ነገር ላይ በመሰማራት የሰውን የማሰብ ኃይል ለማቃወስ
ችለዋል፤ የተፈጥሮ ሀብትም በከፍተኛ ደረጃ እንዲባክን አድርገዋል። በሌላ አነጋገር፣ የምግብን፣ የቤትን፣
የንጹህ ውሃን፣ የህክምናን፣ የትምህርትንና የከተማ ግንባታዎችን ከማስቀደም ይልቅ የሸንኮራ አገዳ
በመትከል ወደ ስኳር ምርት ያመራሉ። ከንጹህ ውሃ ይልቅ የኮካኮላ ኢንዱስትሪ ይከፍታሉ። እህል
ከማብቀል ይልቅ ትምባሆና አበባ ተከላን ያስቀድማሉ። በዚህ መልክ ተፈጥሮአዊ የሆነውን የሰው ልጅ
ፍላጎትና የህብረተሰብ ዕድገት ይጨናገፋሉ። ስለሆነም በየአንዳንዱ የታሪክ ወቅት ስህተት እየተሰራ አንድ
ህብረተሰብና አገር በችግር ላይ ችግር እየተደረበባቸው የማይወጡት ማጥ ውስጥ እንዲወድቁ
ተደርገዋል።

በአገራችንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለሚወራው ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር ስንመጣ የኒዎ-ሊበራል
ኢኮኖሚስቶች እጅግ በተዛነፈ መልክ ያስፋፉትን የገንዘብ የአንጀት አጥብቅ የኢኮኖሚ ፖሊሲ(Austerity
or Monetary policy) በመውሰድ ነው ሁሉም አገር የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ያስፈልገዋል እየተባለ
የሚናፈሰውና እንደዳዊት የሚደገመው። ስለሆነም በዚህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሰረት
ሁሉ ነገር ለገበያ መተው አለበት። መንግስት በምንም ዐይነት በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ መግባት
የለበትም። በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ኢንዱስትሪዎችና የአገልግሎት መስጫ ድርጅቶች፣ ውሃ፣
መብራት፣ የባቡር ሃዲድ፣ ሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶች ሁሉ ወደ ግል መዘዋወር ወይም መሸጥ
አለባቸው። የመንግስት ተግባር ዝም ብሎ እጁን አጣጥፎ ከመቀመጥ በስተቀር በኢኮኖሚውና ሌሎች
ማህበረስቡን በሚመለከቱ ነገሮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት የገበያን ህግ የሚፃረሩ እርምጃዎች መውሰድ
የለበትም ። ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ እ.አ ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ በብዙ አገሮች ውስጥ
ተግባራዊ በመሆን፣ እንደ እንግሊዝ በመሳሰሉት ጥንታዊ የኢንዱስትሪ አገሮች ውስጥ የኢንዱስትሪዎችን
መፈራረስ(Deindustrialization) አስከትሏል። የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ከተጨባጩ የኢኮኖሚ
እንቅስቃሴ(Real Economy) ወደ አየር በአየር ንግድ (Financial Market) ላይ እንዲያዘነብል
በማድረግና፣ የማዕከላዊ ባንኮች በሚከተሉት የአልቦ ወለድ የብድር አሰጣጥ ፖሊሲ (Zero Interset
Rate) አማካይነት ጥቂት ባለሀብቶች የባሰውኑ እንዲናጥጡ በማድረግ፣ እንደወል ስትሪት (Wall Street)
የመሳሰሉት ደግሞ እንደዋና የኢኮኖሚ ዘርፍ ሆነው በመታየት ከፍተኛ የሀብት ማውደም
የሚካሄድባቸው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ለመሆን በቅተዋል። በዚህ መልክ ይህ ዐይነቱ የብድር
አሰጣጥ ፖሊሲና የአየር በአየር ጨዋታ በከተማዎች ውስጥ የኑሮ ሁኔታ እንዲወደድ ሲያደርግ፣ በተለይም
እንደለንደንና ፓሪስ እንዲሁም ኒዎርክ የመሳሰሉት ከተማዎች ውስጥ ሰው መኖር የማይችልበት ሁኔታ
ሊፈጠር ችሏል። ቤቶችና መሬት ወደ አየር በአየር ንግድነት በመለወጥ(Speculation Objects) ከፍተኛ
የሆነ የሀብት ሽግሽግ ይካሄዳል። በዚህ ላይ ከተለያዩ አገሮች ባለሀብቶች፣ ከራሺያ፣ ከዩክሬይን፣ ከቻይናና
ከተለያዩ የአረብ አገሮች በመምጣትና ቤቶችን በመግዛትና በመሸጥ ተራው ሰው ቤት ተከራይቶ ሊኖር
የሚችልበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ተደርጓል። በዛሬው ወቅት ማንኛውም ተራ ሰው የራሱን የግል ቤት
የመስራት ኃይል ወይም አቅም የለውም። አሜሪካም ይህንን መንገድ በመከተሉ እንደዚሁ ሰፋ ያለ
የኢንዱስትሪ መፈረካከስ ሲደርስበት፣ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ኢንዱስትሪዎችን በመንቀል ሜክሲኮና
ቻይና በመውሰድ ለእነዚህ አገሮች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የተወሰነ አስተዋፅዖ ማድረግ ችለዋል። በአንፃሩ
በእነዚህ አገሮች ውስጥ በርካሽ የሰው ጉልበት የሚመረቱት ምርቶች በአሜሪካን ገበያ ላይ በመሸጥ
ገበያውን አጥለቅልቀውታል። በዚህም ምክንያት የአሜሪካን የውስጥ ገበያና የውጭው ንግድ በከፍተኛ
ደረጃ በመዳከሙ ከካፒታል ገበያ፣ በተለይም ከቻይና ገንዘብ እንዲበደር ተገዷል።

የአገራቸውን ተጨባጭ ሁኔታና የሰውን ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት ማንበብ የማይችሉ የማክሮ ኢኮኖሚ
ፖሊሲ ርዕዮተ-ዓለም አራማጆች ማንኛውም አገር የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ(Macroeconomy Policy)
ያስፈልገዋል እያሉ አገራችንን የዓለም የገንዘብ ድርጅት(IMF)፣ የዓለም ባንክና፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ
የኢኮኖሚ „አማካሪዎች“(Consulting Companies) መጫወቻ ለማድረግ በቅተዋል። እንደምናየውና
የኢትዮጵያ ህዝብ የኑሮ ሁኔታ እንደሚያረጋግጥልን እነዚህ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተዋንያንና
የአገራችን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀስቃሾች የህዝባችንን መሰረታዊ ችግሮች መፍታት አልቻሉም።
እንዲያውም ህዝባችን የባሰውኑ ደሃ እንዲሆን በማድረግ ጤናማ ኑሮ እንዳይኖር አድርገውታል። የማክሮ
ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ከሆነ ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ በአዲሰ አበባችን ብቻ ቁጥራቸው የማይታወቅ
የቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎች(Slums) ተስፋፍተዋል። በሌላ ወገን ደግሞ በመንግስት የሚደገፉና ከባንክ
በርካሽ ወለድ ብድር የሚያገኙ በተለይም ከአንድ ብሄር-ሰብ የተውጣጡ ግለሰቦች ደሃውን ኗሪ ሰው
ከመሬቱ በማፈናቀል ፎቅ ቤቶች በመስራት በአጭር ጊዜ ውስጥ የናጠጡ ሀብታሞች ሊሆኑ
በቅተዋል። በዚህ መልክ የአገራችን ሀብት እንዲዘረፍና ከፍተኛ የሆነ የአካባቢ ቀውስ እንዲከሰት
አድርገዋል። ይህ ዐይነቱ የህብረተሰብንና የተፈጥሮን ህግ፣ እንዲሁም የሰውን ምንነት በሚገባ
የማያገናዝብ ኢ-ሳይንሳዊ የሆነና የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በመሆኑ መጠነ-ሰፊ የሆነ፣
በቀላሉ መፍትሄ ሊገኝለት የማይችል የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውስ በአገራችን ምድር ሊከሰት በቅቷል።
ማንም ኃይል በቀላሉ ሊፈታው እንዳይችል ተደርጓል። ነገር ግን ከፍተኛ የአስተሳሰብ ለውጥ ከተደረገና
የአሰራር ስልትም ከተቀየረ አፍጠው አግጠው የሚታዩ ችግሮችን በጋራ መቅረፍ ይቻላል። ለዚህ ደግሞ
ዋናው መሰረተ-ሃሳብ በራስ መተማመን ነው።

ከዚህ ችግር ለመውጣት መሰረታዊ ሃሳቦችን እንረዳ። ይህም በተራ ገበያና በካፒታሊዝም መሀከል
ያለውን ልዩነት ማወቅ ያስፈልጋል። በእኔ ዕምነት አብዛኛዎቹ ስለማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አስፈላጊነት
የሚወተውቱ ኢኮኖሚስቶች የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ምን እንደሆነና በምንስ ዐይነት ህግ እንደሚመራ
የሚያውቁ አይመስለኝም። የዚህ ክፍተት ዋናው ችግር አብዛኛዎቹ ኢኮኖሚስቶች የኢኮኖሚ
አስተሳሰብን ታሪክና የካፒታሊስት ኢኮኖሚን ዕድገት ደረጃ በደረጃ እንዴት እንደተገነባ ባለመማራቸው
ነው። ሁሉም የሚማሩት ሳሙኤልሰን ያስፋፋውን የኢኮኖሚ ትምህርት ስለሆነና በኒዎ-ሊበራል
ኢኮኖሚስቶች እጅግ በተሳሳተ መልክ ተዘጋጅቶ የቀረበውን እንዲማሩ በመደረጋቸው የካፒታሊዝምን
ኢኮኖሚ መሰረተ-ሃሳብና ውስጣዊ ህግ እንዳያውቁ ሆነዋል። ስለሆነም ከአገር ገንቢነት ይልቅ አገርን
አፍራሽና ሀብትን ቸብቻቢ ለመሆን ችለዋል። የሚያወሩትም ፕላቶ እንደሚለንና እንደሚያስተምረን
„እንዴት አድርገን እንደማህበረሰብና እንደህብረተሰብ እንኑር፣ አገርን በጸና መሰረት ላይ
እንገንባ“ ሳይሆን እንደተራ ነገር ነው የሚያስቡት። ይህም ማለት አንድ አገር ወደ ተራ ገበያነት
እንዲቀነስና የሰው ልጅም ባክኖ እንዲቀር የሚያደርግ አስተሳሰብ ነው በአገራችን ምድርና በተቀሩት
የአፍሪካ አገሮች በከፍተኛ ደረጃ መስፋፋትና የሰውንም ጭንቅላት መያዝ የቻለው። ይህ ዐይነቱ የተበላሽ
አስተሳሰብ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ በመውሰድና ሁሉም አገሮች ተግባራዊ በማድረጋቸው ለሙስናና
ለተዛባ የሀብት ክፍፍል ዋና ምክንያት በመሆን፣ ወደ ውስጥ ደግሞ በተስተካከለ የማኑፋክቸር ተከላ ላይ
የተመሰረተ የኢንዱስትሪ ግንባታ እንዳይካሄድ በማገድ የውስጥ ገበያ እንዳያድግ ተደርጓል። አሁን
በቅርቡ በፕሮፌሰር ስቴፋን ሹልማይስተር(Stephan Schulmeister) የታወቁት የአውስትሪያ ኢኮኖሚስት
ታትሞ በወጣው መጽሀፍ፣ „The Road to Prosperity“ በሚለው መጽሀፋቸው ውስጥ ይህ ዐይነቱ
የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን በአገሮች ውስጥ እንዴት የሀብት ክፍፍል መዛባት
እንደፈጠረና፣ በዚያው መጠንም ስርዓቱን የሚቀናቀኑ የፋሺሽትና ዘረኛ ድርጅቶች ብቅ ማለት እንደቻሉ
ያመለክታል። በፕሮፌሰሩ ዕምነትና በኢኮኖሚክስ ቲዎሪና በተፈጥሮ ሳይንስ ምርምርም እንደታየውና
እንደተረጋገጠው በታሪክ ውስጥ ዘለዓለማዊነት ያለውና ሊኖረው የሚችል አንድ ዐይነት የኢኮኖሚ
ፖሊሲ የለም። አዳዲስ የህብረተሰብ ግኑኝነቶችና የሚከሰቱ ችግሮች አዳዲስ ቲዎሪና ፖሊሲዎችን የሚሹ
ስለሆነ፣ በተለይም የሳይንስን መንገድ እከተላለሁ የሚል የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን እንደቀኖና
መውሰድና ካለሱ አማራጭ የለም እያለ መስበክ የለበትም። በፕሮፌሰር ሹልማይስተር ዕምነት በኒዎ-
ሊበራሊዝም ላይ የተመሰረተው የማክሮ ኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ ፀረ-ኢንላይተሜንት ነው። ይህም
ማለት በአውሮፓ ምድር ውስጥ ከስድስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ እስከ አስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን
ድረስ የአውሮፓን ህዝብ ጭንቅላት ቆልፎ እንደያዘውና የሳይንስንና የቴክኖሎጂን ዕድገት አጥብቆ
እንደተዋጋው የካቶሊክ ሃይማኖት ቀኖናዊ አስተሳሰብ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የማክሮ
ኢኮኖሚ ፖሊሲ ፀረ-ስልጣኔ ነው። በፕሮፌሰር ሹልማይስተር ዕምነት በኒዎ-ሊበራሊዝም ላይ
የተመሰረተው ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሳይንስ ሳይሆን ርዕዮተ-ዓለም ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ
የሳይንስንና የቴክኖሎጂን ዕድገት መስፋፋትና የብዙ ቢሊዮን ህዝቦችን ህይወት ማቃለል አጥብቆ
የሚቃወም ነው። ድህነትንና ቆሻሻ የመኖሪያ ቦታዎችን በማስፋፋት በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች
አቅመ-ቢስ ሆነው እንዲኖሩ የሚያደርግ ነው። መብታቸውን እንዳያውቁና ለመብታቸውም
እንዳይከራከሩና እንዳይታገሉ ሁኔታዎችን ውስብስብ የሚያደርግ ነው። የፖለቲካና የኢኮኖሚ ልሂቁን
እንዲሳሳት በማድረግ ድህነት እንዲስፋፋ የሚያደርግና ህብረተሰብአዊ ውዝግብ እንዲፈጠር
የሚያስገድድ ነው።

ከዚህ ስንነሳ በተፈጥሮ ሳይንስ አስተሳሰብ ውስጥም በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ሳይንቲስቶች ከቀደመው
ለየት ያለ ሳይንሳዊ ምርምርና መንገድ በማሳየት ለሳይንስ ምጥቀት አመቺ ሁኔታን እንደፈጠሩ
አመልክተዋል። በመሆኑም የዛሬው የኒዎ-ሊበራል ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ
ሊኖረውና ዘለዓለማዊም ሊሆን በፍጹም አይችልም። እያንዳንዱ መንግስትና ማህብረሰብ ለራሱ
ዕድገትና ለህብረተሰብ መተሳሰር የሚያመች የኢኮኖሚ ፖሊሲ የማውጣቱ ጉዳይ የራሱ መብትና
ኃላፊነት ብቻ መሆን አለበት። ማንም የውጭ ኃይል እየመጣ ይህንን አድርግ እያለ አንድን አገር
የማተረማመስና ህብረተሰብአዊ ሰላምን የማደፍረስ መብት የለውም። ምክንያቱም በአንድ አገር ውስጥ
ታሪክ ሊሰራና ተከታታይነትም ሊኖረው የሚችለው በአንድ መንግስት ንቃተ-ህሊናና በአንድ ህዝብ
ቆራጥ ተሳትፎ ስለሆነ ነው። ይህንን መሰረታዊ ሃሳብ ከተመለከትን በኋላ በገበያ ኢኮኖሚና
በካፒታሊስት ኢኮኖሚ መሀከል ያለውን ልዩነት ደግሞ እንመልከት።

በተራ ገበያ ኢኮኖሚና በካፒታሊዝም መሀከል ያለው ልዩነት !!


የገበያ ኢኮኖሚ መቼና የት ቦታ እንደተጀመረ በግልጽ የሚታወቅ ነገር ባይሆኖርም እንደሜሶፖታሚያ
በመሳሰሉት በጊዜው ሻል ያለ መንግስታዊ አወቃቀርና ህገ-መንግስት ባላቸው አገዛዝች የገበያ ኢኮኖሚ
እንደዳበረ የኢኮኖሚ ታሪክ መጽሀፎች ያረጋግጣሉ። በታሪክ ውስጥ ዛሬ የምናውቀውና የምናየው ገበያ
ዐይነት ወይም የገበያ ኢኮኖሚ ከመፈጠሩ በፊት አብዛኛዎች ማህበረሰቦች የሚያመርቱን ምርት
የሚለዋወጡበት መድረክ ነበራቸው። በጥንት ዘመን ይህ ዐይነቱ ገበያ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ሌሎች
ተግባሮችም ነበሩት። ሃሳብ ለሃሳብ የሚለዋወጡበትና ገዢዎችም አዋጅ የሚያስነግሩበትና ፍርድም
የሚሰጡበት መድረክ ነበር። በዕቃ ልውውጥና በገንዘብ ዕድገት የተነሳ ገበያ ከጥንታዊ ባህርይው
በመላቀቅ ምርት ብቻ የሚሸጥበት መድረክ ሆነ።

በአንድ አካባቢ ተሰበጣጥረው ይኖሩ የነበሩ ሰዎችና ከሌላ ቦታ እየመጡ ምርትንም ሆነ እንደጨው
የመሳሰሉትን በመለዋወጥም ሆነ በመሸጥ ለገበያ ኢኮኖሚ የመጀመሪያውን መሰረት እንደጣሉ ታሪክ
ያረጋግጣል። የስራ-ክፍፍል ሲዳብርና አንዳንድ ግለሰቦችም በጀመሩት ሙያ እየገፉ ሲመጡና፣
ያመረቱትንም ምርት ገበያ ላይ አውጥተው ሲሸጡና የተሻለ ጥቅምም ሲያገኙ ምርትን በገንዘብ
መለወጥ ለገበያ መዳበርና መስፋፋት አመቺ ሁኔታን ሊፈጥር ችሏል። በተለይም የሩቅ ንግድ(Far Trade)
ገፊ ኃይል(Catalyst) በመሆን ለገበያ ኢኮኖሚ በዐይነትም ሆነ በብዛት መስፋፋት ዕምርታን
ሰጥቶታል። ይሁንና ግን የንግድ ልውውጥ እንዲካሄድ ደግሞ የሁሉም መለኪያ የሚሆን ነገር ስላስፈለገ
የግዴታ ገንዘብ ለሚለው መሰረተ-ሃሳብ መንገድ ከፈተ። ባጭሩ አብዛኛዎቹ የዓለም ማህበረሰቦች
ወደዛሬው ዐይነቱ የገበያ ኢኮኖሚ ከመሸጋገራቸው በፊት ብዙ ውጣ ውረዶችን እንዳለፉ ታሪክ
ያረጋግጣል። የገበያ ኢኮኖሚ አፍላቂዎች ወይም ፈጣሪዎች የዛሬዎቹ የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት
አገሮችና አሜሪካ እንዳይደሉ የታወቀ ነገር ነው። የገበያ ኢኮኖሚ እዚህና እዚያ መታየቱና ቀስ በቀስም
ዓለም አቀፋዊ ባህርይ መውሰዱ ተፈጥሮአዊ ሂደት ነው ማለት ይቻላል። በመጀመሪያ ሳይታሰብ
የተፈጠረና፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ በስህተትና በልምድ፣ እንዲሁም በመመልከት መልክ እየያዘ የመጣ ነው።
ስለሆነም አዳም ስሚዝ ያዳበረው የገበያ ኢኮኖሚ ክንውንና ዕድገት የሚታይ ነገሮችን በሚገባ
በመቃኘቱ ብቻ ነው። አዳም ስሚዝ በሁሉም መስክ የሚገለጽ ከፍተኛ ምሁራዊ እንቅስቃሴ
በሚታይበትና የኢንዱስትሪ አብዮት በሚካሄድበት ዘመን በ18ኛው ክፍለ-ዘመን የተወለደና የኖረ
በመሆኑ የገበያን ኢኮኖሚ ዕድገትንና የየግለሰቦችን ታታሪነት ጠጋ ብሎ በመመልከቱ „The Wealth of
Nations“ ብሎ የሰየመውን መጽሀፉን መጻፉ ይህን ያህልም የሚያስደንቅ አይደለም። በሌላ ወገን ደግሞ
በ19ኛው ክፍለ-ዘመን የተወለደውና ያደገው ጀርመናዊው ካርል ማርክስ ከሰላሳ ዐመታት በላይ
የካፒታሊዝምን ዕድገት ጠጋ ብሎ ከመረመረና ካጠና በኋላ የደረሰበት ድምዳሜ ካፒታሊዝም ውስጣዊ
ህጎች ያሉት ብቻ ሳይሆን፣ ደረጃ በደረጃ የሚያድግና በቀውስም ሊገለጽ የሚችል ስርዓት እንደሆነ
አመልክቷል። በሱ ዕምነትም ማንኛውም ስርዓት ታሪካዊ እንደመሆኑ መጠን፣ ካፒታሊዝም ለዝንተ-
ዓለም የሚቆይ ስርዓት ሳይሆን ውስጡ ባለው ቅራኔ ሊዳከም እንደሚችልና በሌላ ስርዓት እንደሚተካ
አረጋግጧል። ስለሆነም ካፒታሊዝም ከታች ከተራ የሸቀጣ ሸቀጥ ምርት በመነሳት ቀስ በቀስ እያለ ወደ
ተወሳሰበ የአመራረት ዘዴና የሀብት ክምችት በመሸጋገር በአገር ደረጃ ብቻ መወሰኑን አቁሞ ዓለም
አቀፋዊ ባህርይ ሊወስድ እንደሚችልም አመልክቷል። የገበያ ኢኮኖሚ ወይም ካፒታሊዝም በአንዳች
ዐይነት ኃይል በራስ ፍላጎት ከላይ ወደ ታች የሚወረወር ስርዓት ሳይሆን ቀስ በቀስ ኢቮሉሺነሪ በሆነ
መንገድ የሚያድግና የሚስፋፋ ነው። ስለሆነም ካፒታሊዝም ሊያቆጠቁጥ የቻለው በፊዩዳሉ ስርዓት
ሲሆን፣ እያደገና እየተስፋፋ ሲመጣ አዳዲስ የሀብረተሰብ ኃይሎችን በመፍጠርና የአረጀውን በመጋፋት
የበላይነትን የተቀዳጀ ስርዓት ነው። ስርዓቱም በኢኮኖሚ ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን፣ በህብረተሰብአዊ፣
በፖለቲካ፣ በርዕዮተ-ዓለምና በባህል የሚገለጽ በዐይነት ከፊዩዳሉ ስርዓት የሚለይና ከፍተኛ ውስጠ-
ኃይል(Dynamism) ያለው ነው።

ያም ሆነ ይህ በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ መገበያያ ቦታ ወይም አንዳች ዐይነት የገበያ ኢኮኖሚ


መኖሩ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም። ምክንያቱም ሁሉም ሰው ለኑሮው የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ
ብቻውን ስለማያመርትና በአንድ ህብረተሰብ ውስጥም የስራ-ክፍፍል እንደመኖሩ መጠን የግዴታ ይህ
ዐይነቱ የስራ-ክፍፍል በንግድና እንዲያም ሲል በገንዘብ አማካይነት የሚገለጽና የሚካሄድ ይሆናል ማለት
ነው። የገንዘብ ዕድገትም ከስራ-ክፍፍል መዳበርና ከገበያ ዕድገት ጋር እንደየሁኔታው እያደገና
እየተወሳሰበ የመጣ ነው። በመጀመሪያ አንድን የፍጆታ ዕቃ በሌላ ዐይነት መለወጥ የተለመደ ሲሆን፣
ይህ ዐይነቱ ልውውጥ አመቺ ባለመሆኑ በሁሉም ገበያተኛ ተቀባይነት ያለው አንድ የሁሉም ዕቃዎች
መለኪያ ወይም መመዘኛ የሆነ ገንዘብ አስፈለገ። ከአንድ የዕቃ ዐይነት ተነስቶ፣ ከመዳብና ከነሃስ፣
ከዚያም በኋላ ከብርና ከወርቅ የተሰራ የንጉሶች ስዕልና ማህተም ያለበት የቀለጠ ብርና ወርቅ እንደገንዘብ
በማገልገል ለገበያ ዕድገት መልክ ሰጥተውታል። ወርቅና ብር እያደገና እየተወሳሰበ ከመጣው የኢኮኖሚ
እንቅስቃሴ ጋር ለመጓዝ ባለመቻላቸውና በጊዜው እንደልብ የሚገኙ ስላልነበር በወርቅ የተደገፈና
የመንግስታት ማረጋገጫነት ያለው የወረቀት ገንዘብና ሳንቲሞች እየታተሙ መገበያያ መሳሪያዎች መሆን
ቻሉ። በተለይም በ18ኛው ክፍለ-ዘመን በእንግሊዝ አገር የኢንዱስትሪ ምርት ሲያድግና የንግድ ልውውጥ
ሲስፋፋ ወርቅና ብርን በብዛት አትሞ በኢኮኖሚው ውስጥ ለማሽከርከር አልተቻለም። ወርቅና
ብር(Silver) የተፈጥሮ ሀብቶች በመሆናቸውና እንደልብም ስለማይገኙ በገበያ ላይ በየጊዜው የገንዘብ
እጥረት ይከሰት ነበር። ይህንን ሁኔታ ጠጋ ብለው የተመለከቱ የተገለጸላቸው ምሁሮች የመጣላቸው
ሃሳብ በወርቅ የሚደገፍ የወረቀት ገንዘብ እያተሙ ማቅረብ አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን
በመረዳት ለመጀመሪያ ጊዜ በእንግሊዝ አገር የመንግስት ዋስትና ያለበት የወረቀት ገንዘብ በማተም
በኢኮኖሚው ውስጥ ማፍሰስ ጀመሩ። የወረቀት ገንዘብ በእርግጥም አመቺና ከሁኔታው ጋር የሚጓዝ
በመሆኑ የኢንዱስትሪ ምርትንና ንግድን ማፋጠን ተቻለ። ሌሎች አገሮችም ከእንግሊዝ በመማር
በመንግስት የሚደገፍና ወርቅ የጀርባው አጥንት የሆነ የወረቀት ገንዘብ በማተም የኢኮኖሚ ዕድገትን
ማፋጠን ቻሉ።

ዛሬ የምናየው የተለያየ የገንዘብ ዐይነት የረጅም ጊዜ የገበያ ዕድገት ውጤት ነው ማለት ይቻላል። ልዩነቱ
በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ ሰፋ ባለ የማኑፋክቸር እንቅስቃሴና ሰፋ ባለና ግልጽ በሆነ የገበያ ኢኮኖሚ መደገፉ
ለገንዘብ ጠንካራነት ተቀባይነት አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል ማለት ይቻላል። የማኑፋክቸር እንቅስቃሴ
ባልተስፋፋባቸው፣ የውስጥ ገበያ ባልዳበረባቸው፣ የምርት ክንውን በሳይንስና በቴክኖሎጂ
በማይደገፍበት፣ ከተማዎችና መንደሮች ለሰው መኖሪያ ሆነው በደንብ ባልተገነቡበት፣ እነዚህም በተለያዩ
የመመላለሻ መንገዶች ባልተሳሰሩበት በየአገሮች ውስጥ የሚሽከረከረው ገንዝብ ጥንካሬነት የለውም።
በተጨማሪም ለአንድ አገር የገንዘብ መጠንከር አብዛኛው ህዝብ ተቀጥሮ የሚሰራና፣ በሚያገኘው የወር
ደሞዝ ማንኛውንም ለኑሮው የሚያስፈልጉትን ነገሮች ገዝቶ የሚጠቀም ከሆነ የገንዝብ መሽከርከር
ፍጥነት(Velocity of Money) መጨመር ለገንዘብ መጠንከር ዋናው ምክንያት ይሆናል። በሌላ ወገን ግን
የሁሉም አገሮች የወረቀት ገንዘቦች ውስጣዊ ዋጋ(Intrnisic Value) የላቸውም። ለምሳሌ ኦይሮ ከጥጥ
ሲታተም፣ ሌሎች አገሮች ደግሞ በቀላሉ ሊቀደድ ወይም በአየር ጠባይ መለዋወጥ የተነሳ ሊበላሽ
ከማይችል ፖልይሜር ከሚባል ልዩ ዐይነት የኬሚካል ውጤት የሚታተም ገንዘብ ነው። ከህትመት ዋጋ
ጉዳይ አንዳንዶች ጠንከር ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊበላሹ ወይም ሊቀደዱ ይችላሉ።
ከዚህ ስንነሳ የአሜሪካን ዶላርና ኦይሮ ታሪካዊ እንጂ ዘለዓለማዊ አይደሉም። ከራሳቸው አገሮች አልፈው
ለሌላ አገር የውስጥ ገበያ ዕድገትና ለኢኮኖሚው መተሳሰር አስተዋፅዖ ሊያበረክቱ አይችሉም። የሁሉንም
ኢንዱስትሪ አገሮች ዕድገት ስንመለከት፣ በመጀመሪያ እንግሊዝ የወረቀት ገንዘብ በማተም ነው
የኢንዱስትሪ ዕድገትንና የውስጥ ገበያን ማስፋፋት የቻለችው። እንዲሁም የአሜሪካ ዶላር የዓለም ንግድ
መገበያያ ገንዘብ ከመሆኑ በፊት በመታተምና በክሬዲት ሲስተም በመሰራጨት ነው በኢንዱስትሪና
በቴክኖሎጂ ምጥቀትን ሊያገኝ የቻለው። በጊዜው የጆርጅ ዋሽንግተን የገንዘብ ሚኒስተር የነበረው
አሌክሳንደር ሃሚልተን የመንግስት ሴኩሪቲ በማተምና ገንዘብ ካላቸው ገንዘብ በመበደር ነው
በማኑፋክቸር ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪ አብዮት ማካሄድ የቻለው። ጀርመንም በተለይም
ከእንግሊዝ በመማርና የራሷን የባንክ ሲስተም በማቋቋምና የክሬዲት ስርዓት በመፍጠር ነው ቀስ በቀስ
የኢንዱስትሪ አብዮት ያካሄደችውና በአንድ ትውልድ ጊዜ ውስጥ እንግሊዝን በቴክኖሎጂ ቀድማ መሄድ
የቻለችው። ይህ ሁሉ የሚያረጋግጠው ከሌሎች ነገሮች ጋር በመደመር ለአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት
ዋናው አንቀሳቃሽ ኃይል ዶላርና ኦይሮ ወይም ሌላ የውጭ ገንዘብ ሳይሆን የአንድ አገር ገንዘብ ብቻ ነው።
በተጨማሪም አንድ አገር ከውጭ አገር በመበደር ሰፋ ያለና ስርዓት ያለው፣ እንዲሁም በሳይንስና
በቴኮኖሎጂ የተመሰረተ የካፒታሊስት ወይም የገበያ ኢኮኖሚ ያዳበረበት አገር የለም። በተለይም
ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተቋቋመው የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ የሚያረጋግጠው
ዕዳ(International Debt) የየአገሮችን ሀብት መምጠጫ ወይም መዝረፊያ መሳሪያ በመሆን ለኋላ-
ቀርነት ወይም ግልጽ ለሆነ፣ በስራ-ክፍፍል ላይ ለተመሰረተ የገበያ ኢኮኖሚ አለማደግ ዋናው ምክንያት
እንደሆነ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።

የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም የንግድ መለዋወጫ ገንዘብ የእንግሊዝ ፓውንድ ሲሆን፣
ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ደግሞ ዶላር የዓለም ንግድ መገበያያና የሀብትም ማጠራቀሚያ ገንዘብ
ሊሆን ችሏል። ፓውንድና ዶላር የዓለም ንግድ መገበያያ ገንዘብ ብቻ ሳይሆኑ የበላይነትን መግለጫና
ማረጋገጫ መሳሪያዎችም ናቸው። ስለሆነም የደካማ አገሮችን የጥሬ-ሀብት መቆጣጠሪያ መሳሪያ
ለመሆን በቅተዋል። ለምሳሌ እንግሊዝ ኃያል መንግስት እስከነበረችበት እስከ 1930ዎቹ ዓመታት ድረስ
ፓውንድ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት የነበረው የንግድ መለዋወጫ ገንዘብ ነበር። እንግሊዝ የበላይነቷን
በአሜሪካን ስትነጠቅ በ1944 ዓ.ም በብሬተንስ ውድስ ስምምነት ላይ የእንግሊዙ ተወካይ የነበረው
ኬይንስ አንድ ከሁሉም አገር ነፃ የሆነ፣ በተለያዩ አገሮች ከረንሲዎች የሚደገፍ „ባንኮር“ የሚባል
አርቲፊሻል ገንዘብ የንግድ መለዋወጫ መሆን አለበት ብሎ ሲከራከር፣ የአሜሪካንን መንግስት ይወክል
የነበረው ኋይትስ የሚባለው እምቢ በማለቱ ዶላር የዓለም ንግድ መለዋወጫና የሀብት ክምችት መሳሪያ
ለመሆን በቃ። በጊዜው አሜሪካ ሰፋ ያለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚደገፍ ትልቅ ገበያ ስለነበረው፣
በውጭ ንግድም ትርፋማ በመሆኑና ከሌሎች አገሮችም ጋር ሲወዳደር ብዙ የወርቅ ክምች ስለነበረው
ዶላር በዓለም አቀፍ ደረጃ የንግድ መለዋወጫ ገንዘብ መሆን አለበት ብሎ መከራከሩ የሚያስገርም
አይደለም።

ያም ሆነ ይህ መሰረታዊው ጥያቄ በሁሉም ማህበረስቦች ውስጥ የገበያ ኢኮኖሚ ብቅ ቢልምና ቢያድግም


ለምድንነው ወደ ካፒታሊዝም ሊለወጥ ያልቻለው ? ለሚለው መመለስና መታወቅ ያለበት ጉዳይ ነው።
ምክንያቱም በተለይም ወደ ኋላ የቀሩ አገሮች የካፒታሊዝምን አነሳስና ዕድገት መረዳት ከቻሉ በቀላሉ
ለራሳቸው የሚስማማ የህብረተሰብ ፕሮጀክት መንደፍ ስለሚችሉ ነው። ይሁንና ግን እዚህ ላይ መዘርዘር
አንባቢውን ማስልቸት ብቻ ሳይሆን፣ በተወሰኑ ቃላቶችና በግብዝነት ምክንያቱ እንደዚህ ነው ብሎ በቂ
ትንተና ወይም መልስ መስጠት በፍጹም አይቻልም። ስለካፒታሊዝም አነሳስና ዕድገት ሰፊ ሀተታ
መስጠት በዚህ አጭር ጽሁፍ ላይ አስፈላጊ አይደለም።

ያም ሆነ ይህ ተራ የገበያ ኢኮኖሚና ካፒታሊዝም አንድ አይደሉም። አብዛኛዎች የዓለም ማህበረሰቦች


የገበያ ኢኮኖሚ ቢያዳብሩም ሁሉም አገሮች ወደ ካፒታሊዝም ሊሸጋገሩ አልቻሉም። በአውሮፓ ምድር
ከረጅም ጊዜ ጭፍን የሆነ የካቶሊክ ሃይማኖት አገዛዝ በኋላ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በፍልስፍና፣ በህንፃ
አገነባብና በስዕል የሚገለጽ የመንፈስ ተሃድሶ(Renaissance)፣ ቀጥሎም የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ብቅ
ማለትና የካቶሊክን ዶግማ መቀናቀንና ቀጥሎም መስበር፣ ከዚያም በኋላ በሳይንስ የሚገለጽ ሰፋ ያለ
ምሁራዊ እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ በነፃ ለማሰብ አመቺ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ። በዚያው መጠንም ስርዓት
ያላቸው ከተማዎች ሲገነቡና የዕደ-ጥበብ ስራ ሲያብብና፣ እነዚህ ከተፈጥሮ ሳይንስ ጋር በመዳበል
ለካፒታሊዝም መሰረት ይጥላሉ። ይህ ዐይነቱ እንቅስቃሴ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ እንግሊዝ አገር
በኢንዱስትሪ አብዮት በመገለጽ ህብረተሰብን በማመሰቃቀልና ከጥንታዊ የአሰራር ስልት በማላቀቅ ቀስ
በቀስ ለካፒታሊዝም ስልተ-ምርት መንገዱን ያመቻቻል። ሌሎች አገሮችም የኢንዱስትሪን አብዮት
እንደምሳሌ በመውሰድ ኋላ-ቀር ከሆነ የአመራረትና የአኗኗር ስልት በመላቀቅ የቴክኖሎጂ ዕድገትን
ያፋጥናሉ። አንዱ ከሌላው በመኮረጅና ሃሳብ ለሃሳብ በመለወዋጥ በተለይም የሃሳብ ፍሰት በቀላሉ
ሊስፋፋ በሚችልበት ምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ካፒታሊዝም ሊያድግና ሊስፋፋ ቻለ። ስለሆነም
ካፒታሊዝም ከተራ የገበያ ኢኮኖሚ በዓይነትም ሆነ በውስብስብነት እጅግ በላቀ መልክ ይለያል።

ባጭሩ ካፒታሊዝም፣

1ኛ) በግል ሀብት የሚገለጽ ነው። በተለይም በኢንዱስትሪ ምርት ላይ የሚያተኩር ነው።

2ኛ) በኢንዱስትሪ ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ ሰራተኛ መኖር አለበት። የሰው ጉልበት ዋናው የትርፍ
ምንጭ ነው።

3ኛ) በኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚመረተው ምርት በቀጥታ ገበያ ላይ ወጥቶ የሚሸጥ ስለሆነ የዋጋና
የወጪ ስሌት

ያስፈልገዋል። ይህም ማለት ማንኛውም አምራች የሚያመርተው ትርፍ ለማግኘት እንጂ


በመጀመሪያ ደረጃ

የህብረተሰብን ፍላጎት አሟላለሁ ብሎ አይደለም። ስለሆነም የወጪውንና የገቢውን ጉዳይ ማስላት


አለበት።

4ኛ)በአምራቾች መሀከል ውድድር መኖር አለበት። በውድድር አማካይነት ብቻ ነው የቴክኖሎጂ


ምጥቀት ሊታይ

የሚችለው።

5ኛ) በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ውስጥና(Interindustry Trade) በጠቅላላው አንድ አገር ኢኮኖሚ ውስጥ
የስራ-ክፍፍል

መኖር(Intraindustry Trade) ለካፒታሊዝም ዕድገት እጅግ ወሳኝ ነው። በዚህ አማካይነት መተሳሰር
ሲኖር፣

ዕድገቱም ይፋጠናል።

6ኛ) የፍጆታ ዕቃዎችን በሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችና በማሺን ኢንዱስትሪና እንዲሁም


ኢንዱስትሪዎችን ዲዛይን አድርገው

በሚያቀርቡ መሀከል ግልጽ የሆነ የስራ ክፍፍል መኖር አለበት። በእነዚህ ሁለት ክፍሎች
(Department1 &

Department II) መሀከል ግልጽ የሆነ የስራ-ክፍፍል ሲኖር ካፒታሊዝም በዐይነትም ሆነ በብዛት
ማደግ ይችላል።

7ኛ) ካፒታሊዝም ሊያድግና ሊስፋፋ የሚችለው ከመንደር ባህርይው ተላቆ በአገር ደረጃ ሲካሄድ ብቻ
ነው።
8ኛ) ለዚህ ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ በደንብ የተሰሩ የማመላለሻ መንገዶች መኖር አለባቸው።
በመጀመሪያ የባቡር ሃዲድ

ሲዘረጋ፣ ቀስ በቀስ ቴክኖሎጂው እያደገ ሲመጣ መኪናዎችን ለመንዳት የሚያስችሉ ሰፋፊ መንገዶች
መሰራት አስፈለገ።

9ኛ) የባንክ ሲስተም መስፋፋትና እንደየኢኮኖሚው ዕድገት አስፈላጊነት ገንዘብ እያተሙ ማቅረብ
ለካፒታሊዝም ዕድገት

አመቺ ሁኔታን ሊፈጥር ቻለ። በዚህ መልክ ገንዘብ የመገበያያ መሳሪያ ከመሆን አልፎ፣ ዕቃዎች
የሚተመኑበትና ሀብት

ማጠራቀሚያ መሳሪያ ሊሆን በቃ። በሌላ አነጋገር ገንዝብ ባንክ ውስጥ ሲቀመጥ ወለድ
ስለሚገኝበት ይህ ሁኔታ

ለሀብት ክምችት ዐይነተኛ መሳሪያ ሊሆን ቻለ። በገንዘብ አማካይነት ዕቃን ወይም ቤትን
መግዛትና፣ የግልን ሀብት ወደ

ገንዘብ መለወጥ ተቀባይነት ያለው የካፒታሊዝም ክንዋኔ ደንብ ነው።

10ኛ) ለካፒታሊዝም በፍጥነት ማደግና መስፋፋት ብድር (Credit) ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። በመዋዕለ-

ነዋይ(Investment) ላይ ለመሰማራት የሚፈልጉም ሆነ በሂደት ላይ ያሉ ካፒታሊስቶች ክንዋኔያቸውን


ለማስፋፋት

የሚችሉት ከባንክ በብድር አማካይነት ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘት ሲችሉ ብቻ ነው። በዚህ መልክ
በኢንዱስትሪዎችና

በባንኮች መሀከል በብድር አማካይነት ግኑኝነት ሲፈጠር፣ ገንዘብ በፍጥነት መሽከርከሩ ብቻ ሳይሆን
ባንኮች

በሚያገኙት ወለድ እያደጉና የካፒታሊስቶችንና የተቀረውን ህዝብ ህይወት እየወሰኑ ለመምጣት


ይችላሉ። ከዚህ

በተጨማሪ በደሞዝ የሚተዳደረው በተለይም የረጅም ዕድሜ ያላቸውን ዕቃዎች፣ ለምሳሌ


እንደመኪናና ሌሎች

ቁሳቁሶችን ለመግዛት የግዴታ ከባንክ ገንዘብ(Consumer Credits) ይበደራል። በዚህ መልክ


የሚመረቱና ገዢ

የሚጠባበቁ ነጋዴዎች በማከማቻ ቦታዎች ውስጥ ያላቸውን ዕቃዎች ቶሎ ቶሎ የመሸጥ ዕድል


ያጋጥማቸውል። ይህ
በራሱ ደግሞ መኪናዎችንና ሌሎች ዕቃዎችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን ቶሎ ቶሎ እንዲያመርቱ
የበለጠ

ይገፋፋቸዋል።

11ኛ) ካፒታሊዝም ሊያድግ የሚችለው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ምርምር ላይ የተደገፈ የሆነ እንደሆነ ብቻ
ነው። ይህም

ማለት አዳዲስና ጥራት ያላቸው፣ እንዲሁም በአነስተኛ ዋጋ ለማምረት ወይም የጥሬ-ሀብት


ለመቆጠብ የግዴታ

ምርታማነትን የሚያሳድጉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በየጊዜው መፈጠርና በስራ ላይ መሰማራት


አለባቸው።

12ኛ) ይህ ዐይነቱ ውድድርና የቴክኖሎጂ ምጥቀት ሲታይ የምርት ክንውን የግዴታ ለትላልቅ
ኢንዱስትሪዎች በሩን

ይከፍታል። ለምሳሌ እንደባቡርና መኪና ፋብሪካዎች። ይህ በራሱ ደግሞ ከሌሎች የተለያዩ


የመለዋወጫ አምራች

ኢንዱስትሪዎች ጋር ሲያያዝ ለካፒታሊዝም ዕድገት ልዩ ዕምርታን ይሰጠዋል። ዕድገቱ በዐይነትም


ሆነ በቁጥር

ይጨምራል።

13ኛ) በዚህ መልክ በአንድ አካባቢ ያደገውና የተስፋፋው ካፒታሊዝም በአገር ደረጃ ብቻ ስለማይወሰን
የግዴታ ዓለም

አቀፋዊ ባህርይ ይወስዳል። የካፒታሊዝም ዓለም አቀፋዊ ባህርይ መውሰድ ደግሞ ሌሎች አገሮችን
ወደ ጥሬ-ሀብት

አምራችነትና ወደ ፕላንቴሽን ኢኮኖሚ ይቀይራቸዋል።

14ኛ) ሰለሆነም የሶስተኛው ዓለም ተብለው የሚጠሩ አገሮች ለካፒታሊዝም ዕድገት የሀብት ክምችት
መሰረት በመሆን

በዓለም አቀፍ ደረጃ ያልተስተካከለ ዕድገትና የንግድ ልውውጥ ሊፈጠሩ ቻሉ። በዚህ መልክ ግሎባል
ካፒታሊዝም

የዓለምን ማህበረሰብ ዕድል ወሳኝ ለመሆን ችሏል። ከሞላ ጎደል በተራ የገበያ ኢኮኖሚና
በካፒታሊዝም መሀከል

ያለው ልዩነት ይህንን ነው የሚመስለው። የካፒታሊዝም ዕድገትና ውስጣዊ ይዞታ ከተመለከትን


በኋላ፣ ካፒታል ወደ
ውጭ በመዋዕለ-ነዋይ ስም ሲንቀሳቀስ በየአገሮች ውስጥ ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት ደግሞ
በሚቀጥለው ርዕስ

እንመልከት።

ከውጭ የሚመጣ መዋዕለ-ነዋይ የአንድን አገር ኢኮኖሚ


ማሳደግ ይችላል ወይ ?
ከውጭ የሚመጣ የመዋዕለ-ነዋይ(Direct Foreign Investment)የተለያየ መልክ አለው። I. በአንድ
የአገልግሎት መስጫ ወይም አምራች ድርጅት ውስጥ ድርሻ(Share) መግዛት ሲሆን፣ ድርሻን የሚገዛ
ግለሰብም ሆነ ድርጅት ተጽዕኖ ለማሳደር ቢያንስ 10% የሚሆነውን ከአገልግሎት መስጫ ውስጥ
መግዛት አለበት። II. ኢንዱስትሪዎችን ወስዶ በቀጥታ መትከልና ምርት እዚያው አገር ውስጥ እንዲመረት
ማድረግ። ለዚህ ዋናው ምክንያት፣ 1ኛ) የማምረቻን ዋጋ ለመቀነስ ሲሆን፣ በተለይም የስራ አበልን
ይመለከታል። በአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የሚመረቱት፣ በተለይም እንደጨርቃ ጨርቅና
ጫማ የመሳሰሉት ምርቶች በርካሽ ጉልበት የሚመረቱና በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የሚሸጡ ናቸው። ይህ
ዐይነቱ ርካሽ ጉልበት የትርፍ ትርፍ(Surplus Value) ዋናው ምንጭ ነው። 2ኛ) ከዚህ ባሻገር አብዛኛዎቹ
የሶስተኛው ዓለም አገሮች በፋብሪካ ደረጃና በአገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀ የሰራተኛው የሙያ ማህበር
የላቸውም። ቢኖራቸውም በጣም የተዳከመ ነው። የተጠናከረና የተደራጀ ምሁራዊ ባህርይ የሌለው
እንቅስቃሴ በሌለበት አገር ውስጥ የውጭ ኩባንያዎች ኢንዱስትሪዎቻቸውን አምጥተው በመትከል
ምርት እንዲመረት ያደርጋሉ። 3ኛ) የማህበራዊና የኢኮሎጂ ስታንደርድ በማይጠበቅበት ወይም የጠበቀ
ህግ በሌለባቸው አገሮች ትላልቅ ኩባንያዎች ኢንዱስትሪዎቻቸውን አምጥተው በመትከል ምርትን
ያመርታሉ። 4ኛ) የቀረጥ ዝቅተኛ መሆንና ትርፍን እዚያው እንደገና መልሶ ለመዋዕለ-ነዋይ አለማዋል
ወይም ወደ ውጭ ማውጣት ሌላው የውጭ ኩባንያዎችን የሚገፋፋ ጉዳይ ነው። ስለሆነም የሚያገኙትን
ትርፍ ሳይቀረጥ እንዳለ ወደ ውጭ ማውጣት ይችላሉ። የገቢ ቀረጥ እንዲከፍሉ በሚገደዱባቸው አገሮች
ደግሞ ከአገሮቻቸው የሚያመጡትን ኢንዱስትሪዎቻቸውንና የመለዋወጫ ዕቃዎችን ዋጋ ከፍ
በማድረግና የማምረቻ ዋጋን ከፍ አድርጎ በማስላት ኢንዱስትሪው ዝቅተኛ ትርፍ እንዳገኘ አድረገው
በማቅረብ ድብቅ በሆነ መልክ ትርፍ ወደ ውጭ እንዲወጣ ያደርጋሉ። III. ሌላው የውጭ መዋዕለ-
ነዋይ(FDI) አካል የሆነው የተለያዩ መገጣጠሚያዎችን በተለያዩ አገሮች ማምረትና ኩባንያው ተቀማጭ
በሆነበት አገር ውስጥ አንድን ትልቅ ምርት ገጣጥሞ ለገበያ ማቅረብ ነው። በተለይም እንደዚህ ዐይነቱ
የመኪናን ምርት ይመለከታል። IV. ሌላው ቀጥተኛ የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ ዐይነት የጥሬ-ሀብትን
ማውጣትና እንዳለ ወደ ካፒታሊስት አገሮች፣ ወደ ቻይናና፣ እንዲሁም ወደሌሎች በዕድገት ላይ የሚገኙ
እንደ ህንድ ወደመሳሰሉት አገሮች መጫን ነው። በተለይም በዚህ ዐይነቱ የጥሬ-ሀብት ቁፋሮ የሚሰማሩ
ትላልቅ ኩባንያዎች(Multinational Companies) ከጥፋት በስተቀር ለአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት
የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ከዜሮ በታች ወይም አሉታዊ ነው ማለት ይቻላል። በጥሬ-ሀብት ቁፋሮ ውስጥ
የሚሰማሩት ሰራተኞች የሚያገኙት ደሞዝ በጣም ዝቅተኛ ነው። በሙያ ማህበር የመደራጀት
መብታቸውም እንደዚሁ ዝቅ ያለ ነው። ኩባንያዎቹ በሚሰማሩባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ
የአካባቢና የማህበራዊ ቀውስን ያስከትላሉ። በመጥፎ ድርጊታቸውም በህግ የሚጠይቃቸው መንግስት
ወይም መስሪያ ቤት የለም። V. ሌላው የውጭ ኩባንያዎች የመዋዕለ-ነዋይ እንቅስቃሴ በአበባ ተከላ
ላይና በሌሎች ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ የእርሻ ምርቶች ላይ ያተኮረ ነው። የአበባ ተከላ ደግሞ ለአንድ
አገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ዜሮ ነው ማለት ይቻላል። ምክንያቱም አበባ
ለጠቀሜታ በፋብሪካ ውስጥ በመፈበረክ ለምግብነት ስለማይውል ነው። በዚህ መልክ የአንድ አገር
ድንግል መሬት ለምግብ የሚሆኑ ሰብልና ፍራፍሬዎች ከሚበቅሉበት ይልቅ የኢንዱስትሪ አገሮችን ሰዎች
ለማስደሰት ሲባል የተለያዩ መርዛማ የሆኑ ኬሚካሎች እየተረጨበት አካባቢ ይወድማል፤ በዚያ
ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ደግሞ ለበሽታ ይደረጋሉ። የአበባን ተከላንና ጠንቁን አስመልክቶ በአቶ
መሳይ አዱኛ ካሳዬ በቀረበው የምርምር ውጤት መሰረት የአበባ ተከላ በተስፋፋባቸው አካባቢዎች
የሚረጨው የተባይ ማጥፍያ መድሃኒት በሰውና በአካባቢው ላይ የጤንነትን መቃወስና መዛባትን
ሲያደርስ፣ ማዳበሪያው ደግሞ በመሬት ውስጥ የሚገኘውን ውሃና ወንዞችን ሊበርዝ ችሏል።
በተጨማሪም አበባውን ለማጠጣት እየተባለ በብዛት የሚረጨው ውሃ ከመሬት ውስጥ የሚገኘውን
የውሃ መጠን በከፍተኛ ደረጃ እንደቀነሰው ጥናቱ ያመለክታል። ይህ ብቻ ሳይሆን ለእርሻ ምርት
ምርታማነትና ለማር ምርት የሚያገለግሉ ነፍሳትና ንቦች በጅምላ እየወደሙ እንደሆነ ጥናቱ ይጠቁማል።
መስኩ ለ85 000 ሰራተኞች የስራ መስክ የከፈተ ቢሆንምና፣ አገሪቱም አበባን ወደ ውጭ በመላክ በዓመት
ወደ $200 ሚሊዮን የሚጠጋ የአሜሪካን ዶላር ብታገኝም የዚህ ንዑስ መስክ መስፋፋት ከጥቅሙ ይልቅ
ጉዳቱ እንደሚያመዝን ነው ጥናቱ የሚያረጋግጠው። በሌላ አነጋገር፣ የአበባ ተከላና የሌሎች ፕላንቴሽን
ኢኮኖሚዎች መስፋፋት እርስ በእርሱ ለተሳሰረና ሰፋ ባለመልክ ለሚገለጽ የስራ-ክፍፍል መዳበርና
ለማህበረሰብ ምስረታ እንቅፋት ነው። የገበያ ኢኮኖሚ ወይም ካፒታሊዝም ሊያድግ አይችልም። መስኩ
የዓለም ካፒታሊዝም ተቀጥያና የካፒታሊስት አገሮችን በሀብት የሚያደልብና የተስተካከለና ተከታታይነት
የሚኖረውን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚፃረር ነው።

በአጠቃላይ ሲታይ የእርሻ ምርት ውጤት እንዳለ ወደ ውጭ ስለሚላክ በዚያ ምርቱ በተመረተበት አገር
ውስጥ እርስ በእርሱ የተሳሰረ(Value Added Chain) የኢንዱስትሪ ዕድገት እንዳይዳብር ይደረጋል።
ለምሳሌ የአገራችንን ቡና ተፈጭቶና ታሽጎ ቢላክ የሚሰጠው ጥቅም፣ 1ኛ) የአገር ውስጥ ገበያ ሊስፋፋ
ይችላል፤ 2ኛ) ከውጭ የሚገኘው ምንዛሪ ከፍ ያለ ይሆናል። 3ኛ) የቡና አምራቹም ገቢ በየጊዜው ያድጋል፤
4ኛ) ቡናን እየቆላ፣ እየፈጨና አሽጎ ወደ ውጭ የሚልክ ፋብሪካ ተጨማሪ የሰው ኃይል ስለሚያስፈልገው
ለሰራተኞች የገቢ ምንጭ ይሆናል፤ 5ኛ) የተፈጨውን ቡና ማሸጊያ ልዩ ዐይነት የማሸጊያ ወረቀት
ስለሚያስፈልግ ማሸጊያውን የሚያመርት ፋብሪካ ይቋቋማል። በዚህ መልክ እርስ በእርሱ የተያያዘ
የምርት ክንውንና ተከታታይ ገቢ ለአገር ውስጥ ገበያ መስፋፋት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። ይሁንና ግን
የአገር ውስጥ ገበያ እንዲስፋፋ ጥረት ከማድረግ ይልቅ በችለተኝነት ወይም ካለማወቅ የተነሳ የአገር
ውስጥ ሀብት በቀላሉ ይባክናል፤ የአገር ውስጥ ገበያም እንዳያድግ ከፍተኛ መሰናክል ይፈጠራል።

ያም ተባለ ይህ የውጭ ኩባንያዎች በቀጥታ የመዋዕለ-ነዋይ እንቅስቃሴ በሚያደርጉባቸው አገሮች


ውስጥ ለየአገሩ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ እጅግ ዝቅተኛ ነው። ከአንዳንድ አገሮች
በስተቀር፣ በተለይም እንደቻይና ከመሳሰሉ ጠንካራ፣ ብልህና የመደራደር አቅም ካላቸው መንግስታትና
አገሮች በስተቀር በአፍሪካ ውስጥ የሚካሄዱት የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔዎች ለዕድገትና ለህብረተሰብ
ለውጥ የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ እጅግ ዝቅተኛ ወይም አሉታዊ ነው ማለት ይቻላል። 1ኛ) ሁሉም
ኩባንያዎች ምርምራቸውን የሚያካሂዱት በየአገሮቻቸው ውስጥ ስለሆነ የቴክኖሎጂ መተላለፍ
(Transfer of Technology) አይኖርም። ይህም ማለት አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ለዕድገታቸው
የሚያመቻቸውን ቴክኖሎጂ ሊኮርጁና ሊጠቀሙበት አይችሉም። 2ኛ) አብዛኛዎቹ ኢንዱስትሪዎች አገር
ውስጥ ካሉ ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ጋር በቀጥታ የሚያያዙ አይደሉም። ተነጥለው የሚካሄዱ የኢኮኖሚ
እንቅስቃሴዎች በመሆናቸው ለአጠቃላይ የሀብት ክምችት የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ አልቦ ነው ማለት
ይቻላል። 3ኛ) በእነዚህ ኢንዱስትሪዎች፣ የጥሬ-ሀብት ማውጫዎችና የአበባ ማሳዎች ውስጥ ተቀጥረው
የሚሰሩት ሰራተኞች ደሞዛቸው በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ ራሳቸው የሚያመርቱትን ወይም ደግሞ ዘመናዊ
ከሚባለው መስክ የሚመረተውን ምርት ገዝተው የመጠቀም ኃይል የላቸውም። 4ኛ) የአገር ውስጥ
ገበያን አያስፋፉም ወይም ለማዳበር አይችሉም። 5ኛ) አብዛኛውን ጊዜ ከባንኩ መስክ ጋር ምንም ዐይነት
ግኑኝነት የላቸውም። ስለሆነም ለባንክ ዕድገትና ለገንዘብ በፍጥነት መሽከርክር ምንም አስተዋፅዖ
አያበረክቱም። ከዚህና ከሌሎች አያሌ ምክንያቶች ስንነሳ ቀጥተኛ የሆነ የውጭ የመዋዕለ-ነዋይ
እንቅስቃሴ(Direct Foreign Investment) ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። አንድን ህብረተሰብ
ከማዘበራረቅና ማህበራዊ ቀውስ እንዲፈጠር ከማድረግ በስተቀር የዕድገት አራማጅ አይሆንም። የውጭ
ኩባንያዎች በሚንቀሳቀሱባቸው የሶስተኛው ዓለም አገሮች በሙሉ የሰብአዊ መብት ረገጣ የተስፋፋና፣
ሰራተኞችም በአገራቸው ውስጥ እንደሁለተኛ ዜጋ የሚቆጠሩ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ በሶስተኛው ዓለም
አገሮች ውስጥ አምባገነናዊና ፋሺስታዊ አገዛዞች የሚነሱትና የሚጠናከሩት ከካፒታሊስት አገሮች ጋር
ስለሚቆላለፉና በጥቅም ስለሚገዙ ነው። ስለሆነም የየአገሩ መንግስታትም የሚያደሉት ለውጭ
ኩባንያዎች እንጂ ለአገራቸው ህዝቦች አይደለም።

ብዙ የሚወራለትን የሃዋሳን የኢንዱስትሪ ፓርክ(Hawassa Industrial Park) ደግሞ እንመልከት።


የኢንዱስትሪ ፓርኩ በ 9 ወራት ጊዜ ውስጥ እ.አ.አ በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ተጠናቆ ስራውን የጀመረ
ነው። ፓርኩ በቻይናዎች የተሰራ ሲሆን፣ ከቻይና ኩባንያዎች በተጨማሪ ፊሊፕስ ቫን ሆይሰን
ኮርፖሬሽን(PVH) የሚባል ዘመናዊ ልብሶችን በመስፋትና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሸጥ የአሜሪካ
ኩባንያ ልብሶችን በሃዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ ያሰፋል። ኢንዱስትሪዎቹ የሚያመርቱት በብዛት የጨርቃ
ጨርቅ ውጤቶችና ጫማዎች ሲሆኑ፣ ጥጥና ፈትሎችም ሆነ ልዩ ልዩ የመለዋወጫ ዕቃዎች ከቻይና
የሚመጡ ናቸው። ከኢትዮጵያ የሚገዙት የጥሬ-ሀብት ሶዲየም ሀይድሮክሳይድ ብቻ ነው። ኩባንያዎቹ
ከኢትዮጵያ የሚገዙት የጥሬ-ሀብት ከቻይናው ጋር ሲወዳደር ውድ ስልሆነ ሶዲየም ሀይድሮክሳይድን
ከቻይና ለማስመጣት በማውጣት በማውረድ ላይ ናቸው። በእነዚህ ፋብሪካዎቹ ውስጥ የሚመረቱት
ምርቶች ለውጭ ገበያ ተብለው ስለሆነ እዚያው ተቀጥረው የሚሰሩት ሰራተኞች የሚከፈላቸው ደሞዝ
በጣም ዝቅተኛ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰራተኛ በወር 650 የኢትዮጵያ ብር፣ በዶላር ደግሞ $ 22 ብቻ
የሚከፈለው ሲሆን፣ ይህ ደሞዝ አንድ ተመሳሳይ ስራ ከሚሰራ ቻይናዊ ጋር ሲወዳደር አንድ አራተኛውን
ብቻ የሚያክል ነው። በሌላ ወገን የውጭ ሰራተኞች ከፍተኛ ደሞዝ ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን ለአምስት
ዓመት ያህል ከቀረጥ ክፍያ ነፃ ናቸው። በተጨማሪ የሚኖሩት በልዩ ቤቶችና በውሃ አካባቢ ነው። በሌላ
ወገን ግን ጥሩ ስራ አገኘን ብለው ከገጠር የሚመጡና ፋብሪካዎቹ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩት
ሰራተኞች በሚያገኙት ደሞዝ ቤት ተከራይተው ለመኖር አይችሉም። ከዚህ በላይ ኩባንያዎቹ ስራቸውን
ለማንቀሳቀስ ለኃይል(Electricity) የሚከፍሉት በጣም ዝቅተኛ ዋጋ ሲሆን፣ ለውሃ ደግሞ ምንም
ሳንቲም እንደማይከፍሉ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። በተጨማሪም የኩባንያዎች ባለቤቶች ኩባንያዎቹ
በተተከሉባቸው መሬት ላይ በካሬ ሜትር $ 25 የአሜሪካን ዶላር ብቻ የሚከፍሉ ሲሆን፣ በመሰረቱ
በአዋሳ ኗሪው ህዝብ ለአንድ ካሬ ሜትር መሬት $245 እንዲከፍል ይገደዳል።

በአጠቃላይ ሲታይ እንደዚህ ዐይነቱ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለአገራችን የተስተካከለ ዕድገት የሚያመጣው
ውጤት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የኢንዱስትሪው ፓርክ ላይ ለአንድ አገር ዕድገት የሚያስፈልጉ እንደ
ማሺን ኢንዱስትሪዎች፣ ልዩ ልዩ መሳሪያዎችን የሚሰሩ ኢንዱስትሪዎች፣ የመለዋወጫ ዕቃዎችን
የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች፣ የተለያዩ ለኃይል ማመንጫ የሚሆኑ መሳሪያዎችንና ኬብሎችን
የሚያመርቱ ... ወዘተ. እርስ በእርሳቸው የተያያዙ ኢንዱስትሪዎች በፍጹም አልተተከሉም። ከዚህም በላይ
አንድን የኢንዱስትሪ ፓርክ የኢንዱስትሪ ፓርክ የሚያሰኘው በዚያው ቦታ ላይ ምርምርና
ዕድገት(Research and Development) ሲካሄዱና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሲፈጠሩና በስራ ላይ ሲውሉ
ብቻ ነው። ሃዋሳና ሌሎች ቦታዎች የተተከሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች እርስ በእርሳቸው የተያያዙ
(Integrated Industrial Development) አይደሉም። ስለሆነም ለአንድ አገር የተስተካከለና ተከታታይነት
ላለው የኢኮኖሚና የማህበረሰብ የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ እጅግ ዝቅተኛ ነው። በአንፃሩ በዝቅተኛ
ደሞዝና በርካሽ አገልግሎት ከፍተኛ ትርፍ ወደ ቻይናና ወደ ተቀሩት አገሮች የሚተላለፍበትን አመቺ
ሁኔታ ነው አገዛዙ የፈጠረው ማለት ይቻላል። መንግስት የኢንዱስትሪ ፓርኩን ለማቋቋም $ 250
ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያወጣ ሲሆን፣ በዚህ ገንዘብ ተከታታይነት ያላቸውን ማሺኖችንና ልዩ ልዩ
መሳሪያዎችን የሚያመርቱ አነስተኛና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ማቋቋም ይቻል ነበር። በተጨማሪም
የተግባረ-ዕድ ትምህርትቤት በማቋቋም በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥረው ሊሰሩ የሚችሉ በተለያየ
ሙያ የሚሰለጥኑ ወጣቶችን ማስመረቅ ይቻላል። አገዛዙ ይህን ዐይነቱን ለአንድ አገር የውስጥ ገበያ
ዕድገትና ለህብረተሰብአዊ ለውጥ (Social Transformation) አስፈላጊ የሆነውን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ
ከመከተል ይልቅ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ብቻ የተቋቋመው የኢንዱስትሪ ፓርክ ዕድገትን የሚያመጣ
ሳይሆን በራሱ በዚያ አካባቢ የሚኖረውን ማህበረሰብ የሚያዘበራርቅ ነው፤ ከዕድገት ይልቅ ኋላ-
ቀርነትንና ድህነትን የሚያጠነክር ነው።

ከዚህ ወጣ ብለን በእርሻው መስክ የሚካሄደውን መዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ ስንመለከት የህዝባችንን የኑሮ
ሁኔታ ሊያሻሽልና ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊያመጣ የሚችል አይደለም። በአበባና በሩዝ ተከላ
የተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ያደረሱት ጉዳት ለሁላችንም ግልጽ ነው። እንደሚድሮክ የመሰለው
የአላሙዲን ኩባንያ በሃያ አምስት ንዑስ-መስኮች ውስጥ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ፣ ጎልቶ የሚታየው
በእርሻው መስክና በወርቅ ቁፈራ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ነው። አላሙዲን በብዙ የኢኮኖሚ ዘርፎች
ውስጥ የሚንቀሳቀስ ቢሆንም ለቴክኖሎጂ ዕድገትና ለስራ-ክፍፍል መዳበር የሚያበረክተው አስተዋፅዖ
አልቦ ነው ማለት ይቻላል። በአንፃሩ ኩባንያው የተሰማራው በሀብት ዘረፋና ተቆፍሮ የወጣውን ወርቅና
የእርሻ ምርት በቀጥታ ወደ ውጭ በማውጣት ራሱንና የውጭ ከበርቴዎችን በማደለብ ነው። የእርሻውን
መስክ ጠጋ ብለን የተመለከትን እንደሆን አሁን በቅርቡ „አረንጓዴው ወርቅ“ (The Green
Gold) በመባል የታየው የዶክሜንተሪ ፊልም የሚያረጋግጠው፣ አላሙዲን ገበሬውን ከመሬቱ
በማፈናቀልና በመሬቱ ላይ ሩዝና ሌሎች የእህል ዐይነቶችን በማምረት የሳውዲ ገበያ ላይ እንደሚያቀርብ
ነው። በሌላ ወገን ግን አገራችን ከውጭ በእርዳታ መልክ እህል ታገኛለች። አገዛዙም በተጨማሪ
ከኢንዱስትሪ አገሮች ስንዴ በመግዛት ራሱ በአገራችን ገበያ ላይ ይሸጣል። ከመሬቱ የሚፈናቀለው ገበሬ
የተወሰነው እዚያው ተቀጥሮ በዝቅተኛ ደሞዝ ሲሰራ፣ የስራ ዕድል ያላገኘው ደግሞ ወደ አካባቢው ባሉ
ከተማዎች በመሸሽ በስራ-ፈትነት እንዲንቀዋለል ተደርጓል። ይህም ማለት አላሙዲን ዕውነተኛ የእርሻ
ባህል የሚያከናውንና አካባቢውን የሚያለማ ሳይሆን፣ ዋና ዓላማው ትርፍ ማካበት ብቻ ነው።
በአካባቢው ማህበረሰብአዊ ክንዋኔዎች አይታዩም። አንድን ህዝብ በአካባቢው እንዲኖር የሚያደርጉት
ቤቶች፣ ትምህርትቤቶች፣ ክሊኒኮችና ሌሎች መዝናኛ ቦታዎችና የባንክ ስይስተም በፍጹም አይታዩም።
ስለሆነም አላሙዲን ከመንግስቱ መኪና ጋር ባለው የጠበቀ ግኑኝነት የፈለገውን የሚያደረግና በብዙ
ሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት ወደ ውጭ እንዲሸሽ ያደረገና የሚያደርግ ነው። አላሙዲን የስራ መስክ
የከፈተ ቢመስልም ጠቅላላው ድርጊቱ አንድ የሰለጠነና የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔን ደረጃዎችንና ደንቦችን
ጠብቆ እንደሚንቀሳቀስና ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል ዐይነት የከበርቴ ወይም አነስተኛ ከበርቴ መደብ
አይደለም። ድርጊቱ የዘረፋነትና ባህልን የማበላሸት ባህርይ ያለው ነው። ስለሆነም ጤናማ ለሆነ
የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ዕድገት የሚያበርክተው አስተዋፅዖ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ሰውየውና
ኩባንያው በቀጥታ ከፍተኛ የሆነ የማህበራዊና የባህል እንዲሁም የአካባቢ ቀውስ ያደረሱና የሚያደርሱ
ናቸው። በቀላሉ ሊታረም የማይችል የባህልና የማህበራዊ ቀውስ በአገራችን ምድር ማስፋፋት ችለዋል።

ከዚህ በተረፈ የአገራችን ጥንታዊ ዘሮች እንዳሉ በመዘረፍ ሞንሳቶ ላቦራቶሪው ውስጥ በሚያዳቅላቸው
የዘር ዐይነቶች(Genetically Modified Seeds) ተተክተዋል። በተለይም ጥንታዊው የጥጥ ዘር በላቦራቶሪ
ውስጥ በተደቀለ ዘር እንደተተካ አሁን በቅርቡ በእርሻ ሚኒስተር ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ አንድ ግለሰብ
ጥያቄ ቀርቦለት ዘሩን መጠቀሙ ምንም ጉዳት እንደማያመጣ ለማብራራት ሞክሯል። በሌላ ወገን ግን
በአውሮፓ አገሮች ላቦራቶሪ ውስጥ የተደቀሉ ዘሮችን መጠቀም ክልክል ነው። ይሁንና ግን በእኛ አገር
እስከዚህም የሳይንስ ምርምር ባልተስፋፋበትና ባልዳበረበት አገር ማንም ተቃዋሚ ኃይል የለም በማለት
ለገበሬው ዘሩን እንዲጠቀም ማደል ከፍተኛ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው። በተለይም ይህንን ዐይነት
ዘር በብዛት የሚጠቀሙ እንደብራዚልና አርጀንቲና የመሳሰሉ አገሮች ውስጥ ገበሬዎችና ቤተሰቦቻቸው
ተባዮችን ለማጥፋት በሚረጨው መርዝ በመበከል ለበሽታ እንደተጋለጡ ዶኩሜንተሪ ፊልሞችና
ጥናቶች ያረጋግጣሉ። በእርሻው አካባቢ የሚወለዱ ህጻናት የአካል ጉድለቶች ይታይባቸዋል። ያም ሆነ
ይህ አገራችን በዘር ብቻ ሳይሆን ጥገኛ ለመሆን የበቃችው የተባይ ማጥፊያም ከውጭ የሚመጣ ነው።
እንደሚባለው በላቦራቶሪ ውስጥ የተዳቀሉ ዘሮች ከተባይ የሚከላከል ውስጣቸው የተተከለ ልዩ ነገር
የለም፤ ቢኖርም አይሰራም። ይህ ቢሆን ኖሮ በላቦራቶሪ የተዳቀሉ ዘሮች በሚዘራባቸው ማሳዎች ውስጥ
ተጨማሪ የተባይ ማጥፊያ ኬሚካሎች ባልተረጩ ነበር።

ሰሞኑን የዶ/ር አቢይን ስልጣን መያዝ አስመልክቶ ከሃያ በላይ የሚቆጠሩ የአሜሪካን ኩባንያዎች ወደ
አገራችን ምድር መጥተዋል። ዋና ዓላማቸውም የተለያዩ የመዋዕለ-ነዋይ ክንውኖችን ለማጥናት ሲሆን፣
አትክሮአቸውም በተለይም በእርሻው መስክና በጥሬ-ሀብት ቁፈራ ላይ ይመስላል። አንዳንድ ቦታዎች
ገበሬውን በማፈናቀል ሙዝ በብዛት ተመርቶ ወደ አሜሪካን እንዲጫን ይፈልጋሉ። ይህም ማለት
ዩናይትድ ፍሩት ካምፓኒ(United fruit Company)በማዕከለኛው አሜሪካ አገሮች ውስጥ የሰራው
ወንጀልና ያካሄዳቸው የመንግስት ግልበጣዎችና የደገፋቸው ፋሺሽታዊ አገዛዞች በአገራችንም ሊደገም
ይችላል። በማዕከለኛው አሜሪካ አገሮች የሙዝ ማሳ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ለአቅመ-አዳም
ያልደረሱ ልጆችና አዋቂዎች በሚሰራጨው መርዝ ለበሽታ እንደተጋለጡ እንደዚሁ ጥናቶችና ዶኩሜንተሪ
ፊልሞች ያረጋግጣሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን በሙዝ ማሳ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩት ሰራተኞች
መብታቸውን የሚያስከብርላቸው የሙያ ማህበርም ሆነ መንግስት የላቸውም። ልጆቹም ትምህርትቤት
የመሄድ መብታቸው የተነፈገ ነው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳና ከዕውነተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት አንፃር የውጭ
አገር ኩባንያዎች በእርሻው መስክ መሰመራት ብሄራዊ ነፃነታችንን የሚቀናቀን ብቻ ሳይሆን በቀላሉ
ሊከፈል የማይችል አደጋ ውስጥ ልንወድቅ እንችላለን። በቤተሰብና በማዕከለኛ አራሾች የሚካሄድ የእርሻ
ባህል እንዳይስፋፋ ያግዳል። ቀስ በቀስ ለብዙ መቶ ዓመታት ያካበትነው የእርሻ ባህላችን መውደሙ ብቻ
ሳይሆን የአመጋገብ ባህላቸው በመቀየር ሰፊው ህዝባችን ለበሽታ እንዲጋለጥ ይደረጋል።

ከዚህም ባሻገር የውጭ ኩባንያዎች በወርቅና በሌሎች ማዕድኖች ቁፈራ ላይ ለመሰማራት ይሹ ይሆናል።
በተለይም የአሜሪካን፣ የፈረንሳይና የእንግሊዝ ኩባንያዎች በላቲን አሜሪካ፣ እንደ ፔሩ በመሳሰሉት
አገሮችና፣ አፍሪካ ውስጥ ደግሞ በማዕከለኛው አፍሪካ አገሮች፣ በኮንጎ በማዕድን ቁፈራ በመሰማራት
የሚያደርሱት የአካባቢ ውድመትና የማህበረሰብ ቀውስ ሰለጠን ከሚሉ አገሮች የሚጠበቅ አይደለም።
የአሜሪካን ኩባንያዎች በተለይም ፔሩ ውስጥ ኗሪውን ህዝብ በማፈናቀልና አካባቢውን በመመረዝ
የሚፈጽሙት ወንጀል በቀላል ቋንቋ የሚገለጽ አይደለም። ዩራኒዩም የሚያወጡ የፈረንሳይ ኩባንያዎችም
እንደዚሁ በኒጄርና በማሌ እንዲሁም በማዕከለኛው አፍሪካ አገር መሬቱን በመመረዝ የሚፈጽሙት
ወንጀል ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የኢትዮጵያ ህዝብ ሳያውቀውና፣ ምሁሩ
ሳይከራከርበት፣ እንዲሁም ህገ-መንግስቱን መሰረት ያላደረገ ማንኛውም የውጭ አገር የመዋዕለ-ነዋይ
እንቅስቃሴ መካሄድ ያለበት አይመስለኝም። የዶ/ር አቢይ አገዛዝ በዚህ ላይ በቂ ግንዛቤ ይኖረዋል ብዬ
እገምታለሁ። ይህ ብቻ ሳይሆን የጥሬ-ሀብት አላቂ እንደመሆኑ መጠን ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው።
ሊያገለግልና መዋል ያለበትም ለአገር ግንባታ ብቻ ነው። የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በሚንቀሳቀሱባቸው
የሶስተኛው ዓለም አገሮች በሙሉ የጥሬ-ሀብቶች እየተሟጠጡ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ። ለእርስ
በእርስ ጦርነቶችና ላለመረጋጋት ምክንያቶች ናቸው።

ከዚህ በመነሳት ሰሞኑን በ36 የኢሃአዴግ የኮሚቴ አባላት የአገር ውስጥ 7 ኩባንያዎችን ድርሻ ለአገር
ውስጥና ለውጭ ከበርቴዎች የመሸጡ ጉዳይ ብዙዎቻችንን ያነጋገረ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኮሚቴው
አንዳች ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ጉዳዩ ፓርሊያሜንት ውስጥ ለክርክር መቅረብ ነበረበት። በሁለተኛ
ደረጃ፣ የህዝብን ንብረት በድርሻ መልክ መሸጥ በህገ-መንግስቱ የሚደገፍ መሆኑን መረጋገጥ ነበረበት።
በሶስተኛ ደረጃ፣ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ምሁራን አስተያየታቸውን እንዲሰጡ መጋበዝ ነበረባቸው።
በአራተኛ ደረጃ፣ ህዝቡ እንዲያውቀውና እንዲወያይበት አስፈላጊ ነበር። ይህም ማለት አንድ መንግስት
አንድ ኮሚቴ በመፍጠር ኮሚቴው በዚህ መልክ ተስማምቷል ብሎ የዱብ ዕዳ ማውረድ ያለበት
አይመስለኝም። ዲሞክራሲያዊ አሰራርም አይደለም። ሀብቱ የመንግስት ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ
እንደመሆኑ መጠን መንግስት ህዝብን የሚጎዳ ውሳኔ ላይ መድረስ ያለበት አይደለም። ያም ሆነ ይህ
የሚነሱት ጥያቄዎች አሁን አገሪቱ ባለችበት ያልተረጋጋ ሁኔታ የእነዚህን ኩባንያዎች ድርሻዎች መሸጡ
ጥቅሙ ምን ላይ ነው ? የሚለው አብዛኛዎቻችንን እያነጋገረ ይገኛል። ከዚህም በላይ ከኢኮኖሚ ግንባታ
አንፃር ሲታይ ሌሎች ቅድሚያ የሚሰጣቸው፣ ድህነትን መቅረፍና ቀስ በቀስ ማውደም የመሳሰሉት
የተወሳሰቡ ችግሮች እያሉ ለምን የኩባንያዎችን ድርሻ መሸጡ ላይ ቅድሚያ ተሰጠ? ሰፋ ያለ ኢኮኖሚያዊ
ዕቅድ ከማውጣት ይልቅ በአሁኑ ወቅት በነዚህ መስኮች ላይ ለምን አትኩሮ ተሰጠ? መንግስትና ህዝብስ
በዚህ ዐይነቱ ሂደት ምን ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ? የሚነሳው ጥያቄ የመሸጥና ያለመሸጥ ወይም የአገርን
እሴት ለውጭ ከበርቴዎች አሳልፎ የመስጠቱ ጉዳይ ሳይሆን፣ ከዕድገት አንፃር ጥቅሙ ምንድነው? የሚል
ነው። ድርሻዎችን በመሸጥ መንግስት የሚፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ሊያገኝ ይችላል ወይ? መንግስትስ
ድርሻዎችን በመሸጥና ዶላር በማግኘት አገሪቱ ያላትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት መፍታት ይችላል ወይ?
ድርሻ መሸጡ የአንድ ጊዜ ሂደት ብቻ ወይስ ተከታታይነት ይኖረዋል ወይ? በእነዚህ ዙሪያ እንቅስቃሴዎች
ይስፋፋሉ ወይ? በዚህ መልክስ አዲስ ዐይነት የቴክኖሎጂ ምጥቀት ሊታይ ይችላል ወይ? በተጨማሪም
የስራ-መስክ በመክፈት ለአጠቃላዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ልዩ ዐይነት ዕምርታ ሊሰጠው ይችላል
ወይ? እንደዚህ እያልን ብዙ ጥያቄዎችን ለማንሳት እንችላለን።

አብዛኛውን ጊዜ የሶስተኛው ዓለም አገሮች በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ የአገልግሎት መስጫ


ድርጅቶችን ወደ ግል በሽያጭ ሲያዘዋውሩ ወይም ድርሻ በመሸጥ የአገር ውስጥና የውጭ ከበርቴዎች
ተካፋይ እንዲሆኑ ሲያደርጉ ተስፋ የሚያደርጉት ነገር አለ። ይኸውም የውጭ ምንዛሪ ይገኛል፤
ኢንቬስተሮች የበለጠ ሀብታቸውን በማፍሰስ ለዕድገት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራሉ፤ በዚያው መጠንም
የቴክኖሎጂ ልውውጥ በማድረግ ለአጠቃላይ ዕድገት አስተዋፅዖ ለማድረግ ይችላሉ ከሚለው
በኢምፔሪካል ደረጃ ካልተረጋገጠ ሁኔታ በመነሳት ነው። ባላፉት 30 ዓመታት ግሎባላይዜሽን የሚሉት
ፅንሰ-ሃሳብ ከተስፋፋና የኢኮኖሚ ተዋንያን(Global Players) በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲሽከረከሩ
የሚሰብኩት ነገር በግሎባላይዜሽን አማካይነት የዓለም ህዝብ አዲስ የሆነ የዕድገት ምዕራፍ ውስጥ
ገብቷል፤ ሁሉም ነገር ለገበያው መለቀቅ አለበት፤ መሽጥ መለወጥና የመንግስታትን ሀብት ወደ ግል
ማዘዋወር(Deregulation)አማራጭ የሌለው አካሄድ ነው እያሉ በመስበከ ነው ብዙ መንግስታትን
መቀመቅ ውስጥ የከተቷቸው። በተጨማሪም የገበያን ኢኮኖሚ የሚያራምዱ አክራሪ አቋም ያላቸው
አማካሪዎች ደግሞ እንደ ውሃ ማሰራጫ፣ እንደ ኃይል ማመንጫ፣ ቴሌኮሙኒኬሽንና የባቡር
መስመሮችንና ባቡሮች በመንግስት ቁጥጥር ስር መዋላቸው የገበያን ህግ የሚፃረርና ተፈጥሮአዊ ያልሆነ
ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ ነው በማለት በመንግስታትና በኢኮኖሚ ኤሊቱ ላይ ጫና ያደርጋሉ። ግፊቱን
መቋቋም የማይችሉና በሰበካው የሚታለሉ መንግስታት ዕውነት እየመሰላቸው የመንግስትን ሀብት
ለሺያጭ ያቀርባሉ። ይሁንና ግን ሁኔታዎችን በጥብቅ የተከታተለና ያጠና በተለይም በሶስተኛው ዓለም
አገሮች ውስጥ የመንግስት ሀብቶችን ወደ ግል ማዘዋወሩ የተጠበቀውን ውጤት እንዳላመጣ ነው
በየአገሮች ውስጥ በገሃድ የሚታዩት ተጨባጭ ሁኔታዎች የሚያረጋግጡት። በተለይም የውጭ
ከበርቴዎች ዋና ዓላማ ከፍተኛ ትርፍ ለማካበት ስለሆነ በየመስኩ የሚሰራውን ሰራተኛ ትርፍ
ነው(Redundant) በማለት ሲያባርሩ ነው የሚታዩት። ይህም ማለት ተጨማሪ የስራ-መስክ መክፈት
ቀርቶ ተቀጥሮ ይሰራ የነበረውን የተወሰነውን የሰው ኃይል እንደሚያባርሩ ነው ጥናቶች
የሚያረጋግጡት። ይህ አንደኛው ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ለውጭ ከበርቴዎች የሚሸጡት ኩባንያዎች
ውስጥ መሰረታዊ የሆነ የቴክኖሎጂ መሻሻል ሲደረግ አይታይም። ይህም ማለት የቴክኖሎጂ ልውውጥ
በማድረግ ምርት በጥራትም ሆነ በብዛት ምጥቀት አያገኝም። የወጭ ኩባንያዎች ዋናው ዓላማም
በተለይም እንደቴሌኮሙኒኬሽን የመሳሰሉትን በመግዛት ወይም በድርሻ በመካፈል የተንቀሳቃሽ
ስልክ(Mobile) ለማስፋፋት እንጂ ኬብሎችን በማስፋፋት በእያንዳንዱ ቤት ውስጥ ቁሚ ስልክ ለመትከል
አይደለም። እንደምናውቀው በአንድ አገር ውስጥ ቋሚ ስልክ ከተስፋፋ የተሻለ የስልክ ግኑኝነት መፈጠሩ
ብቻ ሳይሆን የኬብል ቴክኖሎጂም በዚያው አገር ውስጥ ሊስፋፋና ምርምርም ሊደረግበት ይችላል።
በተለይም አንድ አገር ኬብሎችንና ዋየሮችን፣ እንዲሁም መደወያዎችን ራሷ የምታመርት ከሆነ አዲስ
ቴክኖሎጂን መማሯ ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ አማካይነት ለብዙ መቶ ሺህ ሰዎች የስራ-መስክ ሊከፈት
ይችላል። በተጨማሪም የቋሚ ስልክ መስፋፋት ለፈጣን የኢንተርኔት ስርጭት(Broad Band) መስፋፋት
አመቺ ነው። ከዚህም በላይ ከተንቀሳቃሽ ስልክ ይልቅ የቋሚ ስልክ መስፋፋት ለጤንነት በጣም ጠቃሚ
ነው። ተንቀሳቃሽ ስልክን ለማስፋፋት ሲባል በየቦታው የሚተከሉ ቋሚ ብረቶችና የማግኔቱ ኃይል
ለጤንነት አደገኛ እንደሆኑ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።

ወደ ሌሎች እንደውሃና እንደባቡር የመሳሰሉትም ስንመጣ ወደ ግልሀብትነት በተዘዋወሩት በእነዚህ


መስኮች ውስጥ መሻሻል አይታይም። የውሃ ስርጭትን ሁኔታ ስንመለከት ኔስትለስ(Nestlés)
የሚባለው የስዊዘርላንድ የምግብና የውሃ አምራችና አከፋፋይ ኩባንያ ከሶስተኛው ዓለም መንግስታት
ጋር በመመሰጣጠር ውሃ የማውጣት መብት(Water Grabbing) በመግዛት ንጹህ ውሃ በየቤቱ
የሚያዳርስ ሳይሆን ውሃውን በፕላስቲክ ጠርሙሶች በመሙላትና በመሸጥ፣ ከፍተኛ ትርፍ ሲያካብት፣
አብዛኛው ህዝብ ደግሞ ንጹህ ውሃ የማግኘት መብቱ እንዳለ ተነጥቋል። ኩባንያው ውሃ እንዲያወጣ
መብት በገዛበት እንደፊሊፒን በመሳሰሉ አገሮች ውስጥ አብዛኛው ህዝብ ንጹህ ውሃ ገዝቶ የመጠጣት
አቅም ስሌለው የደፈረሰ ውሃ እንዲጠጣ ተገዷል። በፕላስቲክ የታሸጉ ውሃዎችን ገዝቶ መጠጣት
የሚችለው የየአገሩ ኢሊት ብቻ ነው። የኔስትለስን ህገ-ወጥና ስነ-ምግባር የሌላቸውን ስራዎች
የሚያጋልጡ ዶኩሜንተሪ ፊልሞችና ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ኩባንያው ካለምንም ይሉኝታ
የአንዳንድ የሶስተኛውን ዓለም አገሮችን የውሃና የምግብ ኢንዱስትሪዎች በመቆጣጠር ለጤንነት
መቃወስ ምክንያት እንደሆነ ነው።

ወደ ባቡር መንገድና ኔት ሲይስተሙ ስንመጣ በተለይም ከእንግሊዝ አገር ልምድ እንደምናየው ወደ


ግልሀብትነት የተሸጠው ይህ የመመላለሻ መንገድ እንዳልተሻሻለና፣ ሃዲዶችና ባቡሮቹ ባለመታደሳቸው
በብዙ ሰዎች ላይ አደጋ እንዳደረሱ ነው መረጃዎች የሚያረጋግጡት። በአንፃሩ የባቡር መስመሮችና
ባቡሮች ወደ ግልሃብትነት ባልተዘዋወሩባቸው እንደጀርመንና ስዊዘርላንድ፣ አውስትሪያና
በስካንዲኔቢያን አገሮች በተቀላጠፈ መልክና በትርፍ የሚሰሩ ናቸው። በየጊዜውም አዳዲስ ባቡሮች
በመስመር ውስጥ ሲካተቱና ሃዲዶችም ሲጠገኑ ወይም በአዲስ ሲተኩ ነው የምንመለከተው። በሌላ
ወገን ግን በአውስትሪያም ሆነ በጀርመን የግል ባለሀብቶች አዳዲስ ባቡሮች በመግዛትና ሃዲዶችን
በመከራየት በመንግስት ቁጥጥር ስር ካሉ ባቡሮች ጋር ሊወዳደሩ ይችላሉ።

ለማንኛውም ከዚህና ከሌሎች አያሌ ምክንያቶች ስንነሳ፣ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉት
በቴክኖሎጂና በኢንስቲቱሽን፣ እንዲሁም በውድድር ወደ ኋላ በቀሩ አገሮች ውስጥ በመንግስት ቁጥጥር
ስር ያሉ የአገልግሎት መስጫ ድርጅቶችን ድርሻቸውን መሸጥ ወይም እንዳሉ ወደ ግልሀብትነት
ማዘዋወር ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው። በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ተጨባጭ ምርትን
የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ለአገር ውስጥ ከበርቴዎች ቢሸጡ ለዕድገት ያመቻሉ። ያም ሆነ ይህ የአንድ
መንግስት ዋና ተግባር የአገሩን ህዝብ ደህንነት መጠበቅ፣ አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኝ
የአገልግሎት መስጫ ድርጅቶችን በየቦታው ማስፋፋት ስለሆነ በመንግስት ስር ያሉ የአገልግሎት መስኮች
ባይሸጡ ይሻላል። በሌላ ወገን ግን የግል ባለሀብቶችና የውጭ ኩባንያዎች በአገራችን ምድር የባቡር
መስመር እንዘረጋለን፤ ባቡሮችም በብዛት እናስገባለን፤ እዚያውም እንዲመረቱ እናደርጋለን፤ ሰዎችንም
እናስለጥናለን የሚሉ ከሆነ ኢንቬስት ማድረግ ይችላሉ። በተጨማሪም ቋሚ ስልክ በመትከል ሰፊው
ህዝብ እንዲጠቀም እናደርጋለን፣ በየቤቱ ንጹህ ውሃ ማስገባት እንፈልጋለን ካሉ ገበያውን ክፍት ማድረግ
ይቻላል። ይሁንና ግን የውጭ ኩባንያዎች ለአንድ አገር ዕድገት በሚጠቅሙ እንደባቡር በመሳሰሉ
መስመሮች መዘርጋት ላይ በምንም ዐይነት አይሳተፉም። ዋና ዓላማቸውም ትርፍ ማግኘት ብቻ ስለሆነ
ለአንድ አገር ዕድገት በሚጠቅሙ መሰረታዊ ነገሮች ላይ በፍጹም ሊሳተፉ አይፈልጉም። በታሪክ
እንደታየው በአውሮፓ ምድርና በአሜሪካም ጭምር የባቡር መስመሮች የተስፋፉትና ባቡሮችም
የተመረቱትና የሚመረቱት በመንግስት መነሳሳትና ከፍተኛ ተሳትፎ ብቻ ነው።

ሰለሆነም በእኔ ዕምነት እንደ አየር መንገድ የመሳሰሉት የተገለሉ ኢኮኖሚዎች(Enclave Economy)
በድርሻ መልክ በመሸጣቸው አየር መንገዱ መሻሻልንና መስፋፋትን ያገኛል ብዬ አላምንም። አሁን ባለው
የጦፈ ዓለም አቀፋዊ ውድድር የበለጠ ትርፍ ለማምጣትና ድርሻ ገዢዎችንም ለማስደሰት ሲባል(Share
Holder Value) ሰራተኞችን ማባረርና መስመሮችንም ወደ መዝጋት ሊደረስ ይቻላል። እንደ ኢትዮጵያ
የመሳሰሉ ደካማ አገሮች ቀርቶ ራሳቸው እንደጀርመን የመሳሰሉ ከፍተኛ ዕድገት ላይ የደረሱ አገሮች
አንዳንድ ኩባንያዎች የድርሻ ገዢዎችን ግፊት መቋቋም አቅቷቸዋል። በዚህም የተነሳ የተለያዩ የምርት
ዐይነቶችን የሚያመርቱና በቴክኖሎጂ ገፍተው የሄዱ የብረታ-ብረት ፋብሪካዎች የመጨረሻ መጨረሻ
ሊከስሩ ችለዋል። ባጭሩ ከአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ሁኔታ ስንነሳ ከላይ የተጠቀሱትን ድርጅቶች ወደ
ግል ማዘዋወር ወይም የተወሰነ ድርሻ መሸጥ የተጠበቀውን ውጤት ሊያመጣ አይችልም።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የመንግስት ሀብቶችን ወደ ግል ለማዘዋወር የሚያመቻቹና ጥናት የሚያቀርቡ፣


እንዲሁም የሚያማክሩ 21 የሚሆኑ የታወቁ አገር ቤት ውስጥ የሚኖሩና በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ
የሚሰሩ ግለሰቦችን የዶ/ር አቢይ አገዛዝ መርጧል። የአብዛኛዎችን ስም ዝርዝር ስንመለከት አብዛኛዎች
የኒዎ-ሊበራል አለመለካከት ያላቸው ሲሆኑ፣ ሌሎች በተለይም በውጭ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ይህንን
ያህልም ህብረተሰብን በሚመለከት ግልጽ አቋም ያላቸው አይደሉም። ዕምነታቸውና ርዕዮተ-ዓለማቸው
ንጹህ የሆነ የገበያ ኢኮኖሚ በመሆኑ አንድን አገር ሁለንታዊና እኩልነትን በሚያመጣ መልክ ለማሳደግ
የሚችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚያፈልቁ አይደሉም። እስካሁን እንዳየነውና ተግባሮችም
እንደሚያረጋግጡት በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ለብዙ ዐመታት የሰሩና የስራ ልምድም ያካበቱ
ግለሰቦች ስልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜ አገራቸውን በተስተካከለ መልክ ሊገነቡ እንደማይችሉና
የህዝቦቻቸውን ፍላጎትና ህልም ማሟላት እንደማይችሉ ነው የምንገነዘበው። ዓለም ባንክ ውስጥ ይሰራ
የነበረውና በኋላ የጋና ፕሬዚደንት የሆነው ኩፎርና(Kufuor) የላይቤሪያው ሴት ፕሬዚደንት የሆኑት ኤለን
ጆንሰን(Ellen Johnson) እንዳረጋገጡት እነዚህ ሁለት ፕሬዚደንቶች አገሮቻቸውን የሳይንስና የቴክኖሎጂ
ባላቤቶች በማድረግ ህዝቦቻቸው ተከብረውና ተደስተው እንዲኖሩ ለማድረግ የቻሉ አይደሉም። የዓለም
አቀፍ ኮሙኒቲው ተገዢዎችና ትዕዛዝ ተቀባዮች በመሆናቸው የየአገሮቻቸው የጥሬ-ሀብት፣ ወርቅ ጋና
ውስጥ፣ የጎማ ወተት ደግሞ ላይቤሪያው ውስጥ እንዲመረትና እንዲዘረፉ ያደረጉ ናቸው። በኩፎር
የአገዛዝ ዘመን የጋና ዋና ከተማ ውዳቂ የኤልክትሮንኪስ ጥሬ-ሀብቶች መጣያ በመሆን በአፍሪካ ውስጥ
ተቀዳሚ ቦታ ይዟል። የተለያዩ ጥሬ-ሀብቶችን ለመፈለግ እዚያ ተሰማርተው የሚለቅሙ ህጻናትና ወጣት
ልጆት የሰውነት አካሎቻቸው፣ እንደ ጉበትና ሳምባ የመሳሰሉት በበሽታ ተለክፈዋል። ኩፎር ጋናን የቆሻሻ
መጣያና ሀብቷም በውጭ አገር ኩባንያዎች እንዲዘረፍ በማድረጉ የተከበረ መሪ በመባል
ይታወቃል። በፕሬዚደንት ኤለን ጆንሰን ስምንት የአገዛዝ ዘመን የላይቤሪያ ወጣት የጎማ ወተት ማምረቻ
ፕላንቴሽን ውስጥ ተቀጥሮ በመስራት የሚበዘበዝ ነበር። ለዚህ ተግባራቸውና ላይቤሪያን
በማደህይታቸው ኤሊን ጆንስን የኖቭል ዋጋ ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል። በአጭሩ በዓለም አቀፍ
ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው ሰላሳና ከዚያም ዐመታት በላይ የሰሩ ግለሰቦች በየአገሮቻቸው ሲሾሙ ታሪክ
የሰሩበትና ጤናማ ህብረተሰብ የገነቡበት ዘመን የለም። ዕውቀታቸው በኒዎ-ሊበራሊዝም ላይ
የተመሰረተ በመሆኑ ሹመት ሲሰጣቸው ይህንኑ ተግባራዊ ከማድረግና ህብረተሰብን ከማዘበራረቅ
በስተቀር አንድን አገር የሳይንስና የቴኮኖሎጂ፣ እንዲሁም የባህል አገር በማድረግ አገሮቻቸውን
ያስከበሩበት ጊዜ የለም። ስለሆነም በተቻለ መጠን አገር ውስጥ በሰለጠኑና፣ በተለይም በውጭ አገሮች
ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ስራ ተሰማርተው ምርምር የሚያደርጉና የሚያስተምሩ
ኢትዮጵያኖችን መሰብሰቡና ምክር መጠየቁ የተሻለ አማራጭ ነው ብዬ አምናለሁ። በተለይ የፊዚክስ፣
የማቲማቲክስ፣ የማቴሪያል ሳይንስና፣ የመካኒካል ኢንጂነሪንግና የኤሌክትሮኒክስ ሙያ ያላቸውና፣ ሌሎች
ከተፈጥሮ ሳይንስ ጋር የተያያዘ ሙያ ያላቸው ምሁራን ለዕድገት የበለጠ ይጠቅሙናል።

ለማንኛውም የዛሬውም ሆነ ወደፊት ሊመጣ የሚችለው አገዛዝ በአገራችን ምድር በሳይንስና


በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልግ ከሆነ በተለይም የብረታ ብረት
ቴክኖሎጂዎችን፣ የተለያዩ መሳሪያዎችን የሚሰሩ የማሽን ኢንዱስትሪዎችን፣ የህክምናን መሳሪያ
የሚያመርቱና የህክምና መሳሪያዎችንም መለኪያዎችን፣ ማለትም እንደ ፋይን ሜካኒክ የመሳሰሉት
እንዲቋቋሙ ከአውስትሪያ፣ ከጀርመንና ከስዊዘርላንድ ከመሰሳሉት አገሮች ጋር ልዩ ዐይነት ስምምነቶች
ማድረግ ይችላል። የምንፈልገው መሰረታዊና ስነስርዓት ያለው ለውጥ እስከሆነ ድረስ ስትራቴጂካሊ
ማሰብ ያለብን ይመስለኛል። የለም ይህ አይደለም የሚያስፈልገን፣ የሚያስፈልገን የውጭ ምንዛሪ
ለማግኘት በሚያስችሉን የኢኮኖሚ መስኮች ላይ ብቻ ነው መረባረብ ያለብን የምንል ከሆነ የድህነቱ
ዘመን ይራዘማል። ስለሆነም ምርጫችን ከሁለት አንዱ መሆን አለበት። አይ ሳይንሳዊ መሰረት ወዳለውና
ወደ ተስተካከለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ወደ አገር ግንባታ ላይ ማትኮር፣ አሊያም ደግሞ ቡና፣ አበባ፣
ሙዝና ሌሎች ፍራፍሬዎችን በመትከል የድህነቱንና የጥገኝነቱን ዘመን ማራዘም። ይህንን አወዛጋቢ ጉዳይ
ትተን ወደ ነፃ ንግድ ስምምነት(Free Trade Agreement)ስንመጣ እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገሮች
ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ይመስላሉ። በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ያለው ዕምነት የነፃ ንግድ ስምምነት
የአንድን አገር የኢኮኖሚ ዕድገት ማፋጠን እንደሚችል ነው።

በእኔ ዕምነትና ብዙ ኢምፔሪካል ጥናቶችና የቴዎሪ ትንተናዎች እንደሚያረጋግጡት፣ ከተለያዩ የአፍሪካ


አገሮችም ሆነ ከቻይና፣ ከአሜሪካና ከአወሮፓው አንድነት ጋር የነፃ ንግድ ስምምነት(Free Trade
Agreement) ማድረጉ እንደዚሁ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የካፒታሊስት
አገሮች ስለነፃ ንግድ አስፈላጊነትና በዚህም አማካይነት ለውጥ ይመጣል ብለው ሲሰብኩ ከጥንካሬ
በመነሳት ነው። በታሪክ ውስጥ እንደተረጋገጠው በ18ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻና በ19ኛው ክፍለ-
ዘመን መጀመሪያ ላይ እንግሊዝ በኢንዱስትሪ አብዮት ከፍተኛ ዕምርታን ስታገኝ በብዛት
የምታመርተውን ምርት ውጭ አገር ገበያ ላይ ለማራገፍ ስትል የግዴታ የነፃ ንግድ ስምምነት ያስፈልጋል
እያለች ትወተውት ነበር። እንደጀርመንና አሜሪካን የመሳሰሉት በዚህ ዐይነቱ ሰበካ ባለመታለልና
በውስጥ ገበያ ዕድገት(Home Market) ላይ በመሰማራት በአንድ ትውልድ ጊዜ ውስጥ በሳይንስና
በቴክኖሎጂ መጥቀው ሊሄዱ ችለዋል። በጊዜው እንደፍሪድሪሽ ሊስት (Friedrich List) የመሳሰሉት
ታላላቅ የጀርመን የኢኮኖሚና የሶሻል ሳይንስ ሊቆች ከውስጥ በማኑፋክቸር ላይ የተመሰረተ የውስጥ
ገበያ የሌላቸው አገሮች ራሳቸውን ከመቻላቸውና ተወዳዳሪ ከመሆናቸው በፊት የነፃ ንግድ ስምምነት
ማድረግ እንደሌለባቸው ተሟግተዋል። በእነሱም ዕምነት ወደ ኋላ የቀሩ አገሮች ከአንድ በኢንዱስትሪ
ከበለጸገ አገር ጋር የነፃ ንግድ ስምምነት ካደረጉ በዚያው ቀጭጨው እንደሚቀሩ ነው። ስለሆነም በኋላ
አዲስ የዕድገት ፈለግን የተከተሉ እንደ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ(Developmental States) የመሳሰሉ አገሮች
ገበያቸውን ዝግ በማድረግ ወይም የዕገዳ ፖሊሲ(Protectionism) በመከተል ነው በአንድ ትውልድ ውስጥ
በቴክኖሎጂ ማደግ የቻሉት። እንደዚሁም ቻይና የጥገና ለውጥ ማድረግ ከጀመረች ከ1978 ዓ.ም ጀምሮ
ሰላሳ ዓመት ያህል በሯን ከዘጋችና የተወሰነ የዕድገት ደረጃ ላይ ከደረሰች በኋላ ነው በ2005 ዓ.ም የዓለም
ንግድ ድርጅት(WTO) አባል ለመሆን የበቃችው። ዛሬ ደግሞ ራሷ በመወትወትና የአፍሪካ አገሮችን
በማታላል የነፃ ንግድ ስምምነት እንዲደረግ ግፊት ታደርጋለች። አሁን በቅርቡ ጂቡቲ የተቋቋመው የነፃ
ንግድ ሰፈር ቻይና በብዛት የምታመርተውን ምርት እዚያው በማራገፍ በአካባቢው ያሉ ገበያዎችን
ለመቆጣጠር እንጂ ጂቡቲ ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት አይደለም። በተለይም በዚህ ዐይነቱ የነፃ
ንግድ ስምምነት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች በከፍተኛ ደረጃ ሊጎዱ ይችላሉ። እዚያ የሚራገፈው ምርት
ካለምንም ቀረጥ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በማደግ ላይ ያሉ የጫማና የጨርቃ ጨርቅና ሌሎች
ኢንዱስትሪዎችን ሊያዳክማቻው ይችላል። ስለሆነም የዶ/ር አቢይ አገዛዝ በተለይም ከጂቡት ወደ
ኢትዮጵያ የሚገቡ ዕቃዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የታሪፍ ጭመራና ከታሪፍ ውጭ የሆኑ
ማዕቀቦችን ተግባራዊ ማድረግ የሚኖርበት ይመስለኛል።

በአጠቃላይ ሲታይ የነፃ ንግድ ስምምነት አሁን ባለው የዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታ አማራጭ መንገድ
አይደለም። ደካማ አገሮች ከአቅማቸውና ከሚፈልጉት በላይ ሌሎች አገሮች የሚመረቱ ዕቃዎችንና የእርሻ
ውጤቶችን በማስገባት ከውስጥ የማምረት አቅማቸው እንዲዳከም ይደረጋል። ተክኖሎጂዎችን
ለመግዛት የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ወደ ሌሎች ለዕድገት ይህንንም ያህል በማይጠቅሙ ምርቶች
ላይ በመዋል እንዲባክን ይደረጋል። ከዚህም ባሻገር የነፃ ንግድ ስምምነት ወደ ውስጥ ሰፋ ያለ በስራ-
ክፍፍል ላይ የተመሰረተ የውስጥ ገበያ እንዲያድግ የሚያግዝ ሳይሆን፣ አንድን አገር በተወሰኑ የእርሻ
ምርቶች ላይ ብቻ እንድትረባረብ ያስገድዳታል። ይህ ብቻ ሳይሆን የማያስፈለግ የፍጆታ አጠቃቀም
በመግባትና በመለመድ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል አመጸኛ ሊያደርገው ይችላል። በተለይም ጥራት
የሌላቸው የምግብ ዐይነቶች በመግባት አዳዲስ በሽታዎችን ሊያስከትሉ ይችላሉ። በአሁኑ ወቅት
በኢንዱስትሪ አገሮች የሚመረቱ ምርቶች ዝቅተኛ ገቢ በሚያገኘው የህብረተሰብ ክፍል ላይ
የሚያስከትሉት የጤንነት ጉዳት ከቁጥጥር ውጭ እየወጣ ነው። ይህ ጉዳይ በተለይም አሜሪካ በግልጽ
ሲታይ፣ ገቢው ዝቅተኛ የሆነው የጥቁሩ የህብረተሰብ ክፍል በደም ግፊት፣ በልብ በሽታ፣ በስኳርና በነቀርሳ
እንዲሁም በውፍረት ይሰቃያል። ከዚህም ባሻገር ይህ ዐይነቱ የተትረፈረፈ ምርት የብዙ ኢንዱስትሪ
አገሮችን ሰዎች ጭንቅላት ወደ ተጠቃሚነት ብቻ እንዲያመሩ በማድረግ የህብረተሰብን ኖርም የሚያናጉ
ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው። ከዚህ ስንነሳ በደንብ ያልተጠናና ገደብ የሌለው የፍጆታ አጠቃቀምና የነፃ
ንግድ ስምምነት የመጨረሻ መጨረሻ ህብረተሰብአዊ መናጋትን ሊያስከትል እንደሚችል ብዙ ጥናቶች
ያመለክታሉ። ይህንን ዐይነቱን ሁኔታም የግሪክ ፈላስፋዎች በጥንቱ ዘመን ቀደም ብለው ያዩትና
የተነበዩት ጉዳይ ነው። በእነሱ ዕምነትም ማንኛውም ነገር በማሰብ መካሄድ ያለበትና ሚዛናዊነትን
የጠበቀ መሆን አለበት። መንፈሳዊና ማቴሪያላዊ ሁኔታዎች ሚዛናቸውን ጠብቀው መጓዝ አለባቸው።
ከዚህ ስንነሳ ግሎባል ካፒታሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የጤንነትና የአካባቢ ቀውሶችን
በማስከተል የተፈጥሮንና የብዙ ህብረተሰቦችን ሚዛን በማቃወስ ላይ ይገኛል።

ከዚህ በሻገር አገራችን አሁን ባለችበት ሁኔታ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ጋር የነፃ ንግድ ስምምነት ማድረጓ
ጥቅሙ አይታየኝም። አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ተመሳሳይ ምርቶችን ስለሚያመርቱ ከቴክኖሎጂ ጋር
የሚያያዝ የመዋዕለ-ነዋይ ፍሰት ሊኖር አይችልም። በሁለተኛ ደረጃ፣ ኢትዮጵያ ከጉምሩክ ቀረጥ
የምታገኘው ገቢ ይቀራል። አገዛዙ ባጀቱን ለማሟላት ሲል ሌላ የገንዘብ ምንጭ መፈለግ ይኖርበታል።
በሶስተኛ ደረጃ፣ በአጠቃላይ ሲታይ በማደግ ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎች(Infant Industires) ከወጭ
በሚመጣ ተመሳሳይ ምርት ይጎዳሉ። ስለሆነም በእነዚህ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው
ሰራተኛ የተወሰነው ከስራው ሊባረር ይችላል። በአራተኛ ደረጃ፣ የነፃ ንግድ ስምምነት የባህል ጥራትን
አያመጣም። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ዋናውና ተቀዳሚ ተግባር በጠንካራ መሰረት ላይ የሚመረኮዝ
የውስጥ ገበያ ማዳበርና ማስፋፋት ነው። ከተማዎችንና መንደሮችን መገንባት ነው ቅድሚያ መሰጠት
ያለበት። በተጨማሪም ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ማቋቋም ሰፋ ላለ የስራ-ክፍፍል
መዳበር ያመቻል። ስለሆነም የእርሻ መሳሪያዎችን ለማምረትና ለገበሬው ለማቅረብ ይቀላል። ከዚህም
ባሻገር በየቦታው ተቋማት(Institutions) እንዲቋቋሙ ማድረግና በብዛት የሰው ኃይል ማሰልጠን ሰፋ ላለ
የኢኮኖሚ ዕድገት ያመቻል። እነዚህን የመሳሰሉ ኢንዱስትሪዎችና ተቋማት ከባህላዊ ክንዋኔዎች ጋር
ሲያያዙ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ህብረተሰብአዊ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። በአንፃሩ የነፃ ንግድ
ስምምነት አንድን ደካማ አገር በሁሉም አቅጣጫ እንዳያድግ ቆልፎ ይይዘዋል። ለአንድ ህብረተሰብ
ተስማምቶ መኖር የሚያስፈልጉ የተለያዩ ነገሮች ይታፈናሉ። ይህ ማለት ግን ከተለያዩ አገሮች ጋር የንግድ
ልውውጥ አይኑረን ማለቴ አይደለም። ለማለት የፈለጉት በመጀመሪያ ደረጃ አስፈላጊና መሰረታዊ በሆኑ
ነገሮች ላይ እንረባረብ ነው።

የውጭ ዕርዳታ ጉዳይና የሚያስከትለው ውጤት !


የውጭ ዕርዳታ(Economic Aid) ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የኮሙኒዝምን ርዕዮተ-ዓለም
መስፋፋት ለመዋጋትና አብዛኛዎችን የሶስተኛው ዓለም አገሮችን በአሜሪካን ቁጥጥር ወይም ተፅዕኖ ስር
ለማምጣት በጊዜው የአሜሪካን ፕሬዚደንት በነበሩት በትሩማን የቀረበና ወደ ተግባራዊነት የተለወጠ
ሃሳብ ነው። ይህም ማለት ሃሳቡ ሲነደፍ ዋናው ዓላማው በተለይም የአፍሪካን አገሮች ወደ ካፒታሊስት
ስርዓት በመለወጥ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ሳይሆን፣ በዕርዳታ ስም በእነዚህ አገሮች ልዩ ልዩ
ተቋማት(Institutions) ውስጥ ሰርጎ በመግባትና ለአሜሪካን የሚያድርና የአሜሪካንን ትዕዛዝ የሚቀበል
ልሂቅ በማፍራት ወደ ውስጥ የተስተካከለና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ
ዕድገት እንዳይመጣ ማሳሳት ወይም ማገድ ነው።

የኢኮኖሚ ዕርዳታ ተግባራዊ ከሆነ ወደ ሰባ ዓመት ሲጠጋው በእነዚህ ዐመታት ውስጥ ወደ አፍሪካ ብቻ
ከአንድ ትሬሊዮን በላይ የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ፈሷል። አሜሪካኖችም ሆነ የተቀሩት የምዕራብ
አውሮፓ መንግስታት የሚሰጡት ዕርዳታ እነሱ በሚፈልጉት መልክና ከነሱ ጥቅም ጋር ከሚያያዝ
ፕሮጀክት ጋር ስለሆነ ሁለንተናዊነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያግዝ ወይም የሚያፋጥን
አይደለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ በተናጠል ፕሮጀክቶች ላይ ያነጣጠሩ ዕርዳታዎች ከውስጥ
ኢኮኖሚው ጋር የሚያያዙና የውስጥ ገበያን የሚያዳብሩ ሳይሆኑ ከውጭው የዕርዳታ ሰጭ አገር
ኢኮኖሚ ጋር የሚተሳሰሩ ናቸው። ይህ ዐይነቱ እያደገ የመጣ የዕርዳታ ኢንዱስትሪ ለካፒታሊስት አገሮች
የስራ መስክ መክፈቻና በተጨማሪም ዕቃን በማራገፍና በዕዳ በመተብተብ ለሀብት ክምችት መሰረት
የሆነ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በዕርዳታ ስም በየአገሩ የሚሰማሩ ኢክስፐርቶች ዋና ተግባር ዕውቀትን ይዞ
መምጣት ሳይሆን መሰረታዊ የዕድገት ፈለግን በማሳሳት የድህነት ዘመንን ማራዘም ነው። አንዳንድ
ጥናቶችም እንደሚያረጋግጡት በዕርዳታ ስም በየቦታው የሚሰማሩ ሰዎች ዋና ተግባር ኢንፎርሜሽኖችን
በመሰብሰብ ለየአገሩ መንግስታት በማቀበል፣ በዚያው መጠንም በየአገር ውስጥ በሃይማኖትና በጎሳ ስም
የሚነሱ ግጭቶችን ማስፋፋት ወይም እንዲፋፋሙ ማድረግ ነው። የእርስ በእርስ ጦርነት የሚካሄድ
ከሆነና አለመተማመን ከተፈጠረ የመንግስታት ተግባር ጦርነትን ማካሄድ ይሆናል። ህዝቡም በጦርነት
ስለሚጠመድ ለማሰብና ለመፍጠር በፍጹም ዕድል አያገኝም። ስለሆነም የአንድ ደካማ አገር ህዝብ
አስተሳሰብ ችግርን በመቅረፍ ላይና ጤናማ ህብረተሰብን በመገንባት ላይ ማተኮር የለበትም የሚል
ውስጣዊ ስምምነት(Tacit Agreement)አለ። ከዚህም ባሻገር በአለፉት ሰላሳ ዐመታት ከዕርዳታ ጋር
ተጓተው የመጡ በሽታዎች የየአገሮችን እሴቶች በማውደም አንድ አገር በቀላሉ ሊጠቃ የሚችልበትን
ሁኔታ እንዳመቻቹ እንመለከታለን።

እስካሁን ድረስ በኢምፔሪካል ደረጃ እንደተረጋገጠውና እንደምናየውም ባላፉት ሰላሳና አርባ ዐመታት
በተከታታይ ዕርዳታን የሚያገኙ አገሮች ከድህነትና ከረሃብ እንዳልተላቀቁ ነው የምናየው። የሚሰጠው
ዕርዳታ የባሰውኑ ጥገኛና ራሳቸውን እንዳይችሉ በማድረግ የድህነትን ዘመን እንደሚያራዝም ነው።
በታሪክም እንደተረጋገጠው አንድ አገር ሊያድግ የሚችለው በራሱ ኃይልና በጥበብ ከውጭ በሚኮርጀው
ወይም በሚሰርቀው ቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ነው። ስለሆነም አገራችንም ሆነ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች
ከዕርዳታ ለመላቀቅ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ በአገር
ውስጥ ባለው የተትረፈረፈ የጥሬ-ሀብትና የሰው ኃይል መመካት ሲሆን፣ ከኒዎ-ሊበራሊዝም ነፃ የሆነ
የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ቢደረግ የአፍሪካ አገሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ድህነትን በመቅረፍና
በማስወገድ ቀስ በቀስ ወደ ተስተካከለ ዕድገት ሊያመሩ ይችላሉ። ይህንንም ለማድረግ በዕርዳታ ስም
የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ የሆኑና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ቁጥር መቀነስና የመጨረሻ
መጨረሻም ለቀው የሚወጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት አስፈላጊ ነው። በሌላ ወገን ግን ወጣቱን የተለያየ
ሙያ የሚያስተምሩና የሚያሰለጥኑ ሰዎችን በማፈላለግ ወደ አገራችን እንዲገቡ መጋበዝ በጣም ጠቃሚ
ነው። ያም ሆነ ይህ አንድ አገር እንደማህበረሰብና ህብረተሰብ በሁሉም አቅጣጫ እንዲያድግ የምንፈልግ
ከሆነ የግዴታ መወሰድ ካለባቸው ነገሮች መቆጠብ ያለብን አይመስለኝም።

መደምደሚያ መሰረተ-ሃሳብ !
በአንድ አገር በተለይም ወደ ኋላ በቀረ አገርና ህብረተሰብ ውስጥ ተግባራዊ የሚሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲ
እንዲያው በደፈናው ተግባራዊ መሆን የለበትም። አንድ ፖሊሲ ከመታቀዱና ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት
የአንድን አገር የማቴሪያልና የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ በቲዎሪ ደረጃ በደንብ መተንተን ያስፈልጋል። የአንድን
አገር ተጨባጭ ሁኔታ በቲዎሪና በሳይንስ ብቻ መተንተን የሚቻል እንደመሆኑ መጠን አንድን ተጨባጭ
ሁኔታ ለማንበብ የሚጠቅመንን የቲዎሪና የሳይንስ መሳሪያ በሚገባ ማወቅ አለብን። የአንድን አገር
የተወሳሰበ ችግር በተሳሳተ መልክ የምናነብና ትንተና የምንሰጥ ከሆነ ለችግሩ ትክክልኛ መፍትሄ ልናገኝ
በፍጹም አንችልም።

እንደምናውቀው ዛሬ አብዛኛዎቹ በዓለም ላይ ያሉ አገዛዞች የሚጠቀሙባቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች


በሙሉ የፈለቁት ባደጉ የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ ነው። በካፒታሊስት አገሮች ውስጥ በተለያየ ወቅት
የፈለቁት ቲዎሪዎችም ሆነ ፖሊሲዎች በአንድ ጊዜ ከመቅጽበት የፈለቁ ሳይሆኑ ከረጅም ጊዜ ምርምር ባኋላ
ነው። ይሁንና ግን የተለያዩ ቲዎሪዎችም ሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች የፍልስፍና መሰረት አላቸው። ስለሆነም
በየአንዳንዱ ኤፖክ ብቅ ያለ ምሁር እሱ በሚመስለው መንገድ በጊዜው የነበረውን ተጨባጭ ሁኔታ
በማንበብ ለሱ ይስማማል ብሎ ያሰበውንና ያመነበትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ አፍልቋል። በሌላ ወገን ግን
አንድን ተጨባጭ ሁኔታ ለማንበብ በተለያዩ ምሁራኖች ዘንድ አንድ ዐይነት ግንዛቤና ስምምነት
አልነበረም። አንደኛው የምሁር ክፍል ለተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ሲያደላና፣ ከዚያ በመነሳት ቲዎሪና
ፖሊሲ ሲያፈልቅ፣ ሌላው ደግሞ በዚህ ዐይነቱ ወደ አንድ ወገን በሚያደላው ፖሊሲና ቲዎሪ
የማይስማማው የሚያምንበትንና እኩልነትን ሊያመጣ ይችላል የሚለውን ፖሊሲ በማፍለቅ ሃሳቡ
ተቀባይነት እንዲያገኝ ይታገላል። ይህ ዐይነቱ በሃሳብ ዙሪያ መታገልና በአመኑበት ጸንቶ መቆየት
በአውሮፓ የምሁር እንቅስቃሴ ታሪክ ውስጥ የተለመደ ነው። ስለዚህም ነው በአውሮፓ ምድር ውስጥ
በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ዕድገት ሊመጣ የቻለው።

ወደ ሶስተኛው ዓለም አገሮች ስንመጣ ግን በተለያዩ ጊዜያት ተግባራዊ ያደረጓቸውና የሚያደርጓቸው


ፖሊሲዎች በሙሉ የፈለቁትና የዳበሩት በካፒታሊስት አገሮች ነው። የእነዚህን ዕውቀቶች፣ በተለይም
የኢኮኖሚ ፖሊሲን የቲዎሪና የፍልስፍና መሰረት ሳይመረምሩ በደፈናው ተግባራዊ ያደረጓቸውና
የሚያደርጓቸው ፖሊስዎች በሙሉ ዛሬ በአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ ለሚታየው
ድህነት፣ ኢ-ሰብአዊነት፣ ህብረተሰብአዊ መዘበራረቅ፣ የአካባቢ መቆሸሽና በቆሻሻ ቦታዎች መኖርና ሀብት
መባከን ተጠያቂዎች ናቸው። በተለይም በአፍሪካ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊት ዕምነት ማንኛውም
በምዕራቡ ዓለም የፈለቀውና የዳበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ አለው። ስለሆነም
ከፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ፣ ከባህል፣ ከአስተሳሰብና ከአደረጃጀት እንዲሁም ከስራ ባህል ባሻገር በምዕራቡ
ዓለም የፈለቀው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማንኛውም አገር ተግባራዊ ሊሆን ይችላል። ይህ ዐይነቱ ጭፍን
አስተሳሰብና ዕምነት፣ እንዲሁም የእየአንዳንዱን አገር ህብረተሰብአዊ አወቃቀር በደንብ ሳይመረምሩ
ተግባራዊ የሚሆን ፖሊሲ እንደምናየው አብዛኛዎቹን አገሮች ለድህነት የዳረገ፣ ለሀብት መባከን ምክንያት
የሆነና፣ ከፍተኛ የሆነ የአካባቢ ውድመትን ያስከተለ ነው። በተለይም ካፒታሊዝም ለአንዴም
ለመጨረሻም ጊዜ በአሸናፊነት ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በአፍሪካ መንግስታት ላይ በረቀቀ መልክ
በሚደረገው ጫና ሳይወዱ በግድ እየደጋገሙ አገር አውዳሚ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ
ተገደዋል።

የኒዎ-ሊበራል ማክሮ ኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ በአሻናፊነት ከወጣ ጀምሮ፣ በተለይም ባለፉት አርባ
ዓመታት ከልምድ፣ ከባህል፣ ከኢኮኖሚ አወቃቀር፣ ከፖለቲካ ኃይል አሰላለፍና ከታሪክ ባሻገር ሁሉም
አገሮች መከተል ያለባቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው እየተባለ ነው የሚናፈሰው። ስለሆነም የሰው
ልጅ የገበያን ኢኮኖሚ ሊቀዳጅ የቻለውና የሚችለው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረጉ
ብቻ ነው። የገበያን ኢኮኖሚ እንደ ርዕዮተ-ዓለም አድርገው በሚያምኑና፣ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ
ተግባራዊ መሆን አለበት ብለው በሚሰብኩ በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች ዕምነት ሳይንስና ቲክኖሎጂ
ቦታ የላቸውም። የገበያ ኢኮኖሚም ካለጊዜና ካለቦታ ነው የሚካሄደው። የሰው ልጅም የሚኖርበት ቤትና
የሚንቀሳቀስበት ልዩ ልዩ የመመላለሻና የመገናኛ መሳሪያዎች አያስፈልጉትም። ከዚህም ባሻገር
እንደፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ፣ ማቲማቲክስ፣ መካኒካል ኢንጂነሪንግ፣ ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ፣
አርኪቴክቸር፣ የከተማ ዕቅደና እንዲሁም ለሰው ልጅ የሚጠቅሙ ልዩ ልዩ የዕደ-ጥበብ ሙያዎች በሙሉ
ቦታ የላቸውም። ወይም ደግሞ እንዳሉ ወይም እንደተሰጡ(as given) ተደርገው ነው የሚወሰዱት። ይህ
ዐይነቱ አሳሳች አመለካከትና ኢኮኖሚ የሚባለው ነገር ካለነዚህ መሰረታዊ የዕድገት አውታሮች
ይንቀሳቀስ ይመስል የሰው ልጅ ሁሉ ትርፍን በማካበትና ጥቅምን በማሳደግ ላይ ብቻ መረባረብ አለበት።
ስለሆነም የሰውን ልጅ ፍላጎት ገበያ ይፈታዋል፤ የሰው ልጅ በሙሉ በገበያ ኢኮኖሚ ፍልስፋና መሽከርከር
አለበት። እንደምናየውና እንደምንኖርበት በተለይም ይህ ዐይነቱ የተዛባ አመለካከት አገሮችን መቀመቅ
ውስጥ ከቷቸዋል። ህብረተሰብአዊ ውዝግብን የፈጠረና ብዙ አገዛዞችም ሁኔታዎችን ለመቆጣጠር
የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

የብዙዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮችም ችግር በዚህ ዐይነቱ አሳሳች ዕምነትና በሳይንስ ባልተረጋገጠ
ተጨባጭ ሁኔታዎችን ማስነበብ በማይችል ቲዎሪ መሰል ነገር በመመራታቸው ነው። እጅግ በረቀቀ መልክ
በማቲማቲካል ሞዴል የሚቀርቡ ፖሊሲዎች አብዛኛዎችን የአፍሪካ አገሮችን መንግስታት በማሳሳት
ያላቸውን የጥሬ-ሀብቶች በስነ-ስርዓት እንዳይጠቀሙና ፍትሃዊነት የሰፈነበትና የተከበረ ኑሮ እንዳይኖሩ
ተገደዋል። ኑሮአቸውም ወደ አልባሌነት በመለወጥ የሰው ልጅ መጫወቻና የተፈጥሮ ሰለባ ሊሆኑ
በቅተዋል። ከዚህ ስንነሳ ፕላቶ እንደሚለው „ስለተራ ነገር ሳይሆን የምናወራው ስለሰው ልጅ
ህይወት ነው። የሰው ልጅም ህይወት የተከበረ ነው።“ ስለሆነም መነሳት ያለበት ጥያቄና ክርክር
በምን ዘዴና ቲዎሪ በመመራት ነው የተስተካከለ ዕድገት ማምጣትና ፍትሃዊ የሆነ ህብረተሰብ መመስረት
የሚቻለው? ብለን ነው መጠየቅና መከራከር ያለብን። በውጭ ኤክስፐርቶች ወይም በዓለም አቀፍ
ኮሙኒቲው እየተመራን ተግባራዊ የምናደርገው ፖሊሲ የባሰ ትርምስ ውስጥ የሚከተንና ወደ ጦርነትም
የሚያመራን ነው። ስለሆነም ምርጫችን ቀናውን መንገድ በመከተልና አሳሳቹን ፖሊሲ ተግባራዊ
በማድረግ ላይ ይሆናል ። ከዚህ ባሻገር ለአንድ አገር የተፋጠነና የተስተካከለ ዕድገት የአገር ወዳድ ስሜት
መኖር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። በምሁሩ ዘንድም የጋራ መንፈስ(Collective Spirit) መኖር
ለተስተካከለና ሰብአዊነት ለሚኖረው ዕድገት ያመቻል። ስለሆነም ለራስ ህዝብና አገር ቅድሚያ መስጠት
የአንድ አገር ምሁር ግዴታ መሆን አለበት። ማንኛውም ምሁር የአገሩንና የህዝቡን ጥቅም ማስቀደም
አለበት። ለዚህ ደግሞ የዓለም አቀፍን የኢኮኖሚ ስርዓትና መካኒዝሞችን በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል።
አንድ አገዛዝና ምሁር ካፒታሊዝም በአገር ደረጃም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዴት እንደሚሰራና
የሶስተኛውን ዓለም አገሮች በሱ የብዝበዛ ወጥመድ ውስጥ ከቶ እንዴት አድርጎ ወደ ድህነትና ወደ
ጥገኝነት እንደሚከታቸው በዚህ ላይ ጠለቅ ያለ ዕውቀትና ግንዛቤ እንዲኖረው ያስፈልጋል። ይህ ዐይነቱ
ግንዛቤ ሲኖር ብቻ ነው ስለሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በማኑፋክቸር ላይ ተመርኩዞ ሰፋ ያለ
የውስጥ ገበያ ስለመገንባት ማሰብና ማውራት የሚቻለው። በመሆኑም ጠንካራ መንፈስ ሊኖረው
የሚችል የፖለቲካና የኢኮኖሚ ልሂቅ ማሰልጠኑ የጊዜው አንገብጋቢ መሰረተ-ሃሳብና ሊታለፍ የሚገባው
ነገር አይደለም። ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይም የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ምሁር ሁሉ የህብረተሰብንና
የኢኮኖሚ ዕድገትን፣ የሳይንስንና የቴክኖሎጂን ጉዳይ... ወዘተ. ሊወያይና ሊከራከር የሚችልበት መድረክ
መዘጋጀት አለበት። ከአጭር ጊዜም ሆነ ከረጅም ጊዜ አንፃር የአገራችን የተወሳሰቡ ችግሮች ሊፈቱ
የሚችሉት በዚህ መልክ ነው እያለ እያንዳንዱ ድርጅትና እንዲሁም ግለሰብ የጥናት ጽሁፎችን በማቅረብ
በድፍረት መከራከርና ህዝቡን ማስተማር አለበት። በዚህ መልክ ብቻ ማን ለምን ዐይነት የህብረተሰብ
ርዕይ እንደቆመና፣ በምን ዐይነት የቲዎሪና የፖሊሲ መሳሪያ የአገራችንን የተወሳሰቡ ችግሮች ለመፍታት
በቂ ግንዛቤ እንዳለው መረዳት ይቻላል።

በኛ ዘንድ ያለው ትልቁ ችግር የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ዕድገት፣ ሳይንስና፣ ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም
ጥበብና የባህል ዕድገት በሚሉት ለአንድ አገር መተሳሰርና ጥንካሬ በሚያስፈልጉ መሰረተ-ሃሳቦች ላይ
ለማጥናት፣ ለመወያየትና ለመከራከር ዝግጁ አለመሆን ነው። አብዛኛዎች ለስልጣን እንታገላለን የሚሉ
ድርጅቶች ፖለቲካ የሚባለውን ግዙፍ ፅንሰ-ሃሳብ ከነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ነጥለው በማየት ምሁራዊ
ውይይት እንዳይደረግ ከፍተኛ መሰናክል ፈጥረዋል። ስለሆነም በየቦታው ሳይንስንና ቴክኖሎጂን
የመጥላት ስሜት አለ። ጊዜው የሳይንስና የቴክኖሎጂም ቢሆንምና ሁላችንም የምንቀሳቀሰውና
የምንጠቀመው በቴክኖሎጂ አማካይነት ቢሆንም፣ በነዚህ መስረታዊ፣ ለአንድ አገር አስፈላጊ በሆኑ
ጉዳዮች ላይ አትኩሮ ያለመስጠት አዝማሚያ አለ። ለዚሁ ሁሉ ችግር ሁላችንም ጭንቅላታችንን ብሩህ
በሚያደርግ በዕውነተኛ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ባለማለፋችን የአገራችንን ዕድል ከሳይንስና
ከቴክኖሎጂ ጋር አያይዘን ለማየት እንዳንችል ተደርገናል። በተለይም ፖለቲካ የሚባለው ፅንሰ-ሃሳብ
ችግርን መፍቻ፣ ታሪክን መስሪያና ለሳይንስና ለቲክኖሎጂ መሰረት ጣይ መሆኑ ቀርቶ ስልጣንን መያዣ
መሳሪያ ተደርጎ በመወሰዱ በፖለቲካው መስክ ሽወዳና ተንኮል እንዲሁም ምቀኝነትና መናናቅ ሰፈነውና
ስር ሰደው ለዕውነተኛ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ እንቅፋት ፈጥረዋል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ቡድናዊ
ስሜትን በማጎልመስ በሃሳብ ዙሪያ ከመሰባሰብና ለዕድገት የሚያመች ሁኔታ ከመፍጠር ይልቅ
አብዛኛዎቻችን በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ያለን አስተሳሰብ እጅግ የሚያሳዝንና ወደ ኋላ የሚጎትት ነው።
በአውሮፓ ምድር ውስጥ የሳይንስን፣ የቴክኖሎጂን፣ የፍልስፍናንና የቲዎሪን ዕድገት ስንመለከት እነዚህ
ዕውቀቶች ሊዳብሩና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊስፋፉ የቻሉት አፍላቂዎች ጭንቅላታቸው ከተንኮል የጸዳ
በመሆኑና ኋላ-ቀር አስተሳሰብን አሽቀንጥረው በመጣላቸው ነው። ማንኛውንም ነገር፣ ህብረተሰብንም
ሆነ ተፈጥሮን በፍልስፍና፣ በሳይንስና በቴዎሪ መነፅር በመመልከታቸውና በመመርመራቸው ለሳይንስና
ለቴክኖሎጂ ግኝቶች የሚያመቹ ሁኔታዎችን ፈጥረው አልፈዋል። ስለሆነም በአገራችን ምድር መሰረታዊ
ለውጥ እንዲመጣ ከፈለግን የግዴታ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ አለብን። ተንኮልና ሽወዳ እንዲሁም
ምቀኝነት ለአንድ አገር ዕድገት ፀር መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርብናል።

ከዚህ በተረፈ በአሁኑ ጊዜ አፍጦ አግጦ የሚታየውን የስራ-አጥ ቁጥር ለመፍታት የግዴታ ምግብ
ለስራ(Food for Work Program) የሚል ለብዙ ዐመታት የሚዘልቅ ዕቅድ መዘጋጀት አለበት። መሰረታዊ
ፍላጎቶችን ለማሟላት የግዴታ መንግስትና የየክልሉ አስተዳዳሪዎች ተግባራዊ ሊያደርጓቸው የሚችሉ
ደረጃ በደረጃ ሊከናወኑ የሚችሉ ነገሮች አሉ። ከዚህ ቀደም እንዳሳሰብኩት ምግብ ለስራ(Food for Work)
የሚለውን መርሃ-ግብር ተግባራዊ ለማድረግ በተለይም ውጭ አገር የሚኖረው ኢትዮጵያዊ
እንደየችሎታው በወር የተወሰነ ገንዘብ ቢያወጣ ገንዘቡ ሰፋ ላለ የአገር ግንባታ ላይ ሊውል ይችላል።
ቤቶችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ከተማዎችንና መንደሮችን፣ እንዲያም ሲል የባህል ማዕከሎችንና የተግባረ-
ዕድ መማሪያዎችን ለመደጎምና ለመስራት ይጠቅማል። ሁላችንም እንድምናውቀው አገራችን እንደ
ህብረ-ብሄርና እንደማህበረሰብ በደንብ ያልተገነባች አገር እንደመሆኗ መጠን ማንኛውም ኢኮኖሚያዊና
ማህበራዊ እንቅስቃሴ ከረጅም ጊዜ አንፃር መተለም ያለበት ጉዳይ ነው። ህይወት ያላቸውና በውሃና
በዛፎች የተከበቡና ያሸበረቁ እንዲሁም ልዩ ልዩ ድልድዮች ያሏቸው ከተማዎችና መንደሮች የአንድ ህዝብ
መግለጫዎችና ሊኖርበትም የሚያስችሉ ናቸው። የአገራችንን የተትረፈርፉ የጥሬ-ሀብቶች በማንቀሳቀስ
ላይ የተዘረዘሩትን ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕውን ማድረግ ይቻላል። በአገር ግንባታ ውስጥ ሰፊ
ህዝብ ሳይንቀስቃሰና ሳይሳተፍ ህብረተሰብአዊ ለውጥ የመጣበት አገር የለም።

ይህንን አስመልክቶ የዶ/ር አቢይ አገዛዝ የገንዘብ መሰብሰቢያ የባንክ ቁጥር ከፍቷል። ይሁንና ግን ውጭ
አገር ከሚኖረው ኢትዮጵያዊ የሚሰበሰበው ገንዝብ በምን ዐይነት ፕሮጀክቶች ላይ እንደሚውል የሰጠው
ማብራሪያ የለም። ስለሆነም የሚሰበሰበው ገንዘብ በምን ዐይነት ፕሮጀክቶች ላይ እንደሚውል አገዛዙ
ጥናትና ማብራሪያ ማሰራጨት አለበት። የሚሰበሰበው ገንዘብ ከፕሮጀክት ጋር የሚያያዝ መሆኑን
ማረጋገጥ አለበት። ገንዘቡ የውጭን ዕዳ ለመክፈል ወይም የውጭ ምንዛሪን ለመቅረፍ ሲባል ባልሆኑ
ነገሮች ላይ መዋል የለበትም። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ ምድር የተካሄደውን የገንዘብ
ስብሰባ ስንመለከት መሰራት ካለባቸው ነገሮች ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ሲሆን ብቻ ለመሰብሰብም ሆነ
ውጤቱንም ለመቆጣጠር ያመቻል። ከገንዘብ ስብሰባ ጋር በማያያዝ የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ወደ ሃያ
የሚጠጉ ታዋቂ ስዎችን ሰይሟል። የአብዛኛዎችን ስም ዝርዝር በምንመለከትበት ጊዜ ስለህብረተሰብና
ስለኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸው ግንዛቤ የቱን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ያስቸግራል። ብዙ ስዎችን ማካተቱ
የመደመር ስትራቴጂ አንድ አካል ቢሆንም የሚመረጡት ግለሰቦች ዝና ስላላቸው ብቻ መመረጥ
ያለባቸው ሳይሆኑ ስለህብረተሰብ ሳይንስና ስለአገር ግንባታ በቂና ሰፋ ያለ ግንዛቤ ያላቸው መሆን
አለባቸው። በተጨማሪም በራሳቸው የሚተማመኑና የውጭ ኃይሎች ተቀጥያ መሆን የለባቸውም።

ለማንኛውም ከዚህ አልፈን አሁን ያለውን የዋጋ ግሽበት ለመቋቋም በመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ
የዋጋ ቁጥጥርና ትመና ማድረግ አስፈላጊ ይመስለኛል። በአሁኑ ጊዜ ህዝቡ በኑሮ ውድነት በጣም
እየተማረረ ነው። በተለይም የጥቁር ገበያን ለመቆጣጠርና የዋጋ ግሽበትን ለመግታት በኢትዮጵያ ብር
ላይ ጥገናዊ ለውጥ(Currency Reform) ማድረግ ያስፈልጋል። አዲስና በቀላሉ ሊኮረጅ የማይችል ገንዘብ
ሲታተም የድሮውን ገንዘብ አንድ በሁለት በመለወጥ ከዝውውር ውስጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማውጣት
የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ከዚህ ጋር ተደምሮ የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ጋር ያለው ግኑኝነት መስተካከል
አለበት። እስካሁን ድረስ በተከታታይ ገንዘብን ዝቅ(Devaluation) ማድረጉ የአገራችንን የንግድ ሚዛን
አላሳደገውም ወይም ቡናና ሌሎች የጥሬ ሀብቶችን በመሸጥ ብቻ በቂ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት
አልቻልንም። እንዲያውም የአገሪቱ የንግድ ሚዛን ወደ ታች ማሽቆልቆሉ ብቻ ሳይሆን በዕዳም
ለመተብተብ በቅታለች። ከዚህም በላይ የኢትዮጵያ ብር ዝቅ ማለት ግሽበትን አስከትሏል። በተለይም
ከውጭ የጥሬ-ሀብቶችንና የመለዋወጫ ዕቃዎችን የሚያስመጡ አምራቾች አንድ ዶላር ለመግዛት ብዙ
የኢትዮጵያ ብር ማቅረብ ስላለባቸው ይህ በራሱ የማምረቻን ዋጋ ያሳድገዋል። ይህም ማለት የመጨረሻ
ምርቶች ገበያ ላይ ወጥተው በሚሸጡበት ጊዜ ዋጋቸው ይወደዳል። ስለሆነም በብርና በዶላር መሀከል
ያለው ግኑኝነት ቋሚ መሆን ሲኖርበት፣ እንደየሁኔታው የኢትዮጵያን ብር ከፍ(Revaluate) ማድረግ
ያስፈልጋል። አሁን ካለው የዶላር/ብር ልውውጥ የኢትዮጵያ ብር ከፍ ማለት አለበት። የጥቁር ገበያን
ለማስወገድ ከህግ አንፃርና ተግባራዊ መሆን ያለባቸው የመቆጣጠሪያ መሳሪያዎች አሉ። ችግሩ ግን
የተዘበራረቁና ግልጽነት የሌላቸው ከተማዎችና መመሸጊያዎች ለጥቁር ገበያ የሚያመቹ ናቸው።

ከዚህ ስንነሳ የአንድ አገር የመኖርና ያለመኖር ዕድል፣ የአንድ ህዝብም የመኖርና ምኞቱን የማሟላቱ
ጉዳይ ከተስተካከለ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የተያያዘ ነው። የኢኮኖሚ ዕድገት ደግሞ በሳይንስና
በቴክኖሎጂ ላይ መመስረት አለበት። ወደዚያ ለማምራት ግን በቅድሚያ የህዝባችን መሰረታዊ ፍላጎቶቹ
መሟላት አለባቸው። አንድ ህዝብ ሆዱን ሳይሞላ፣ ንፁህ ውሃ ሳያገኝ፣ መጠለያ ሳይኖረው ወይም ጎጆ
ቤት ውስጥና ቆሻሻ አካባቢ እየኖረ፣ የመማር ዕድል ሳያገኝ፣ እንዲሁም የመታከም ዕድል ሳይኖረው
በደፈናው ስለሳይንስና ስለቴክኖሎጂ አስፈላጊነት ማውራት አንችልም። ከዚህም ባሻገር በደንብ የታቀዱ
ከተማዎችና መንደሮች በሌሉበት አገር እንደዚሁ ስለሳይንስና ስለቴክኖሎጂ ማውራቱ ወደፊት
የሚያራምደን አይደለም። እንዲያውም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሊያድጉና የተፈለገውን ውጤት ሊያስገኙ
የሚችሉት ተጠንተውና ታቅደው በተሰሩ ከተማዎች ውስጥ ብቻ ነው። እንደምናውቀው አብዛኛዎቹ
የኢትዮጵያ ከተማዎች በዕቅድ የተሰሩ አይደሉም። የሰውን መንፈስ የመቅረጽ ኃይላቸው በጣም ደካማ
ነው። በከተማዎች ውስጥ ፓርኮችና ዛፎች የሉም። ወንዞች ደርቀዋል። በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ
ውስጥ የሚሰሩት ቤቶች አቅድ የሌላቸው ናቸው። በአልፉት አስርና ከዚያም በላይ ዐመታት የተሰሩት
ህንጻዎችና በኮዶምኒዩም ስም የሚሰሩት ቤቶች ለአንድ ከተማ ውበት የሚሰጡት አይደሉም። አብዛኛዎች
ጓሮና መዝናኛዎች የላቸውም። በተለይም ህፃናትን፣ ሽማግሌዎችንና ድኩማኖችን በማካተት ታሰበው
የተሰሩ ቤቶች አይደሉም። ሽማግሌዎች እስከ አራተኛና ከዚያም በላይ ፎቆች በእግራቸው ሊወጡ
የማይችሉባቸው የቤት አሰራሮች ናቸው የተስፋፉት። ይህ ዐይነቱ የቤት አስራር ቆሞ ከረጅም ጊዜ አንፃር
የታሰቡና ብዙ ነገሮችን ያካተቱ የቤት አሰራሮች መለመድና መስፋፋት አለባቸው። በአጭሩ ሰው
የሚኖርባቸው ከተማዎች መገንባት አለባቸው። በዚህ መልክ ከተማዎች ባህላዊ ባህርይ ሲኖራቸው
ለፈጠራ ስራም የሚያመቹ ይሆናሉ። ከዚህ ስንነሳ የአንድ መንግስትና የአገሬ ጉዳይ ያገበኛል የሚለው
ምሁር ግዴታና ኃላፊነት የህዝባችንን መሰረታዊ ጉዳዩችን በማሟላት ላይ ከማተኮር አልፎ አገራችን
በአዲስና ዘላቂነት ባለበት መልክ የምትገነባበትን ሁኔታ ማዘጋጀት ነው። ስለሆነም ስለኢኮኖሚ ዕድገት
በምናወራበት ጊዜ እነዚህን መሰረተ-ሃሳቦች በምንም ዐይነት ከጭንቅላታችን ውስጥ ማስወገድ
የለብንም። እንዲያውም የህይወታችን ፍልስፍናዎች መሆን አለባቸው።

ከዚህ በተረፈ በትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ላይ ከማትኮር ይልቅ በትናንሽና በማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ላይ


ማትኮሩ እርስ በእርሱ ለተሳሰረ የኢኮኖሚ ዕድገት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። አብዛኛውን ጊዜ ዕውነተኛ
ፈጠራ በትናንሽና በማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚፈልቅ ነው። በመሆኑም እነዚህን መስኮች
ከምርምርና ከሳይንስ ጣቢያዎች ጋር ማያያዝ ያስፈልጋል። በተለይም በአገልግሎት መስኩ ላይ መረባረብ
መቀነስ አለበት። ካለአግባብና ካለዕቅድ በየቦታዊ የሚሰሩ ሆቴልቤቶች ጥሬ-ሀብትን፣ ውሃንና ኃይልን
በከፍተኛ ደረጃ የሚጋሩ ናቸው። የሆቴልቤቶች መስፋፋት ከምርት ክንዋኔና ከቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር
ያልተያያዘ በመሆኑ የስራ-መስክ ለሚፈልገው ሰፊ ህዝብ በቂ የስራ ዕድል ሊያዘጋጅ ወይም ሊሰጥ
የሚችል አይደለም።

በአጭሩ አገራችን ውስጥ ስርዓትና የተቀነባበረ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ከተፈለገ አገዛዙ ከኒዎ-
ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ መላቀቅ አለበት። የውጭ ኢክስፐርቶችን ምክር በምንም ዐይነት መስማት
የለበትም። አገዛዙ ሁለትና ሶስት ሚሊዮን ዶላር እየከፈለ የአገር ሀብት ማባከን የለበትም። በዚህ መልክ
በየጊዜው ለውጭ ኤክስፐርቶች ለምክራቸው የሚከፈለው ገንዘብ አንድ አስር ሺህ ህዝብ የሚኖርበትን
የተዝረከረከ ከተማ እንደገና ስርዓት ባለው መልክ ሊያስገነባና የስራ መስክ ሊያስከፍት ይችላል። ከዚህ
ቀደም በምዕራቡ ዓለም ጠቅላይ ሚኒስተር ወይም ፕሬዚደንት የነበሩ አሁን ዋና ተግባራቸው
የሶስተኛውን ዓለም አገሮች፣ በተለይም የአፍሪካን መንግስታት በማማከር ገንዘብ መሰብሰብ ነው።
አንዳንድ የአፍሪካ መንግስታት በእነዚህ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተሮች በመታለል መቀመቅ ውስጥ
ገብተዋል። የእነዚህ ትላልቅ ሰዎች ዋና ዓላማም ሳይንሳዊ ምክር መስጠት ሳይሆን፣ እንዴት አድርጎ ሀብት
ከአፍሪካ ወደ ውጭ የሚተላለፍበትን መንገድ ማዘጋጀት ነው። ድሮ የዓለም ባንክ ሰራተኛ የነበረና
ከፍተኛ ቦታ የነበረው ጆን ፐርኪንስ እንደነዚህ ዐይነት ኤክስፐርቶችን አሳሳች ኢኮኖሚስቶች(Economic
Hit Men) ብሎ ይጠራቸዋል። ፍልስፍናቸውም ነፃ ንግድና የኒዎ-ሊበራል ርዕዮተ-ዓለም ነው። ስለሆነም
በእነዚህ „ኤክስፐርቶችና አማካሪዎች“ መታለል አያስፈልግም። በታሪክ ውስጥ ውጤታማ የሆኑ
አገሮች በሙሉ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻሉት በውጭ ኤክስፐርቶች በመመከር ሳይሆን
በራሳቸው የማሰብ ኃይል ብቻ በመመራትና በራሳቸው በመተማመን ነው። በሌላ ወገን ግን የውጭ
ኤክስፐርቶች ሳይንሳዊ አመለካከት እስካላቸው ጊዜ ድረስና የኒዎ-ሊበራሊዝምን አስተሳሰብ
የማያስተጋቡ ከሆኑ ከእነሱ ምክር ልንቀበል እንችላለን። እንደነዚህ ዐይነት ኤክስፐርቶች ደግሞ ብዙ
ገንዘብ የሚጠይቁ አይደሉም። ለማንኛውም ኢትዮጵያን እንደ አንድ ጠንካራ አገር ለመገንባት የምንመኝ
ከሆነ የግዴታ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ አለብን። የአስተሳሰብ ለውጥ ለማድረግ ደግሞ የግዴታ
በሳይንስና በፍልስፍና ዓለም ውስጥ የተደረገውን የጦፈ ክርክር ጠጋ ብሎ መመልከት ያስፈልጋል። በዚህ
መልክ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ፈላስፋዎች ተፈጥሮንና ህብረተሰብን ለምን በተለያየ መልክ
እንደሚተረጉሙና ትክክል ነው ብለው በሚያምኑበት የሳይንስ መሳሪያ ህብረተሰብአቸውን ለመቅረጽ
እንደሚፈልጉ ለማወቅ ይረዳናል። ስለሆነም ትክክለኛውን ዕውቀትና የአገር ግንባታ ዘዴ ሳይንሳዊነት
ከሌለው ነጥሎ በማውጣት አዲስና ጤናማ ህብረተሰብ ለመገንባት እንችላለን። ተግባራዊ ለማድረግ
የምንፈልገው ፖሊሲ በአቦሰጡኝ መሆኑ ቀርቶ ሳይንስንና ፍልስፍናን የሚመረኮዝ ይሆናል ማለት
ነው። መልካም ግንዛቤ !!

Back to Front Page

fekadubekele@gmx.de

Literature

Aglietta, Michael(1979), The Theory of Capitalist Regulation: The US Experience, London

Amin, Samir(1974), Accumulation on a World Scale: A Criticque of the Theory of

Underdevelopment, New York

Angresano, James(1997),The Political Economy of Gunnar Myrdal, UK

Bekele, Fekadu(2016), African Predicaments and the method of solving them effectively,

Berlin

Brose E. Dorn (1992),The Politics of Technological Change in Prussia, Princeton & New

Jersey

Burgis, Tom (2016), The Looting Machine, London

Byrne H. Patrik & Hefling C. Charles (eds.) (1999), Collected Works of Bernard Lonergan,

Macroeconomic Dynamics: An Essay in Circulation Analaysis, Toronto

Cowley, Catherine (2006), The Value of Money, London & New York
Daniel K. Finn(ed.) (2010),The True Wealth of Nations: Catholic Social Thought and

Economic Life, New York

Goldthwaite A. Richard(2009), The Economy of Renaissance Florence, Baltimore & Maryland

GordonJ. Robert (2000), Macroeconomics, New York

Gorga, Camine (2010), The Economic Process: An Instantaneous Non-Newtonian Picture,

New York

Goswami, Amit (2011), How Quantum Activism Can Save Civilization, USA

Herrmann, Ulrike (2015), The Triumpf of Capital: How wealth appears in the world, Berlin

Keen, Steve (2010), Debunking Economics: The Naked Emperor Dethroned, London

Klein, Naomi (2007), The Schock Doctrine, London

Landes S. David (1999), The Wealth and Poverty of Nations, New York & London

Landes S. David (2003), The Unbound Prometheus: Technological Change and Industrial

Development in Western Europe from 1750 to the Present, New


York

Mason, Paul (2015), Postcapitalism: A Guide to our Future, UK

Meštrović, G.Stjepan(1993), The barbarian temperament: Toward a postmodern critical

theory, London & New York

Molander, Per(2017), The Anatomy of Inequality: Where does it come and how we can

Control it, Frankfurt/Main

Nachtwey, Oliver( 2016) The Declinig Society: Dissent in the Age of Regressive Modernity,

Berlin

Piketty, Thomas (2014), Capital in the Twenty-First Century, London

Polanyi, Karl (1971), The Great Transformation, New York

Reinert S. Erik (2007), How Rich Countries Got Rich… and Why Poor Countries Stay Poor,

London

Schulmeister, Stephan (2018), The Road to Prosperity, Salzburg


Schumpeter A. Joseph(1951), The Theory of Economic Development, Cambridge &

Massachusetts

Soddy, Frederick(1983), Wealth, Vitual Wealth and Debt: The Solution of the Economic

Paradox, London

Strong, Tom & Lock, Andy (2010), Social Constructionism, UK

You might also like